ዚምባብዌ አዲስ የባንክ ኖቶችን ማሰራጨት ልትጀምር ነው

ዚምባብዌ

በኢኮኖሚያ ቀውስ እየተናጠች ያለችው ዚምባብዌ አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ማሰራጨት ልትጀምር ነው።

በሃገሪቱ የተከሰተውን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ይቀርፋል በማለት ነው የዚምባብዌ ማዕከላዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ አዲሱን መገበያያ ገንዘብ ማሰራጨት የሚጀምረው።

ከፍተኛ የዋጋ ንረት ባለባት ሃገር አዲስ መገበያያ ገንዘብ ወደ ገብያው ማስገባት ያለውን የዋጋ ንረት እንዲጨምር ያደርጋል የሚል ስጋት በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዘንድ በስፋት እየተሰማ ነው።

ይሁን እንጂ ማዕከላዊ ባንኩ የሚያሰራጫቸው አዲሶቹ ባለ ሁለት እና ባለ አምስት የባንክ ኖቶች የሚያስከትሉት ተጽእኖ እምብዛም ነው እያለ ነው።

ይልቁንም በሃገሪቱ የተከሰተውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያቃልላሉ ይላል ማዕከላዊ ባንኩ።

በርካታ የሃገሪቱ ዜጎች የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት እጥረት መከሰቱን ተከትሎ በባንክ ያላቸውን ገንዘብ ወጪ ማድረግ ተስኗቸው ቆይተዋል።

መንግሥት አዲስ የባንክ ኖቶችን ማሳተም አማራጭን ይፋ ካደረገ በኋላ በሃገሪቱ የነበረው የዋጋ ንረት ከአንድ ወደ ሶስት አሃዝ ከፍ ብሏል።

አሁን ላይ መንግሥት ይፋዊ የዋጋ ንረት መጠኑን ማሳወቅ አቁሟል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ያለው የዋጋ ንረት ከ300% በላይ እንደሆነ ይገመታል።

የዚምባብዌ ዶላር የመግዛት አቅም እጅጉን መዳከሙን ተከትሎ እ.አ.አ. ከ2009 ጀምሮ ዜጎች በአሜሪካ ዶላር መገበያየት ጀምረው ነበር።

ይሁን አንጂ መንግሥት ዜጎች በዚምባብዌ ገንዘብ መገበያየት እንዲጀምሩ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።