ለ'አገራችን አፈር አብቁን' ሲሉ የሚማፀኑት ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, JOSEPH EID
በሊባኖስ ለበርካታ አስርተ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ድቀት መከሰቱን ተከትሎ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ለከፋ መጋለጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በምጣኔ ሃብት ድቀቱ ምክንያት አሰሪዎች ደሞዝ መክፈል ባለመቻላቸው ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጎዳና ላይ እየተጣሉ ይገኛሉ።
በሊባኖስ ለበርካታ ዓመታት የኖረችው ትነበብ ኃይሉ በርካታ ኢትዮጵያውን በአሰሪዎቻቸው እየተጣሉ ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ነግራናለች። ''ሜዳ ላይ ከመጣል" ምግብ እና መጠለያ ለማግኘት ብለው ደሞዝ ሳይከፈላቸው እየሰሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ቁጥራቸው እንደሚልቅ ጨምራ ትናገራለች።
የሊባኖስ የኢኮኖሚ ድቀት
የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ 'ሊባኒስ ፓዎንድ' ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለው ግነኙነት ሰማይ ነክቷል። ሊባኒስ ፓዎንድ በታሪክ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ 70 በመቶ ወርዷል።
የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሊባኖስን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።
በውዝፍ እድ ውስጥ የምትገኘው ሌባኖስ፤ ሥራ አጥ በሆኑ ወጣቶች በተቃውሞ ስትናጥ ቆይታለች። የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ የተጣለው ገደብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ግን 'ከድጡ ወደ ማጡ' እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።
ይህ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት መዳከም፤ በሊባኖስ ለሚገኙ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ፈተናን ይዞ መጥቷል።
"ማዳም . . . ጥለኝ ሄደች"
በአሰሪዎቻቸው እንዲወጡ ከተደረጉት መካከል ጣይቱ ሙለታ አንዷ ነች። ጣይቱ ወደ ሊባኖስ መዲና ቤሩት ከመጣች ዓመታት መቆጠራቸውን ታስታውሳለች።
ጣይቱ አሰሪዎቿ ሁለት ቦታ ያሰሯት እንደነበረ ትገልጻለች። "ሱቅ እና ምግብ ቤት አጸዳለሁ። የሚከፍሉት ሲያጡ ሁለት ዓመት ሰርቼ 'ያለሸ የአምስት ነው' አሉኝ። ከዛ ደግሞ የሰጡኝ የሶስት ወር ብቻ ነው" በማለት የደረሰባትን በደል ትናገራለች።
ከጣይቱ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ የምትጋራው ወርቂቱ ቦኬ ነች። ወርቂቱ 3 ዓመታትን በሊባኖስ ስታሳለፍ "የማይነግር መከራን አይቻለሁ" ትላለች። "ያለ እረፍት ስሠራ ነበር። በሽታው ከመጣ በኋላ ማዳም (አሰሪዋ) የምትከፍለው ስታጣ እጥልሻለሁ እያለች ታስፈራራኝ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት ምንም ነገር ሳልይዝ በታክሲ ይዛኝ ወጥታ ኢምባሲው ጋር ጥላኝ ሄደች" በማለት አሰሪዋ ያደረገችውን ታስረዳለች።
ጣይቱም ሆነች ወርቂቱ፤ አሰሪዎቻቸው አውጥተው ከጣሏቸው በኋላ "በረንዳ ላይ ለማደር" መገደዳቸውን ይናገራሉ።
"የመጀመሪያዎቹን ቀናት በረንዳ ላይ ነው ያደርኩት። ከእኔ ጋር ብዙ ልጆች ነበሩ። ከዛ የኢትዮጵያ ልጆች አንስተውን ሆቴል አስቀምጠውናል። ምግብ እየሰጡን ነው። እዛ ቆንስላው ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች መዝገበውናል። በዚህ ሁኔታ እዚህ እስከመቼ እንደምቆይ አላውቅም" ትላለች ወርቂቱ።
"ሆቴል ውስጥ ነኝ። በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት ሆነን ነው ያለነው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከማዳም ቤት የተጣሉ ናቸው" በማለት ጣይቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ወርቂቱ ለሶስት ዓመታት በቤሩት ስትኖር ከቤት ወጥታ እንደማታውቅ እና የኢትዮጵያውያኑ ድጋፍ ቢቋረጥ መሄጃ እንደሌላት ትናገራለች። "አገሩን አላውቅም፤ አንድም የማውቀው ሰው የለም። ሶስት ዓመት ሙሉ ከቤት ወጥቼ አላውቅም" ትላለች።
የኢትዮጵያውያኑ ድጋፍ
እንደ ወርቂቱ እና ጣይቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመንገድ እያነሱ በሆቴል እና በመኖሪያ ቤት እያቆዩ እና የምግብ ድጋፍ እያደረጉ ካሉ አካላት መካከል አንዱ 'እኛ ለኛ በስደት' የተሰኘው በጎ አድራጊ ድርጅት አንዱ ነው።
በእና ለኛ በስደት አስተባባሪ የሆነችው ጽጌሬዳ ብርሃኑ፤ ድርጅቱ ከተመሰረት ሶስት ዓመት እንዳስቆጠረ እና በእስካሁኑ ቆይታቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተለያየ መልክ ያለው ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ታስረዳለች።
የክህሎት ስልጠና መስጠት፣ ቤት አልባ ለሆኑ መጠለያ ማቅረብ፣ ለታማሚዎች እና አቅመ ደካሞች ቲኬት ገዝቶ ወደ አገር ቤት ከመላክ በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስተማሪ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያዘጋጃሉ።
