ጃክ ማ እና ጃክ ዶርሲ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ምክንያት ምን ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ጃክ ማ በአንድነት ፓርክ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከጃክ ማ ጋር በአንድነት ፓርክ ውስጥ

ሁለቱ ጃኮች በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝተዋል። የአሊባባው ጃክ ማ እና የትዊተሩ ጃክ ዶርሲ።

የቻይናው አሊባባ የኤክትሮኒክስ መገበያያ ድርጅት እስያ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ግዙፍ ድርጅት ነው። ትዊተር ደግሞ በአራት አሜሪካዊያን ወጣቶች የተመሠረተ ግዙፍ የማሕበራዊ ትስስር መድረክ ነው።

ጃክ ማ እና ጃክ ዶርሲ ቀጠሮ እንዳላቸው ወርሃ ኅዳር አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ተገኝተው የመገናኛ ብዙኀን ትኩረት አግኝተዋል።

ቻይናዊው ጉምቱ የቢዝነስ ሰው ጃክ ማ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር መክረዋል። አልፎም በአይሲቲ ፓርክ የተገኙት ጃካ ማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር በመሆን 'ኤሌክትሮኒክ ዎርልድ ትሬድ ፎረም' [ኢደብልዩቲፒ] የተሰኘ ፕሮጀክትን መርቀዋል።

ፕሮጀክቱ በዓለም ዙሪያ ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እና መገበያየት ለሚፈልጉ አነስተኛ የንግድ ተቋማት አመቺ ዕድል ይፈጥራል ተብሎለታል።

በሌላ በኩል የትዊተር አጋር መሥራች የሆነው ወጣቱ ጃክ ዶርሲ ዓላማው ከናይጄሪያና ከኢትዮጵያ በአንዱ አገር ከሦስት እስከ ስድስት ወራት በመቆየት የኢንቨስትመንት አማራጩን ማየት ነው።

ለምን ኢትዮጵያ?

የፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ሊቀ መንበር የሆኑት ዘመዴነህ ንጋቱ እኒህ የቴክኖሎጂ ባላባቶች ኢትዮጵያን የመረጡበት ዋነኛው ምክንያት የሕዝብ ብዛት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምጣኔ ሃብቷ ከጊዜ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ነው ይላሉ።

«ከሰሃራ በታች ካሉ ኢኮኖሚዎች ኢትዮጵያ በጂዲፒ [በአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት] ሦስተኛ ነች። የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ በምርትም ሆነ በመሠረተ ልማት ዝርጋት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ኢትዮጵያ ትኩረት እየሳበች ነው።»

አክለውም «እነዚህ ሁለት ጃኮች ይህንን ተገንዝበው ነው የመጡት። በተለይ የአሊባባ ጃክ ማ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ግብዣ ነው የመጡት። አሊባባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ800 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችል አንድ መድረክ ነው» ብለዋል።

አሊባባ የተሰኘው ኩባንያ 'አሊፔይ' የሚባል የመገበያያ መንገድ አለው። አቶ ዘመዴነህ ይህን የመገበያያ መንገድ እንደትልቅ አማራጭ ያዩታል።

ስቴምፓወር የተሰኘውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ላይ የተሠማራ ድርጅት ዋና የቴክኖሎጂ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ኢዮኤል ኃይሌም 'አሊፔይ' ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መምጣቱ ትልቅ እመርታ ነው ይላሉ።

«የእነዚህ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቁ ጥቅም የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው። እኛ አገር ለምሳሌ የኢ-ኮሜርስ ሰርቪስ ገና ዳዴ እያለ ነው። ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ኢ-ኮሜርስ በጣም ብዙ የሰው ኃይልን መያዝ የሚቻልበት ዘርፍ ነው። ለምሳሌ እንደኛ ዓይነት ድርጅቶች ከእነ አሊባባ ልምድ መቅሰም ይችላሉ። የቴክኖሎጂ ባሕል ወደሃገራችን መግባቱ ትልቅ ጥቅም ነው።»

የጃክ ማ አሊባባና የኢትዮጵያ መንግሥት በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል ለመገንባት የፊርማ ስምምነት አድርገዋል።

አቶ ዘመዴነህ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም እነዚህን የሚመስሉ የግዙፍ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እምብዛም አይስተዋልም ይላሉ።

«ብዙ ጊዜ ሩዋንዳ ነው የሚሄዱት፤ ነገር ግን ሩዋንዳ ትንሽ ሃገር ነች። ኢትዮጵያ ግን ግዙፍ ናት። ይሄ ትልቅ አማራጭ ነው። ለምሳሌ ትዊተር በጣም ግዙፍ ሶሻል ሚድያ መድረክ ነው» በማለት የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ይጠቅሳሉ።

