ማልታ ከባሕር ላይ የታደገቻቸው 65 ስደተኞች ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

ማልታ ስደተኞችን የምትታደገው ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የማልታ የጠረፍ ጠባቂዎች ከሜዲትራንያን ባሕር ላይ ከታደጓቸው 94 ስደተኞች መካከል ሁለት ሦስተኛዎቹ በኮቪድ-19 የተያዙ መሆናቸው ተገለፀ።

ለስደተኞቹ ምርመራ የተደረገው እንደደረሱ ሲሆን 65 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

ከስደተኞቹ መካከል ሃያዎቹ ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥ ዘጠኙ ደግሞ ውጤታቸውን ገና አልተቀበሉም ተብሏል።

ስደተኞቹ ከኤርትራ፣ ሞሮኮ እና ሱዳን የሄዱ መሆናቸው ሲገለፅ፣ በማልታ የድንበር ጠባቂዎች እይታ ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ባሕር ላይ ለ30 ሰዓታት መቆታቸው ተገልጿል።

ስደተኞቹ በለይቶ ማከሚያ ውስጥ እንደሚቆዩም ታውቋል።

"በጀልባ ማልታ የደረሱት ስደተኞች ወዲያውኑ ለ14 ቀን ያህል ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አድርገናል። ቫይረሱ የተገኘባቸው ተለይተው እንዲቀመጡ ሲደረግ ቀሪዎቹ ደግሞ ክትትል ይደረግላቸዋል" ያሉት የማልታ ጤና ሚኒስትር ናቸው።

94 የስደተኞች ቡድን ከሊቢያ በአነስተኛ ጀልባ መነሳቱ ተገልጿል። ስደተኞቹ በድንበር ጠባቂዎቹ የተገኙት የመዛልና የተሰፋ መቁረጥ ምልክት ካሳዩ በኋላ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

ከባህር ላይ የተገኙት ስደተኞች በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሰራተኞች እየተመዘገቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

"ቡድኑ ማልታ የደረሰው በጋራ ሲሆን ከመመርመራቸው በፊት ከጥቂት ሰዎች ጋር ብቻ ግንኙነት ነበራቸው" ያሉት ሚኒስትሩ የአካባቢው ሰዎች በዚህ የተነሳ በኮቪድ-19 ሊጋለጡ ይችላሉ የሚለውን ስጋት ውድቅ አድርገዋል።

እንደ ፈረንሳይ የዜና ወኪል ከሆነ እነዚህ ስደተኞችን ጨምሮ በማልታ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 99 ብቻ ናቸው።

በዚህች አነስተኛ ደሴት ኮቪድ-19 የተያዘ የመጀመሪያው ሰው የተገኘው በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሲሆን እንዲህ ቁጥሩ በዛ ያለ ሰው በአንድ ጊዜ በቫይረሱ መያዙ ሲታወቅ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

በማልታ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነው።

ቫይረሱ በአውሮፓ ሲሰራጭ 450 000 ነዋሪ ያላት ይህች ደሴት ድንበሮቿን ሙሉ በሙሉ ዘግታ ስደተኞች የመታደግ ሥራዋንም ሙሉ በሙሉ አቋርጣ ቆይታ ነበር።

ኮሮና
Banner