የዓለም ሁለተኛዋ ሴት ቢሊየነር 60 ቢሊየን ብር ለገሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማኬንዚ ስኮት የዓለም 2ኛዋ ሴት ቢሊየነር ናት።
የአማዞን ኩባንያ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ ባለቤቱ ማኬንዚ እስከ ዛሬ ለበጎ ተግባር የሚውል 1.7 ቢሊዮን ዶላር ለግሳለች። ይህም በብር ሲሰላ ወደ 60 ቢሊዮን ብር ይጠጋል።
ማኬንዚ ይህን አዱኛዋን የለገሰችው በዋናነት የጥቁሮች ኮሌጅ ለሚባሉት የትምህርት ተቋማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚሰሩ ድርጅቶች እንዲሁም ለጤና ተቋማት ነው።
ማኬንዚ ይህንን ድምር የልግስና አሐዝ ይፋ ያደረገችው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሲሆን 'ቤዞስ' የሚለውን የቤተሰብ መጠርያዋ ሆኖ የቆየውን ስም ማስቀየሯን በዚሁ አጋጣሚ ይፋ አድርጋለች።
ማኬንዚ ከዓለም ቁጥር አንዱ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ጋር ሰማንያቸውን የቀደዱት ባለፈው ዓመት ነበር።
ፎርብስ እንደሚለው የማኬንዚ አዱኛ ሲሰፈር አሁን 62 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። ይህም በዓለም እጅግ የናጠጠች ሁለተኛዋ ሴት ሀብታም ያደርጋታል።
የልቦለድ ጸሐፊዋ ማኬንዚ ቤዞስን ያገባችው አማዞንን ከመመስረቱ አንድ ዓመት በፊት ነበር።
ያኔ በአማዞን ከተቀጠሩ የመጀመርያዎቹ ሠራተኞች አንዷ ናት። ፍቺ ስትፈጽም ታዲያ የድርጅቱ 4 ከመቶ ንብረት ይገባታል ስለተባለ ይህንኑ አዱኛ ወስዳለች።
ማኬንዚ ከቤዞስ ጋር ፍቺ ከፈጸመች በኋላ የመጀመርያ ተግባሯ ያደረገችው የልግስና ቅጽ መሙላት ነበር። በዓለም እጅግ የናጠጡት ዋረን በፌትና የቀድሞው የማይክሮሶፍት አለቃ ቢል ጌትስ ከባለቤቱ ሜሊንዳ ጋር በመሰረቱት የበጎ አድራጎት ድርጅት ቢሊዮኖችን ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር። ይህንኑ እየፈጸመች ነው ዛሬ።
የቢልጌትስና ሜሊንዳ ድርጅት ባለጸጎች አብዛኛውን ድርሻቸውን ለበጎ ሥራ እንዲያውሉ ለማበረታት የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ማኬንዚ ይህን ዓመት በታላቅ ሐዘንና ልብ መሰበር እንዳሰለፈች የገለጸች ሲሆን ይህም የኮሮናቫይረስ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ አብራርታለች። ችግሩን ለመቅረፍና ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግም እርዳታ እንደምታደርግ ተናግራለች።
በሽታው በድሀና ሀብታም እንዲሁም በጥቁርና ነጭ መሀል ያለውን ልዩነት ያጋለጠ ነበር ያለችው ማኬንዚ የዘር ልዩነትን ለማጥበብ ለሚሰሩ ተግባራት ብቻ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር መለገሷን ገልጻለች።
በታሪክ የጥቁሮች ኮሌጅ ተብሎ ለሚጠራው ተስክጊ ዩኒቨርስቲ 20 ሚሊዮን ዶላር መለገሷና ይህም በኮሌጁ ታሪክ ትልቁ ልግስና መሆኑን የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ሊሊ ማክኔይር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ የግብረሰናይ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር ብራይን ሚተንዶርፍ የማኬንዚ እርዳታ ከባለጸጎች ሁሉ ይለያል ይላሉ።
"አንዳንድ ልግስናዎች ለሰጪው ገጽታ ግንባታ የሚውሉ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የምርም ለውጥ ለማምጣት የሚሰጡ ናቸው። የማኬንዚ ከሁለተኛው ይመደባል" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
የማኬንዚ እርዳታ በተለይ አሁን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ባጋጠማቸው ጊዜ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል ፕሮፌሰር ብራየን።