«ጃክ ዶርሲ በግልም ይሁን በኩባንያ ደረጃ ኢንቨስት የማድረግ ሃሳብ አለው የሚል አዝማሚያ አለ እንደምንሰማው። ቀደም ሲል በዚህ በኩል ፍላጎት የያሳዩ የነበሩት ከምሥራቅ የሚመጡ ናቸው። በተለይ ባለፈው አንደ ዓመት ተኩል ግን ከምዕራቡ ዓለም ትልቅ ፍላጎት እየታየ ነው» ሲሉ የትዊተርን መምጣት ያነሳሉ።

እንደ አቶ ዘመዴነህ ትንተና እነዚህ ግዙፍ ድርጀቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በቴክኖሎጂ ብቻ ኢንቨስት ለማድረግ አይደለም፤ በሌሎችም የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው።

«አውነት ለመናገር ሌላኛው ትኩረት ሳቢ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል ሽልማት ነው። ለምሳሌ እኔ በተሰማራሁበት የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። ለኢትዮጵያ 'ብራንዲንግም' [ገጽታ] ሽልማቱ ከፍተኛ ትርጉም አለው» በማለት ይናገራሉ።

የአፍሮ ኤፍኤም፣ የቃና ቴሌቪዥና እና 251 ኮሚዩኒኬሽንስ መሥራች የሆነው አዲስ አለማየሁ «ሁለት ቢሊየነሮች መጡ ማለት እኮ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ከካርታው ላይ አትፋቅም ማለት ነው» በማለት ጉብኝቶቹ ጠቃሚ ቦታ ለአገሪቱ እንደሚያስገኙላት ይገልጻል።

«ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል ቢሊየነሮች አገሩን ልይ ብለው ሲመጡ። ይህ ማለት አገራችን ከዚህ በኋላ ከቴክኖሎጂው ዓለም ርቃ የምትኖር አትሆንም» በማለት በዘርፉ ብዙ እምቅ ተሰጥዖ መኖሩን ጠቅሶ «በዚህ በኩል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሚሆን በጣም ብዙ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች አሉን። እነዚህ ወጣቶች አሁን ተሻግረው ማየት ይጀምራሉ ማለት ነው። እነዚህ ሁለቱ መጡ ማለት ሌሎችም መከተላቸው አይቀርም።»

ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለውጥ በር ከፍቷል ይላል አዲስ፤ «ኢኮኖሚው እየተከፈተ ነው። አዳዲስ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ሊገቡ ነው። ኢንተርኔት ላይ ያለው ጭንቅንቅ የዛሬ ስድስት ወር፤ አንድ ዓመት ይቀረፋል ብዬ አምናለሁ። ሌላኛው ምክንያት 110 ሚሊዮን ሕዝብ ነው ያለን። አማካይ ዕድሜ 18 ዓመት ነው። የኢኮኖሚውም ዕድገት በጣም ፈጣን ነው።»

ጃክ ዶርሲ

የፎቶው ባለመብት, JACK DORSEY TWITTER

የምስሉ መግለጫ, ጃክ ዶርሲ

የቴክ ባላባቶቹ ከመንግሥት ምን ይሻሉ?

«አሊባባ ኢትዮጵያ ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን አኔ 'ሴልስማን' [ሽያጭ ሠራተኛ] ሆኜ፤ ማኔጀርም ሆኜ አገለግላለሁ» ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለጃክ ማ ያሰሙት ንግግር ነበር።

አቶ ዘመዴነህም ይህንን ንግግር ያወሳሉ። «መንግሥት ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን በብዙ ጥረት የሚመጣው ኢንቨስተር ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ስለሚገባ እሳቸው [ጠ/ሚ ዐብይ] ያሉት እውነታቸውን ነው። እነ አሊባባና ትዊተር ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ስኬታማ ከሆኑ ውጤቱ ለአገራችን 'ብራንድ አምባሳደር' [የመልካም ገጽታ] ይሆኑናል።»

ነገር ግን ከዚህ አንጻር የተጀመረውን መልካም ሂደት ለማስቀጠል አቶ ዘመዴነህም ሆኑ አዲስ የፖሊሲ ለውጥ እንደሚያሻ ይስማማሉ።

«መንግሥት የጀመረውን የለውጥ አጀንዳ መጨረስ አለበት። ለወጣቱ፤ በተለይ ደግሞ ለጀማሪ ኢንቨስተሮች ልዩ የሆነ ፖሊሲ መውጣት አለበት። አንድ ወጣት ሥራ ልሥራ ቢል ያለው ፈተና፤ ኩባንያውን ከማስመዝብ ጀምሮ እስከሚከፍለው ታክስ ድረስ እጅግ ከባድ ነው» የሚለው አዲስ ነው።

