የአማዞን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለቤት አልባ ድሆች 2 ቢሊየን ዶላር ሊለግሱ ነው

ጄፍ ቤዞስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአማዞን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ ባቋቋሙት የግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኘነት ቤት ለሌላቸው ድሆች መኖሪያ ቤት ለመስራት እና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት 2 ቢሊየን ዶላር (55 ቢሊየን ብር ገደማ) ፈሰስ ሊያደርጉ ነው።

ባለጸጋው እቅዳቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ይፍ ባደረጉበት ወቅት፤ የግብረ ሰናይ ድረጅቱ ስም 'ደይ ዋን ፈንድ' ይባላል ብለዋል።

164 ቢሊየን የሚገመት ሃብት እንዳለቸው የሚነገርላቸው ቤዞስ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ አይሳተፉም እየተባሉ ይወቀሱ ነበር።

ቤንዞስ እአአ 1994 የመሰረቱት አማዞን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ ከሚገኙ በአክሲዮን ድርሻ ከተቋቋሙ ኩባንያዎች መካከል ከአፕል በመቀጠል 1 ትሪሊየን ዶላር የሚያወጣ ኩባንያ ለመሆን ችሏል።

ምንም እንኳ የአማዞኑ መስራች 2 ቢሊየን ዶላር ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለማዋል ቢያስቡም፤ በርካቶች ግን ከቢል ጌትስ እና ከማርክ ዙከርበርግ ጋር በማነጻጻር ሁለት ቢዮን ዶላሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም እያሉ ነው።

ከማይከሮሶፍት መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ቢል ጌትስ በራሳቸው እና ባለቤተቸው ስም በተቋቋመው ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት ከ10 ቢዮን ዶላር በላይ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ፈሰሰ አድረገዋል። የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ከማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያተርፈውን 99 በመቶ ያክሉን ለበጎ ሥራዎች ላይ እንደሚያውል ቃል ግበቷል።

የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባለቤት የሆኑት የአማዞን መስራቹ ቤዞስ 'ብሉ ኦሪጅን' በተሰኝ የህዋ ፕሮጀክት ላይ እየሰሩ ይገናሉ።