ከኮሮናቫይረስ በእጅጉ እያተረፉ ያሉት ትልልቅ ድርጅቶች

ኩባንያ

የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO

የምስሉ መግለጫ, ኩባንያ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የበርካታ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና እያደረሰ ቢሆንም ትልልቅ የሚባሉት የዓለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን ጥሩ የሚባል ትርፍ እየሰበሰቡ ነው።

በበይነ መረብ አማካይነት የተለያዩ አይት መገልገያዎችን የሚሸጠው አማዞን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማግስት ባሉት ሶስት ወራት ብቻ ሽያጩ 40 በመቶ ከፍ እንዳለለት ያስታወቀ ሲሆን ታዋቂው የስልክና የላፕቶፕ አምራች አፕል ደግሞ የአይፎንና ሌሎች መቀየሪያ መሳሪያዎች በደንብ እንደተቸበቸቡለት ገልጿል።

ፌስቡክ ደግሞ በስሬ በማስተዳድራቸው እንደ ዋትስአፕና ኢንስታግራም ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተጠቃሚዎች ቁጥር 15 በመቶ ከፍ ብሎልኛል ብሏል።

የአማዞን የሩብ ዓመት ትርፍ 5.2 ቢሊየን ዶላር ሲሆን ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ ይህ ከፍተኛው ነው ተብሏል። ድርጅቱ እንደውም ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ ለሰራተⶉቹ መከላከያ መሳሪያዎችን ለመግዛትና የመከላከያ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱ ትርፉን ዝቅ ያደርገዋል ተብሎ ተፈርቶ ነበር።

በአጠቃላይ በበይነ መረብ የሚካሄዱ ንግዶች የሽያጭ መጠኑ 40 በመቶ ከፍ ብሏል። እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ባሉት ሶስት ወራት ደግሞ በአጠቃላይ 88.9 ቢሊየን ዶላር አንቀሳቅሷል።

ትርፍም ቢሆን በአስገራሚ ሁኔታ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 2.6 ቢሊየን ዶላር ወደ 5.2 ቢሊየን ዶላር ከፍ ብሏል።

በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜያቸውን ማሳለፋቸውን ተከትሎ የበይነ መረብ ሽያጭ በእጅጉ ተጧጡፏል። አማዞንም ቢሆን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት በሩብ ዓመቱ ብቻ ተጨማሪ 175 ሺ ሰራተኞችን ቀጥሯል።

ፍላጎቱ በዚሁ መቀጠሉ ስለማይቀር በርካታ መጋዘኖችንና ሰራተኞችን ለመጨመርም እያሰበ ነው።

የአፕል የሩብ ዓመት ትርፍ ደግሞ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 11 በመቶ በመጨመር 59.7 ቢሊየን ደርሷል። ሰዎች ስራቸውን ከቤታቸው ሆነው መስራታቸው የተለያዩ መገልገያዎችን እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል።

በዚህም ምክንያት የማክ ላፕቶፖችና አይፓዶች በእጅጉ ተፈላጊ ነበሩ። ሁለቱም የአፕል ምርቶች ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ ገበያቸው እንደደራ ድርጅቱ አስታውቋል።

በዚህም ምክንያት ባለፈው ከነበረው 10 ቢሊየን ዶላር ትርፍ ወደ 11.25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ብሏል።

ፌስቡክ ደግሞ ከኮሮናቫይረስ በኋላ ትርፉ በእጅጉ እንደሚቀንስ ቢጠበቅም እንደውም የ 11 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። አነስተኛ ድርጅቶች ያሏቸው ሰዎች ለማስታወቂያ ወደ ፌስቡክ ላይሄዱ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ተንብየው ነበር።

ነገር ግን ወረርሽኙን ተከትሎ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ በመጨመሩ ምክንያት ለማስታወቂያ የሚመጡ ድርጅቶችም ቁጥር አብሮ ከፍ ብሏል። በዚህም ምክንያት የድርጅቱ የሩብ ዓመት ትርፍ 5.2 ቢሊየን ዶላር እንዲደርስ ሆኗል።

ፌስቡክ እንደሚለው ባለፈው ሰኔ ወር ብቻ በሁሉም የማህበራዊ ሚዲያዎቸ ላይ 2.4 ቢሊየን ተጠቃሚዎች የነበሩ ሲሆን ይህም የ15 በመቶ ጭማሪ አለው።

ከአራቱ ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው አልፋቤትም ቢሆን እንደ ሌሎቹ ባይሆንም ትርፋማ ሆኗል።

ድርጅቱ በስሩ ጉግልና ዩቲዩብን የያዘ ሲሆን እስካሁን ያገኘሁት ትርፍ 38.3 ቢሊየን ዶላር ነው ብሏል። ይህ ደግሞ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሁለት በመቶ ቅናሽ ያሳያል።