ትዊተር ከስድስር ወር በላይ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ገጾችን ሊዘጋ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዊተር ከስድስት ወር በላይ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ገጾችን (አካውንቶችን) ሊያጠፋ ነው። የትዊተር ገጾቹን የከፈቱ ግለሰቦች እስከ ታህሳስ 11 ድረስ ገጻቸውን ካላንቀሳቀሱ ትዊተር አካውንቶቹን እንደሚያጠፋ አስታውቋል።
ከሚሰረዙት መካከል ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ግለሰቦች ገጾች ይገኙበታል። ቤተሰብ ወይም ሌላ የቅርብ ሰው በሟቾች ገጽ ላይ አንቅስቃሴ ካላደረገ፤ አካውንቶቹ ይዘጋሉ።
ትዊተር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ገጾችን ሲያጠፋ የመጀመሪያው ነው።
ተቋሙ እንዳለው፤ ገጻቸውን ከስድስት ወር በላይ ያልጎበኙ ተጠቃሚዎች፤ ድርጅቱ በቅርብ ጊዜ ያስተዋወቀውን የተሻሻለ የደህንነት ጥበቃ ፖሊሲ ስለማያውቁ፤ አካውንታቸው ይዘጋል።
የትዊተር ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ ምንም እንቅስቃሴ የማያደርጉ ተጠቃሚዎችን ገጽ በመዝጋት፤ ለሌሎች ተጠቃሚዎች ያላቸውን ተዓማኒነት ማረጋገጥ ይሻሉ። ከአሜሪካ ውጪ ያሉ ገጾችን ከማጥፋት ተነስተውም በእንቅስቃሴው እንደሚገፉ አስታውቀዋል።
ትዊተር፤ ገጻቸው እንዲዘጋ ለተወሰነባቸው ተጠቃሚዎች ስለጉዳዩ ኢሜል መላኩን ገልጿል። ምን ያህል ገጽ እንደሚዘጋ በይፋ ባይገለጽም፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አካውንቶች እንደሚሰረዙ ተገምቷል።
በቀጣይ፤ ገጽ ከፍተው ምንም እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎችን አካውንት ወደመዝጋት የመሸጋገር እቅድም ተይዟል።
ትዊተር በቅርቡ ያወጣው መረጃ፤ ቋሚ እለታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ 145 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት። የአካውንቶች መዘጋት በዚ ቁጥር ላይ ለውጥ እንደማያመጣም ተገልጿል።
ተቋሙ እንዳለው፤ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ገጾችን በመዝጋት፤ ትዊተር ሰዎች የሚያምኑት የመረጃ መለዋወጫ መድረክ መሆኑን ማስረገጥ ግባቸው ነው። እንቅስቃሴ አልባ ገጾችን በመዝጋት፤ ሌሎች የትዊተር ተጠቃሚዎች መረጃ እንዲለጥፉ ለማበረታታም ወጥነዋል።












