ትራምፕ ከፌስቡክ፣ ትዊተርና ጉግል ጋር ጦርነት ገጥመዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከማሕበራዊ ድር አምባዎቹ ከፌስቡክና ትዊተር እንዲሁም ጉግል ጋር ጦርነት ገጥመዋል። ስለኔ ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ እያቀረቡ አይደለም በማለትም እየከሰሷቸው ይገኛሉ።
ትራምፕን በተመለከተ ዜና ብለው ለሚፈልጉ ሰዎች የተዛባ መረጃ እያቀረበ ነው ያሉትን ጉግል «ቢጠነቀቅ ይሻላል» ሲሉ ዛቻ ሰንዝረዋል።
«አስተዳደሬ መሰል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ወደኋላ አይልም» ሲሉም ተደምጠዋል።
የጉግል ሰዎች በበኩላቸው የመፈለጊያ ዘዴዎቻችን ከማንኛውም የፖለቲካ አጀንዳ የፀዱ እና ሚዛናዊ ናቸው ሲሉ የአፀፋ ምላሽ ሰጥተዋል።
ለመገናኛ ብዙሃን ቃላቸውን የሰጡት ትራምፕ «ጉግል ሰዎችን መጠቀሚያ እያደረገ ነው፤ ይህን ጉዳይ አቅልለን የምናየውም አይደል» ብለዋል።
አክለውም ትዊተር እና ፌስቡክ የተባሉት የማሕበራዊ ድር አምባዎችም «ቢጠነነቁ ነው የሚሻላቸው» የሚል ማስፈራሪያ ጣል አድርገዋል።
«በርካታ ሺህ ቅሬታዎች እየዘነቡ ነው፤ በሰዎች ላይ ይህን ማድረግም ተገቢ አይደለም» የትራምፕ ሃሳብ ነው።
ሰውየው ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ግን ፍንጭ አልሰጡም።
የፕሬዝደንቱ ምጣኔ ሃብት አማካሪ የሆኑ ግለሰብ ግን «ጉግል ላይ ምርመራ እያካሄድን ነው፤ አስፈላጊውን እርምጃም እንወስዳለን» የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በዘርፉ ጥርስ የነቀሉ ተንታኞች ግን የትራምፕ ክስ ውሃ አያነሳም ይላሉ፤ ማስረጃ ለማቅረብ እንደሚከብዳቸውም ያስረዳሉ።












