በሊባኖስ የኢኮኖሚ ቀውሱን ተከትሎ ተቃውሞዎች እየተባባሱ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሊባኖስ ያጋጠማትን የመገበያያ ገንዘቧ መድከምን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የሊባኖስ መገበያያ ገንዘብ ዋጋ በታሪኳ ዝቅተኛ ወደሚባል ደረጃ በመውረዱና 70 በመቶ የሚሆነውን አቅሙን በማጣቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ አገሪቷ ተቃውሞዎችን እያስተናገደች ነው፡፡ ቁጣዎችም ተባብሰዋል፡፡
የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተርም የኢኮኖሚ ቀውስ ላይ ውይይት ለማድረግ አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡
ተቃውሞዎቹ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ እንደገና ተጀምሯል፡፡
የሊባኖስ ፓውንድ ዋጋ መውደቅ አገሪቷን በአስርት ዓመታት ውስጥ አስከፊ ወደ ሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ከቷታል፡፡
በጥሬ ገንዘብ ምንዛሬ ላይ የተሰማሩ አብዛኞቹ ሊባኖሳዊያንም ለድህነት ተዳርገዋል፡፡ በወረርሽኙ ወቅትም ችግራቸው ተባብሷል፡፡
በሊባኖሷ ከተማ ቤሩት የቢቢሲ ዘጋቢ ሊና ሲንጃብ እንደገለጸችው፤ ሐሙስ ዕለት ምሽት በከተማዋ እንብርት ላይ ተሰባስበው የነበሩ ተቃዋሚዎች እሳት በማቀጣጠል እና መንገዶችን በመዝጋት ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የአኮኖሚ ቀውሱን ተከትሎ በመጀመሪያዎቹ ወራት በነበሩት ተቃውሞዎች ፖለቲካዊ ለውጥ ለመጠየቅ የተደረጉ ቢሆንም የአሁኑ ግን መነሻው ርሃብ ነው፡፡
በአገሪቷ የሥራ አጦች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል፡፡ አብዛኞቹ ሊባኖሳዊያንም ለሰሩበት የሚከፈላቸው ዋጋው በወደቀው የአገሪቷ ገንዘብ ነው፡፡ በመሆኑም ለአብዛኞቹ ቤተሰቦች ምግብና መሰረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ፈታኝ ሆኗል፡፡
ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዷ "ሊባኖስ ሁል ጊዜ በተቃውሞ ውስጥ ነው ያለችው ፤ ይህ ማለት ጥረታችን እና ጩኸታችን ለውጥ ማምጣት አልቻለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በበለጠ ተቃውሞ ማሰማት አለብን" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ አብዛኞቹ አሁን እየታየ ያለው ችግር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1975 ሊባኖስ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ቀድሞ የነበረውን ጊዜ እንደሚያስታውሳቸው እና ተቃውሞው በዚህ ሁኔታ እየቀጠለ ከሄደ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አሳስቧቸዋል፡፡
ሌላኛው ተቃዋሚም "ዛሬ የአንድ ዶላር ምንዛሬ 7ሺህ የሊባኖስ ፓውንድ ደርሷል፡፡ የቤት ኪራይ ለመክፈልም ሆነ ምግብ ለመመገብ አልቻልንም ፤ በመሆኑም የዶላር ምንዛሬው ዝቅ ካላላ በስተቀር እና ጥያቄዎቻችን ካልተመለሱ እዚሁ እንቆያለን ፤ ያገኘነው ጠቅላይ ሚኒስተርም ከዚህ ቀደም ከነበረው የባሰ ነው" ብለዋል፡፡
ከቤሩት ውጭ ያሉ በርካታ መንገዶች አሁንም እንደተዘጉ ናቸው፡፡
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽን ቀድሞም ሌባኖስ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ጸረ መንግሥት ተቃውሞዎችን አስነስቷል፡፡
ምንም እንኳን የአገሪቷ መንግሥት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሰጠው ምላሽ ቢመሰገንም ግማሽ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው ከድህነት ወለል በታች ነው፡፡
የመገበያያ ገንዘብ ዋጋው መውደቅም የዋጋ ግሽበት በማስከተሉ የገቢ ንግድ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
በሺህዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት ኪሳራ አጋጥሟቸዋል፡፡ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ህዝቧም ሥራ አጥ ሆኗል፡፡