በሊባኖስ የአንድ የቤት ሠራተኛ ደሞዝ በአማካይ 150 የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ የምትናገረው ጽጌሬዳ፤ የአገሪቱ ዜጎች በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የመክፈል አቅማቸውም እጅጉን ተዳክሟል። ዶላር ከባንክ ማውጣትም አይችሉም። በዚህም ምክንያት የምጣኔ ሃብት ቀውሱ መከሰት ከጀመረበት ከእአአ ኦክቶበር 2017 ጀምሮ ደሞዝ ያልተከፈላቸው በርካታ ሠራተኞች አሉ ትላለች።
ለመክፈል አቅም እና ፍላጎት ያላቸውም ቢሆኑ ደሞዝ ለሰራተኞች እየከፈሉ ያሉት በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ነው።
"አንድ ልጅ ለምሳሌ ወደ ሃገር ቤት ገንዘብ መላክ ብትፈልግ፤ በሃዋላ ገንዘብ የሚልኩ ድርጅቶች ዶላር ብቻ ስለሚቀበሉ፤ ዶላር ከጥቁር ገበያ ላይ ገዝተው ሲልኩ የገንዘባቸው 80 በመቶ ያጣሉ" ትላለች።
ከቤት ሠራተኝነት ውጩ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ኢትዮጵያንም የምጣኔ ሃብቱ ድቀት ከኮቪድ-19 ጋር ተደማምሮ ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ታስረዳለች።
ወደ አገር ቤት መመለስ
ጣይቱ እና ወርቂቱ ከምንም በላይ "ወደ አገራችን መመለስ ብቻ ነው የምንፈልገው" ይላሉ። ለዓመታት በአሰሪዎቻቸው የደረሰባቸው በደል ረስተው፤ ለዓመታት ያልተከፈላቸው ውዝፍ ክፍያ ይቅርብን ብለው ማየት የሚሹት የአገራቸውን ምድር ብቻ ነው።
በቤሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ከዚህ ቀደም የጉዞ ሰነድ ለሌላቸው ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ አዘጋጅቶ፤ በሁለት በረራዎች 658 ሰዎች ከቤሩት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ማድረጉን በሌባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ቆንስል የሆኑት አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ ያስታውሳሉ።
በእስር ላይ፣ በመጠለያ፣ ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው፣ በህመም ምክንያት መስራት ባለመቻላቸው ከሊባኖስ ለመውጣት ያመለከቱ ዜጎች በሁለቱ በረራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ያስታውሳሉ።
ከእነዚህ በረራዎች በአንዱ ላይ የነበረችው እና ስሟ እንዲጠቀሰ ያልፈለገች ኢትዮጵያዊት፤ አዲስ አበባ ከደረሰች በኋለ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ በለይቶ ማቆያ የነበራትን ጊዜ አጠናቅቃ ለመውጣት እየተጠባበቀች እንደሆነ ተናግራለች። "አሁን የአእምሮ ሰላም አግቻለሁ" ትላለች።

በመካከለኛ ምሥራቅ በምትገኘው ሊባኖስ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህም መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው መሆናቸውን ከቆንስላ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የቆንስላው ቆንስል የሆኑት አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ።
አቶ አክሊሉ "ሕጋዊ የሆኑ ሠራተኞች ለብዙ ወራት የሰሩበት ደሞዝ ሳይከፈላቸው አሰሪዎቻቸው 'ቆንስላ ጽ/ቤት የአየር ቲኬት ከፍሎ ይልካችኋል' ብለው በማታለል ሜዳ ላይ ጥለው እየሄዱ ነው" ይላሉ።
እንደ ማሳያም ባለፉት ሳምንታት 133 የሚሆኑ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸው ተጥለዋል።
ይህ የአሰሪዎች ተግባር ዓለም አቀፍ የሠራተኛ መብትን የሚጥስ ከመሆኑም በተጨማሪ ኢሰብዓዊ ስለሆን ይህን ድርጊት በደብዳቤ ለአገሪቱ የሠራተኛ ሚንስቴር አሳውቀናል ብለዋል። "በደብዳቤው ላይ ሊባኖሳውያን አሰሪዎች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እና ውዝፍ ያልተከፈለ ደሞዝ ያለባቸው በአስቸኳይ ለሰራተኞች እንዲከፍሉ ጠይቀናል" ሲሉ ተናግረዋል።
ለቆንስሉ ጥያቄ የሊባኖስ መንግሥት የሰጠው ምላሽ "እየሰራንበት ነው" የሚል መሆኑን አቶ አክሊሉ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር እና የሊባኖስ የሠራተኛ ሚንስትር በጉዳዩ ላይ በስልክ መነጋገራቸውንም አስታውሰዋል።
የሊባኖስ መንግሥት ግዴታውን አልተወጣም የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ "የሊባኖስ መንግሥት አሰሪ በሆኑ ዜጎቹ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እየወሰደ አይደለም። በሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን በደል እያሳወቅናቸው ነው። አሰሪዎቹን ጠርቶ ለፈጸሙት በደል የሚገባቸውን ካልሰጠ ከባድ ነው የሚሆነው። እኛም ጫና እያሳደርን ነው። ውጪ ጉዳይም ይህን እንዲያደረገ ነው" ይላሉ።

የሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ማርሊን አታላህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሠራተኞቹ እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጋር አብረን እየሰራን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያኑ የቤት ሠራተኞችን በሆቴል ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል እንዳሳደሯቸውና ወደ መጠለያዎችም መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ለቤት ሠራተኞቹ ደመወዝ ባለመከፈልም ሆነ በመባረራቸው የተከሰሰ አሰሪ አለመኖሩን ማርሊን አታላህ የተናገሩ ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ ግን ምርመራዎች እንደተጀመሩ ገልፀዋል።