አቶ ዘመዴነህም ቢሆን የፖሊሲ ለውጥ በአስቸኳይ መደረግ አለበት ከሚሉት ወገን ናቸው።

«እርግጥ ነው ለአገር የሚጠቅም መሆን አለበት፤ ግን ደግሞ ኢንቨስተሮች እንዳይሸሹ የሚያደርግ ፖሊሲ ያሻል። ለምሳሌ የሞባይል ክፍያ አገልግሎት ከፋይናንስ ዘርፉ ጋር የተገናኘ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ሕጎች አሉ የውጭ ድርጅቶችን ከመሳተፍ የሚያግዱ። እነዚህ ፖሊሲዎች እንደገና መቃኘት አለባቸው።»

ለአቶ እዮኤል ግን ዋናው ጉዳይ ለቴክኖሎጂ ያለው አመለካከትና የውጪ ምንዛሪ [ዶላር] ነው።

«ያልተነካ ትለቅ ገበያ አለ። ነገር ግን ዲጂታል ማርኬቲንግ ምንድነው? ወይም ኢ-ኮሜርስ ምንድነው? ከቤተህ ቁጭ ብለህ እንዴት ትሸጣለህ? እነዚህ ሃሳቦች ብዙ አይታወቁም» ይላል እዮኤል።

ይህንን በምሳሌ ሲያስረዳም ኢትዮጵያ 'ሞባይል ባንኪንግ' ብዙ ተጠቃሚ ያለው ሶማሌ ክልል ውስጥ መሆኑና በቀን ውስጥም የብዙ ሚሊዮን ብር ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቅሶ ለዚህም የቴክኖሎጂው መኖር ያለውን ጠቀሜታ ይናገራል።

እዮኤል ከዚህ አንጻር የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ሲናገር «አብዛኛው ሰው የሚገበያየው በደረቅ ኖት ነው። ኤቲኤም እንኳ በአግባቡ እየተጠቀምን አይደለም። ሌላውም ቦታ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል የምንለው ለዚህ ነው።»

በተጨማሪ ደግሞ ዶላር እንዴት ማነቆ ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዳ «እኔ ኢትዮጵያ ሆኜ ከእንግሊዝ ወይም ከአሜሪካ አንድ ዕቃ መግዛት ብፈልግ አገሪቱ በቂ የሆነ 'ሃርድ ከረንሲ' [የውጭ ምንዛሪ] አላት ወይ? ምክንያቱም እኔ ከዚህ ለኢትዮጵያ መንግሥት የምከፍለው ብር ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሚከፍልልኝ ዶላር ነው። በቂ ዶላር አለን ወይ ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳም አሊባባ በራሳቸው የመገበያያ መንገድ ይህንን ችግር ሊፈቱት ይችላሉ» ሲል ይናገራል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የቻይና ሀብታሙ ሰው ጃክ ማ ድርጅቱ ባዘጋጀው ድግስ ላይ እንደ ማይክል ጃክሰን አጊጦ መጥቷል

የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥን በተመለከተም አቶ እዮኤል «አፍሪካ ውስጥ ትልቅ የፋይበር ገመድ ከተዘረጋባቸው አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ነች። በእርግጥም የኢንተርኔት መቆራረጥ አለ። ነገር ግን ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ሊገቡ ነው» የሚባለው ችግሩን እንደሚቀርፉት ያምናል።

የእነዚህ ኩብንያዎች መግባትም አሊባባን ለመሳሰሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ሌላ ተጫማሪ አማራጭ እንደሚሆኑ ጠቅሶ «በእኔ ምልከታ ቴሌኮም በሞኖፖሊ የተያዘ ስለሆነና ፉክክር ስለሌበት ነው መቆራረጡ የሚያጋጥመው። እነዚህ ኩባንያዎች ግዙፍ ናቸው። የራሳቸውን 'ቪሳት' ተክለውም ቢሆን መጠቀም ይችላሉና ኢንትርኔት ብዙ ፈተና ይሆናል ብዬ አልጠበቅም» ይላል።

የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ በጀት 386.9 ቢሊዮን ብር ነው። የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ የተጣራ ገቢ ደግሞ 4.2 ቢሊየን ዶላር [አሁን ባለው የምንዛሪ ገበያ ቢያንስ 126 ቢሊየን ብር ገደማ ነው]፣ የጃክ ማ የተጣራ ገቢ ደግሞ 36.6 ቢሊየን ዶላር [ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ] ነው።

አዲስም ሆነ አቶ ዘመዴነህ፤ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ እዩኤል እነዚህ የናጠጡ ቢሊየነሮች ያላቸው አቅም በጣም ግዙፍ እንደሆነ ይስማማሉ። ጥያቄው ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሰዎች ለመጠቀም ምን ያህል ዝግጁ ናት? የሚለው ነው።