ማይክሮሶፍት በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል አለ

ቶክዮ ውስጥ ሠራተኞች እረፍት ሲወስዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቶክዮ ውስጥ ሠራተኞች እረፍት ሲወስዱ

የጃፓኑ የማይክሮሶፍት ቅርንጫፍ ሠራተኞቹ በሳምት አራት ቀን ብቻ እንዲሠሩ ማድረጉን ተከትሎ ሽያጭ በ40 በመቶ ማደጉን ይፋ አድርጓል።

ሠራተኞች ከወርሀዊ ደሞዛቸው ሳይቀነስባቸው በሳምት አራት ቀን ብቻ ቢሠሩ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ለማወቅ ጥናት እየሠራ የነበረው ማይክሮሶፍት፤ ተቀጣሪዎቹ በየሳምንቱ አርብ ቢሮ እንዳይገቡ አድርጎ ነበር።

ድርጅቱ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞቹን ደሞዝ እየከፈላቸው እረፍት እንዲወስዱም ውሳኔ አሳልፏል። ከዚህ በተጨማሪም ስብሰባ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንዲካሄድ፣ ፊት ለፊት ተገናኝቶ ከመወያየት ይልቅ በድረ ገጽ መነጋገር እንዲዘወተርም አድርጓል።

ጃፓን በረዥም የሥራ ሰዓት ከሚታወቁ አገሮች አንዷ ናት።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2017 ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ከጃፓን ተቋሞች አንድ አራተኛው ሠራተኞቻቸውን በወር ከ80 ሰዓት በላይ ያለ ተጨማሪ ክፍያ ያሠራሉ።

ማይክሮሶፍት ዘንድሮ የሠራው ጥናት፤ 92 በመቶ ያህል ተቀጣሪዎቹን ያሳተፈ ነበር።

ድርጅቱ እንዳለው፤ ጥናቱ ሲካሄድ፤ የኤሌክትሪክ ፍጆታ 23 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ የወረቀት ህትመት ደግሞ 59 በመቶ አሽቆልቁሏል።

ማይክሮሶፍት በቀጣይ ሠራተኞቹ በአግባቡ እረፍት የሚወስዱበት አሠራር የመዘርጋት እቅድ አለው።

ከዚህ በተቃራኒው፤ የእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ ያሠራው ጥናት በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራት አዋጭ እንዳልሆነ ያሳያል።

የድረ ገጽ መገበያያ አሊባባን የመሰረተው ጃክ ማ፤ "996" የተባለ አሠራር መዘርጋቱ ይታወሳል። ሠራተኞች በቀን ለ12 ሰዓት፣ ለስድስት ቀናት ይሠራሉ።