ሊባኖስ፡ በቤይሩቱ ፍንዳታ አንድ ኢትዮጵያዊ መሞቱ ተገለፀ

ጭስና እሳት ሲትጎለጎል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሊባኖስ መዲና ቤሩት ከትላንት ወዲያ በደረሰው ከባድ ፍንዳታ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ማለፉን በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል የሆኑት አቶ ተመስገን ኡመር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዲት በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባትና ህክምና እየተከታተለች የነበረች ኢትዮጵያዊት በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ እንደምትገኝም አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

Presentational grey line

ከዚህም በተጨማሪ አስር ኢትዮጵያዊያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ቆንስላው በትናንትናው ዕለት ገልጿል።

ቢቢሲ በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማናገር እንዳረጋገጠው በዚህ ከባድ ፍንዳታ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጉዳት ደርሷል።

በከተማዋ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስላሉበት ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለ ያለው በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ እንዳሳወቀው የደረሰው ፍንዳታ ከባድ ከመሆኑ አንጻር በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ላይም ጉዳት ደርሷል።

አቶ ተመስገን ለቢቢሲ በቆንስላውና በኢትዮጵያ ማህበረሰብ በኩል ጉዳት እንደደረሰባቸው የተረጋገጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አስር መሆኑንም በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።

ከእነዚህም መካከል ሁለቱ መካከለኛ፣ ሰባቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው አንድ ግለሰብ መሞቱ ቢነገራቸውም ከሚሰራበት ተቋምም ሆነ ከሊባኖስ መንግሥት የተጣራ መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልፀው ነበር።

እንደ ቆንስላው ከሆነ መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ሁኔታ የሚታከሙበት ሆስፒታል ድረስ በመሄድ መመልከታቸውን ገልፀው፣ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሰባቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ግን ህክምና አግኝተው ወዲያው ወደ መኖሪያቸው መሄዳቸውን አስረድተዋል።

አቶ ተመስገን አክለው ወደ ቆንስላውም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ያልመጡ ሌሎችም ጉዳት የደረሰባቸው ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል።

በቤይሩት ትናንት አመሻሽ ላይ ባጋጠመው ከባድ ፍንዳታ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

የሊባኖስ ፕሬዝደንት ማይክል አኑን ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ ላይ 2750 ቶን የሚመዝን አልሙኒየም ናይትሬት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ እንደነበር ገልፀዋል።

በቤይሩት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ከፍንዳታው በኋላ የቆንስላው ኃላፊና ሠራተኞች የኢትዮጵያዊያኑን ሁኔታ ለማወቅ ሌሊቱን ወደ ተለያዩ አካባቢዎችን የህክምና ቦታዎች በመሄድ ሲያጣሩ ነበር።

በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ማህበር ከሆነው "የእኛ ለእኛ በስደት" አባላት ቢቢሲ በማጣራት ባጋጠመው ፍንዳታ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ኢትዮጵያዊያን ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ቁጥራቸው ያልታወቀ ደግሞ የት እንዳሉ አለመታወቁን አረጋግጧል።

ነገር ግን እስካሁን በተገኘው መረጃ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂት ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ቀላል የሚባል ጉዳት አጋጥሟቸው ትናንት ከፍንዳታው በኋላ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ድጋፍ አግኝተው መመለሳቸው ተገልጿል።

የማኅበሩ አባላት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባላቸው መረጃ መሰረት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ላይ ጉዳት ደርሶ ሆስፒታል መግባታቸውንና አንዲት ኢትዮጵያዊት ያለችበትን ለማወቅ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማኅበሩ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን ማግኘት ስላልቻሏቸው ጓደኞቻቸው በተደጋጋሚ እየጠየቁ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

የወደመው የወደብ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የወደመው የወደብ አካባቢ

የቤይሩቱ ንዳታ በኢትዮጵያዊቷ ዓይን

በቤይሩት ነዋሪ የሆነችው ጽጌረዳ ብርሃኑ ትናንት በከተማዋ ቤይሩት ስለደረሰው ፍንዳታ ለቢቢሲ ስትናገር "ሕልም የሚመስል እውነት እና የሚያስፈራ" ነበር ብላለች።

ፍንዳታው የተከሰተው ትናንት፣ ማክሰኞ እለት፣ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት አካባቢ መሆኑን አስታውሳ፣ እርሷ በወቅቱ ከጓደኞቿ ጋር ተሰብስባ አሽፈርዬ የሚባል አካባቢ እንደነበረች ትናገራለች።

ፍንዳታው በደረሰበት ወቅት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ለችግር ለተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን የምግብ እርዳታ ለማቅረብ በሚሰባሰቡበት ስፍራ ሰዎችን እያስተናገዱ ነበር።

ኢትዮጵያዊያኑ በፍንዳታው ህንፃዎች ሲንቀጠቀጡ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ መስሏቸው እንደነበር ገልጻ፣ ወደ ዋናው መንገድ በምትወጣበት ወቅት በፍንዳታው ከባድ ውድመት መድረሱን ማስተዋሏን ገልፃለች።

