በቤይሩቱ ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሌባኖሷ መዲና ቤይሩት በተከሰተው ከባድ ፍንዳታ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
ትናንት ከሰዓት ላይ ፍንዳታው ሲያጋጥም መላ መዲናዋ በፍንዳታው ተናውጣ ነበር።
ፕሬዝደንት ማይክል አኑን ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ ላይ 2750 ቶን የሚመዝን አልሙኒየም ናይትሬት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ ነበር ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ለዛሬ አስቸኳይ የካቢኔ ሰብሰባ የጠሩ ሲሆን፤ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
ሌባኖስ ለሦስት ቀናትም የብሔራዊ የሃዘን ቀን አውጃለች። ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንቱ 66 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲመደብ አዘዋል።
“ከባድ አደጋ ነው የገጠመን። ህይወታቸውን ያጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በየቦታው ነው የሚገኙት” ያሉት የሌባኖስ ቀይ መስቀል ሥራ አስኪያጅ ጆርጅ ጄታኒ ናቸው።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አሁንም ድረስ ተጎጂዎችን ከፍርስራሽ ስር እያወጡ ይገኛሉ። በዚህም የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል።
ትናንት ባለስልጣናት ለፍንዳታው ቀጥተኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ምርመራ እንዲካሄድ ወስነው ነበር።
የሌባኖስ የጦር ኃላፊ ለፍንዳታው ተጠያቂ ሆነው የሚገኙት ላይ የሚቻለውን “ከፍተኛ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል” ብለዋል።
አልሙኒየም ናይትሬት ምንድነው?
አልሙኒየም ናይትሬት በርካታ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም፤ አብዛኛውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው ለእርሻ ሥራ ማዳበሪያነት እና ተቀጣጠይ ነገር ሆኖ ነው።
አልሙኒየም ናይትሬት ከእሳት ጋር ከተገናኘ እጅግ ተቀጣጣይ ሲሆን እንደመጠኑ ፍንዳታ ያስከትላል።
በእሳት ሲያያዝ ናይትሮጅን ኦክሳይድ እና አሞኒያ ጋዝ የሚባሉ ለጤና ጎጂ የሆኑ አደገኛ የጋዝ ልቀትን ያስከትላል።
ይህ ኬሚካል አደገኛ ተቀጣጣይ እንደመሆኑ መጠን የሚጓጓዝበት እና የሚከማችበት ሁኔታን በተመለከት ጥብቅ መመሪያዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
አልሙኒየም ናይትሬቱ ለምን አስፈለገ?
የሌባኖስ ዜጎች እንዴት ከ2700 ቶን በለይ የሚመዝን ተቀጣጣይ ነገር በመሃል ከተማ በመኖሪያ ስፍራ ላይ ይከማቻል ሲሉ እየጠየቁ ይገኛሉ። የአገሪቱ ፕረዝደንት አልሙኒየም ናይትሬቱ ለስድስት ዓመታት በስፍራው ተከማችቶ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዜጎች ይህ "የመንግሥት እንዝላልነትን የሚያሳይ ነው" እያሉ አጥብቅ የመንግሥትን ቸልተኝነት እየኮነኑ ይገኛሉ።
የመከከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ የቻተም ሃውስ ፕሮግራም መሪ የሆነችው ሊና ካሃቲብ፤ "2750 ቶን አልሙኒየም ናይትሬት ማን ምን ሊያደርግለት ይፈልጋል?" ስትል ጠይቃለች።
ሊና ይህ ኬሚካል ተቀጣጣይ ነገሮችን ለመሠራት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በማስታወስ፤ የሌባኖሱ ታጣቂ ኃይል ሔዝቦላህ የቤይሩት ወደብ በመጠቀም አልሙኒየም ናይትሬት በድብቅ ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግራለች።
ይሁን እንጂ አልሙኒየም ናይትሬቱ ይህን አይነት ጉዳት እንዲያስከትል ያደረገው ምን እንደሆነ አልተረጋገጠም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፍንዳታው ያጋጠመው የከተማዋ ወደብ የሚገኝበት አቅራቢያ ሲሆን በስፍራው ተከማችቶ የነበረው አልሙኒያም ናይትሬት ከ6 ዓመታት በፊት ከአንድ መርከብ ላይ ወርዶ በስፍራው እንዲከማች ተደርጓል።
ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የሌባኖስ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ነው።
የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሌባኖስን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።
ከሳምንታት በፊት ሥራ አጥ የሆኑ የሌባኖስ ወጣቶች አደባባይ ወጥተዋል። የቫይረሱን ስርጭትም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ግን 'ከድጥ ወደ ማጡ' እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2005 ላይ የቀድሞ የሌባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ራፊክ ሃሪሪን ገድለዋል የተባሉ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የፊታችን ዓርብ በሌሉበት ብይን ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው ፍንዳታው ያጋጠመው።
በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አራቱም ግለሰቦች በኢራን መንግሥት የሚደገፈው የሔዝቦላህ ቡድን አባላት ናቸው።
ሔዝቦላህ በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ ውስጥ እጄ የለበትም ሲል በተደጋጋሚ ተከላክሏል።
የተፈጠረው ምን ነበር?
ፍንዳታው ያጋጠመው ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ገደማ ላይ ነበር።
ወደብ አቅራቢያ የደረሰው ፍንዳታ ወደቡን ከሥራ ውጪ አድርጎታል። ፍንዳታው የፈጠረው ንቅናቄ ከ240 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ተሰምቶ ነበር።
በቆጵሮስ ደሴት ላይ የሚኖሩ ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥ መስሎን ነበር ብለዋል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ ሰዎች ምስልም ማስመልክት ጀመሩ።
በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ ህጻዎች እና ተሽከርካሪዎች በፍንዳታው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ታይተዋል።
“በፍንዳታው ዙሪያ የነበሩ ህንጻዎች በሙሉ ፈራርሰዋል። የመስታውት ስብርባሪ ላይ እየተራመድኩ እገኛለሁ” ሲል አንድ የዓይን እማኛ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ሆስፒታሎች የሕክምና እርዳታ በሚፈልጉ ሰዎች መጨናነቅ የጀመሩት ወዲያው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
አስክሬን ማቆያ ስፍራ እየተዘጋጀ ነው
እስካሁን በፍንዳታው ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይረጋጋጥ እንጂ ከፍንዳታው መጠን እና ካደረሰው ጉዳት አንጻር የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የሌባኖስ ቀይ መስቀል ማህበር ከሌባኖስ የጤና ባለስልጣናት ጋር በመሆን የሰዎች አስክሬን እሰከሚለይ እንዲሁም ለቀብር እስኪዘጋጅ ድረስ የማቆያ ስፍራ ለማቋቋም እየሰሩ መሆኑ ተነግሯል።
ፍንዳታው ያጋጠመበት ስፍራ ይሰሩ የነበሩ የወደብ ሠራተኞች ከፍተኛ ጉዳት እንዳጋጠማቸው ታውቋል።
ከ300ሺህ በላይ ቤት አልባ ሆነዋል
የቤይሩት አስተዳዳሪ የሆኑት ማርዋን አባውድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፍንዳታው ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ቤት አልባ አድርጓል።
አስተዳዳሪው ጨምረው እንደተናገሩት በፍንዳታው ምክንያት የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲለካ ከ3-5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ተናግረዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ 'ዘ ኢኮኖሚስት' አርታዒ ከታች ያሉትን የመኖሪያ ቤቱን ምስል በትዊተር ገጹ ላይ አጋርቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ















