ቻይናዊው ቢሊየነር ጃክ ማ በአዲስ አበባ

ጃክ ማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ

ቻይናዊው ጉምቱ የቢዝነስ ሰው ጃክ ማ አዲስ አበባ ገብተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር መክረዋል።

አሊባባ የተሰኘው ግዙፉ የቻይና 'ኦንላይን' መገበያያ መድረክ አጋር መሥራች የሆኑት ጃክ ማ ትላንት ምሽት ነው ለሁለት ቀናት ጉብኝት ኢትዮጵያ የገቡት።

አይሲቲ ፓርክ የተገኙት ጃካ ማ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር በመሆን 'ኤሌክትሮኒክ ዎርልድ ትሬድ ፎረም' [ኢደብልዩቲፒ] የተሰኘ ፕሮጀክት መርቀዋል።

ፕሮጀክቱ በዓለም ዙሪያ ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እና መገበያየት ለሚፈልጉ አነስተኛ ቢዝነሶች ዕድል ይሰጣል ተብሎለታል።

ኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሚዪኒኬሽን ቴክኖሎጂ [አይሲቲ] የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲሆን ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች።

አይሲቲ ፓርክም የተገነባው ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እንደሆነ መንግሥት ይናገራል።

ባለፈው ሚያዚያ ቻይና አቅንተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ሃንግዡ የሚገኘውን የአሊባባ ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘታቸው አይዘነጋም።

የጃክ ማ አሊባባና የኢትዮጵያ መንግሥት በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል ለመገንባት የፊርማ ስምምነት አድርገዋል።

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያዊያን ምርቶች በቻይና እና በቻይና ጎረቤት ሃገራት ገበያዎች ላይ እንዲተዋወቁ ይደረጋል።

ቻይናዊው የቢዝነስ ሰው ጃክ ማ በ33 ዓመታቸው ነው የመጀመሪያ ኮምፒውተራቸውን ገዝተው ወደ 'ኦንላይን' ወይም በይነመረብ ቢዝነስ የገቡት።

በግሪጎሪያዊያን አቆጣጠር 2017 ላይ ፎርብስ የተሰኘው መፅሔት ባወጣው መረጃ መሠረት ጃክ ማ 36.6 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው።

አሊባባ በተሰኘው እጅግ ግዙፍ 'ኦንላይን' መገበያያ ላይ ያላቸው 9 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ 420 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

ባለፈው ሳምንት ናይጄሪያ የነበሩት የትዊተር አጋር መሥራችና ዋና ኃላፊ የሆኑት ጃክ ዶርዚ ለቀናት ጉብኝት ኢትዮጵያ ገብተዋል።