ፌስቡክና ትዊተር ፕሬዝደንት ትራምፕ ላይ እርምጃ ወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፌስቡክና ትዊተር፤ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የቅስቀሳ ቡድናቸው ተገቢ ያልሆነ መረጃ አስተላልፈዋል በሚል እርምጃ ወስደውባቸዋል።
ፌስቡክ የፕሬዝደንቱ መልዕክቱ ጎጂ የኮቪድ-19 መረጃ ይዟል በሚል ከመድረኩ ላይ እንዲወገድ አድርጓል። ትዊተር ደግሞ የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የለጠፈውን መልዕክት እስኪያወርድ ድረስ አግዶታል።
ትራምፕ ፎክስ ኒውስ ከተሰኘው ጣብያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ላይ 'ሕፃናት ኮሮናቫይረስ አይዛቸውም' ያሉበትን ምስል በማጋራታቸው ነው እርምጃ የተወሰደባቸው።
የአሜሪካ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም ሕፃናት ለኮሮናቫይረስ ይጋለጣሉ ይላል።
የፌስቡክ ቃል-አቀባይ 'ምስሉ ስለ ኮቪድ-19 ሃሰተኛ የሆነ መረጃ ይዟል፤ ይህ ደግሞ ስለ ኮቪድ-19 ያለንን ፖሊሲ የሚጥስ ነው' ብለዋል።
ፌስቡክ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ስለ ኮሮናቫይረስ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል በማለት እርምጃ ሲወስድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሁን እንጂ በሌላ ይዘት እርምጃ ወስዶባቸዋል ያውቃል።
በመቀጠል ፕሬዝደንቱ ላይ እርምጃ የወሰደው ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር-አምባ ነው። ትዊተርም በተመሳሳይ ዶናልድ ትራምፕ የተሳሳተ መረጃ ያዘለ መረጃ አጋርተዋል በማለት ገፃቸው ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ አድርጎ ነበር።
የትዊተር ቃል አቀባይ፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ኮቪድ-19ኝን በተመለከተ የኩባንያውን ፖሊሲ ጥሰዋል ብለዋል።
"የገፁ ባለቤት ያጋሩትን መረጃ ከገፃቸው ላይ እስካልወገዱ ድረስ 'ትዊት' ማድረግ አይችሉም" ብለዋል ቃል-አቀባዩ።
ፕሬዝደንቱ ከዚህ በኋላ ያጋሩትን መረጃ እንዳስወሰገዱ መረዳት ተችሏል።
ትዊተር ከጥቂት ሳምንታት በፊት የዶናልድ ትራምፕ፤ ልጅ ትራምፕ ትንሹ ሃይድሮክሲክሎሮክዊን ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል የሚል መረጃ ማጋራቱን ተከትሎ ገፁ ለተወሰነ ሰዓታት እንዲዘጋ ማድረጉ አይዘነጋም።
ባለፈው መጋቢት ቢሊየነሩ ኢላን ማስክ 'ሕፃናት ኮሮናቫይረስን ይመክታሉ' የሚል መልዕክት የትዊተር ግድግዳው ላይ ቢለጥፍም ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደበትም።
ፎክስ ኤንድ ፍሬንድስ ለተሰኘው ፕሮግራም በቴሌፎን ቃላቸውን የሰጡት ትራምፕ ትምህርት ቤቶች በመላው ሃገሪቱ መከፈት አለባቸው ሲሉ ሞግተዋል። ለዚህ ሃሳባቸው ማስረገጫ እንዲሆናቸው ነው ሕፃናት ኮሮናቫይረስ አይዛቸውም ያሉት።
ባለሙያዎች ሕፃናት በኮሮናቫይረስ እንደሚያዙና ለሌሎችም እንደሚያስተላልፉ ይናገራሉ። ነገር ግን በበሽታው ክፉኛ የመታመማቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው። ይልቁንስ ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች ቫይረሱ የጠና ሕመም ሊያመጣባቸው እንደሚችልና ለሞትም እንደሚዳርጋቸው ያስረዳሉ።




