እርሷ ያለችበት አሽረፍዬ፣ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ የሆኑት ዋርኒኬል፣ ጅማይት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ፍንዳታው የደረሰበት የወደብ አካባቢ ጽጌረዳ ከምትኖርበት ከአሽረፍዬ የ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ መንገድ መሆኑንም ጠቅሳለች።

ከፍንዳታው በኋላ ወደ ጎዳና ስትወጣ በደም ተነክረው የሚሮጡ፣ የሚያለቅሱ ሰዎች እንዲሁም አውራ ጎዳናዎች በተሰባበሩ መስታወቶች ተሞልተው በሰዎች ተጨናንቀው እንደነበር ትናገራለች።

በወቅቱ በተለያዩ ሆቴሎች የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቀላል ጉዳት ብቻ አጋጥሟቸው መትረፋቸውንም ማረጋገጧን ለቢቢሲ ገልፃለች።

ሆስፒታሎች እርዳታ ለተጎጂ ግለሰቦች

ከፍንዳታው በኋላ በቤይሩት ከተማ ውስጥ የመብራት፣ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በከተማዋ ያሉ ሆስፒታሎች በሙሉ በአደጋው በተጎዱ ሰዎች ተሞልተው ነበር።

በፍንዳታው ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰ በመሆኑ ወደ ሆስፒታሎች የሚመጣው ሰው ማከም ከሚችሉት በላይ ስለነበረ በተቋማቱ ግቢ እና የመናፈሻ ስፍራዎች ላይ ህክምና ለመስጠት ተገደው ነበር።

"በሆስፒታሉ ስደርስ በርካታ ሰዎች እየመጡ ቁስላቸው እየታሸገላቸው ወደ መጡበት ሲመለሱ ተመልክቻለሁ፤ ታሞ የሚታከም ሰው አልነበረም። ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለ አይመስልም" ነበር ትላለች በሆስፒታል ውስጥ ያየችውን ጽጌረዳ ለቢቢሲ ስትናገር።

"በሆስፒታሎች ውስጥ ህክምና የሚሰጠው ተጎድቶ ለመጣ ሁሉ ነበር" የምትለው ጽጌረዳ፣ እስከ ለሊቱ 9፡00 ሰዓት ድረስ በተለያዩ ሆስፒታሎች መሄዷን በማስታወስ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁስላቸው እየተጠረገና እየታሸጉ መውጣታቸውን ነገር ግን በትክክል ስንት ኢትዮጵያዊያን እንደተጎዱ እርግጠኛ መረጃ እንዳላገኘች ትናገራለች።

"አንዲት ኢትዮጵያ መሞቷን ብሰማም ማረጋገጥ አልቻልኩም" የምትለው ጽጌረዳ፣ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በርከት ያሉ ኢትዮጵያን ቢኖሩም ቀላል ህክምና አግኝተው መሄዳቸውን ማረጋገጧን ጨምራ ትናገራለች።

ነዋሪዎች ሲሸሹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢትዮጵያ ቆንስላ

እርሷ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያንን ለማየት ወደ ሆስፒታል በምትሄድበት ወቅት በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ የሆኑት አምባሳደር ተመስገን በተለያዩ ሆስፒታሎች እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያዊያኑ ያሉበትን ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን በመስማቷ እንዳስደነቃት ለቢቢሲ ገልጻለች።

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቆንስላ ኃላፊዎች በዜጎቻቸው ችግር በሚገጥማቸው ወቅት በፍጥነት ምላሽ እንደማይሰጡ በማንሳት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የቆንስላው ተግባር ተስፋ እንደሰጣት ጠቅሳለች።

ፍንዳታው አሁን ካደረሰው ጉዳት ባሻገር በኢትዮጵያዊያን ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እንደሚኖረው የምትናገረው ጽጌረዳ፤ ፍንዳታው በርካታ የገበያ ማዕከሎችን በማውደሙ እዚያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩና በዚህም ሳቢያ ከሥራ ውጪ ስለሚሆኑ ለተደራራቢ ችግር መጋለጣቸው አይቀርም ስትል ትናገራለች።

እንኳን እኛ የአገሪቱ ዜጎች እያለቀሱ ነው የምትለው ጽጌረዳ በምጣኔ ሃብቱ መንኮታኮት፣ በኮሮናቨይረስ ወረርሽኝ ላይ ይህ ችግር መጨመሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑን ትገልፃለች።

"ባለው ችግር ላይ እጥፍ ችግር ነው የተጨመረው" በማለትም የችግሩን ግዝፈት ታስረዳለች።

የደረሰ ጉዳት

በከተማዋ ላይ ባጋጠመው ከባድ ፍንዳት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

ፕሬዝደንት ማይክል አኑን ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ ላይ 2750 ቶን የሚመዝን አልሙኒየም ናይትሬት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ ነበር ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ለዛሬ አስቸኳይ የካቢኔ ሰብሰባ የጠሩ ሲሆን፤ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

ሌባኖስ ለሦስት ቀናትም የብሔራዊ የሃዘን ቀን አውጃለች። ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንቱ 66 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲመደብ አዘዋል።