በአማዞን ሥራ ቀጣሪና አባራሪ እየሆነ የመጣው ሮቦት

የአማዞን የስራ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኮምፒውተር የቀን በቀን ሥራዎትን ሲከታተል ምን ይሰማዎታል?

ሮቦቶች የሰዎችን ሥራ ይነጥቃሉ ተብሎ መወራት ከጀመረ ከራረመ። አሁን ተራ ወዛደር ብቻ ሳእሆን የሰው ኃእል አስተዳደር ሆኖም መግቢኣ መውጫ ሰዓትን ይቆጣጠራል፤ በሥራ ላይ ያለዎትን አፈፃፀም ይከታተላል። ይሾማል ይሸልማል፤ ካልሆነ ያባርራል።

ይህ ጉዳይ ተግባራዊ ጉዳዩ መገናኛ ብዙኃን ጆሮ የደረሰው ደግሞ አማዞን ውስጥ ነው። ግዙፉ የአማዞን ድርጅት ውስጥ ካሰቡት በተለየ ሁኔታ ሠራተኞችን በማባረር የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ውሏል ይላል ዘገባው።

ዘ ቨርጅ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ዘጋቢ እንዳስነበበው አማዞን ውስጥ ኮምፒውተሮች የሰራተኞችን ውጤታማነት እየመዘኑ እስከማባረር ደርሰዋል።

አማዞን በዝቅተኛ ክፍያና ከባድ የስራ ጫና ምክንያት በተደጋጋሚ ከሠራተኞች ቅሬታ የቀረበበት ሲሆን አንድ ሠራተኛ ድርጅቱ የሚመለከተን እንደ "ሮቦት" ነው ሲል ምሬቱን ገልጿል።

ዘ ቨርጅ እንደዘገበው ብዙ ሠራተኞች በየዓመቱ እቃዎችን በፍጥነት ማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ከሥራቸው ይባረራሉ።

ይህ ሁኔታ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰዎች አለቃ እየሆነ እንደመጣ ያሳያል የሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ። ቴክኖሎጂው የሰዎችን ውጤታማነት ተከታትሎና መዝኖ ማስጠንቀቂያ መስጠት እስከመቻል ደርሷል። በሂደቱም ሁለተኛ እድል መጠየቅ እንደሚቻል ዘ ቨርጅ በዘገባው ላይ አመልክቷል።

ሮቦት የሠራተኛ ፎቶግራፍ ሲመርጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወደፊት ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ሠራተኞችን ያባርር ይሆን?

በሮቦቶች እንደ ሮቦት መታየት

በንግድ ሥራዎች ላይ የህግ ባለሙያ የሆኑት ስታንሲ ሚቼል "አማዞን ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች በሮቦቶች እንደ ሮቦት ነው የሚታዩት" ይላሉ። ሠራተኞቹ እንዲያሳኩ የሚጠበቅባቸው የሥራ መጠንም ሆነ የውጤታማነት መለኪያዎቹ በውል አይታወቅም ሲሉም ያክላሉ።

አማዞን ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ "ሠራተኞች በኮምፒውር ውሳኔ ይባረራሉ የሚባለው ወሬ ፍፁም ውሸት ነው። እንደማንኛውም ድርጅት ለሠራተኞቻችን የሥራ ውጤታማነት መመዘኛ መንገድ ያለን ሲሆን ማንንም ግን ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ እገዛ ሳናደርግ አናባርርም። በፍጥነት የሚያድግ ድርጅት ስላለን በዘላቂ የሙያ ድጋፍ የሠራተኞቻችንን ብቃት ለማሻሻል እንተጋለን" ብሏል።

ድርጅቱ ምን ያህል በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እንደተደገፈና ሠራተኞችን ለማባረር እየተጠቀመ እንደሆነ በግልፅ አልገለፀም።

አማዞን ከአንድ ሳምንት በፊት ለደንበኞቹ ዕቃዎችን ያሉበት ድረስ ለማድረስ የሚወስድበትን ጊዜ ለመቀነስ ቃል የገባ ሲሆን ለዚህ መስዋትነት የሚከፍሉት ሠራተኞቹ ይሆኑ ሮቦቶች ግልፅ ያለ ነገር የለም።

አምዲት በጣም የተጨናነቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ መከታተልና ማባረር ሠራተኞች ላይ ጫና ይሆረው ይሆን?

የወደፊቱ የሥራ ሁኔታ

አማዞን ሠራተኞችን በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ውሳኔ ለማባረር የመጀመሪያው አይደለም፤ የመጨረሻውም አይሆንም። ታዲያ ይህ ለወደፊቱ የሥራ ሂደት ምን ያስከትላል?

ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለመቆጣጠርና ውጤታማነታቸውን ለመመዘን የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ለዓመታት ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

ይህንም ተከትሎ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ሠራተኞችን በመመዘን ምን ያህል ውጤታማ ነው? ሠራተኞች ለሚሰሩበት ድርጅት ያላቸውን አስተያየት እንዴት ይቀይራል? ቴክኖሎጂው በውሳኔው የሰው ድጋፍ ያስፈልገው ይሆን?

ዘ ቨርጅ ባወጣው ዘገባ "በአማዞን ሠራተኞች በየጊዜው በሚሻሻሉ የሥራ መስፈርት መለኪያዎች ይመዘናሉ። አንድ የውጤታማነት መመዘኛ ወጥቶ 75 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች ግቡን ከመቱ በኋላ መመዘኛው ይሻሻላል" ይላል።

ይህንም ተከትሎ የተሻሻለውን የሥራ መመዘኛ ማሟላት ያልቻሉ ሠራተኞች ሊባረሩ ይችላሉ። ስታንሲ "ሥራህን ለማትረፍ ሁሌም ሩጫ ነው። አንዴ በጣም ውጤታማው ሠራተኛ ልትሆን ትችላለህ ግን እሱ ምንም ፋእዳ የለውም" ይላል።

ሮቦት ቆሞ ሰነዶችን ሲመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ሰራተኖች ላይና ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጥያቄ እያስነሳ ነው

ሠራተኞች ላይ ምን ጫና ሊኖረው ይችላል?

ዴቪድ ዲቪዛ ድርጅቶች ሠራተኞችን እንደ መቅጠርና ማባረር የመሳሰሉ መሠረታዊ የሃላፊነት ቦታዎችን በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂዎች ከመተካታቸው በፊት በደንብ ጥናት እንዲያደርጉ ያሳስባል። "አንዳንድ ሥራዎች በቴክኖሎጂ መሠራት መቻላቸው ብቻ እንዲቀየሩ አያደርጋቸውም። በቴክኖሎጂ ስለተሰሩም የተሻለ ውጤታማ ናቸው ለማለት ያስቸግራል። ሠራተኞች ሊከበሩ ይገባል፤ የሚገባቸውንም ክብር በኮድ በተደገፈ ቴክኖሎጂ ለመስጠት ያስቸግራል" ይላል።

እ.ኤ.አ 2018 ዲአሎ ከስራው በሃላፊው ሳይሆን በኮምፒውተር ትዕዛዝ ነበር የተባረረው። ለቢቢሲ እንደተናገረው ሃላፊው ስለመባረሩ ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር። ዲአሎ የእርሱ አጋጣሚ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ እንዲሆን ተስፋ ያደርጋል አለበለዚያ ግን ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ይላል።