ማይክሮሶፍት ጽሁፍን የሚያቀል አሠራር ፈጠረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማይክሮሶፍት ተቋም የጸሀፊዎች ሥራ የሚያቀል አዲስ አሰራር ይፋ አድርጓል።
በ 'ማይክሮሶፍት ወርድ' የሚጽፉ ሰዎች ከእንግዲህ ስለ ቃላት ድግምግሞሽና ስለ ሰዋሰው አወቃቀር መጨነቅ የለባቸውም ብሏል።
'ማይክሮሶፍት ወርድ' ከዚህ ቀደምም የእንግሊዘኛ ቃላትና ሰዋሰው ግድፈት ያርም ነበር። አሁን ግን አሰራሩን ወደላቀ ደረጃ ወስጄዋለሁ ብሏል።
ማይክሮሶፍት እንዳለው፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) በመጠቀም የተጣመመ አረፍተ ነገር እንዲቃና፣ ሴት ወይም ወንድን ብቻ የሚገልጽ ቃል ሁለቱንም ያማከለ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር ፈጥሯል።
በጽሁፍ ውስጥ ሰነድ ወይም ሰንጠረዥ ካለ በተገቢው ሁኔታ እንዲቀመጥ ይጠቁማል። ጽሁፍን አጭርና ግልጽ ለማድረግ ለቃላትና ሀረጎች አቻ ትርጉም ይሰጣል።
አሰራሩ የቀረበው 'ማይክሮሶፍት ወርድ' ን በኢንተርኔት ለሚጠቀሙ ተገልጋዮች ሲሆን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ተግባር ላይ ይውላል።
ተቋሙ እንዳለው፤ ጽሁፍ ልዩ የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታ የሚጠይቅ በመሆኑ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መተካት አይቻልም። ሆኖም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሰውን እንዲያግዝ ማድረግ ይቻላል።
ጸሀፊና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤክስፐርት ካሉም ቼስ፣ አዲሱ አሠራር ውጤታማ እንደሚሆን ይናገራሉ።
"አሰራሩ ቃላት ከማስተካከል ጀምሮ አረፍተ ነገርና አንቀጽ ወደማስተካከል ያድጋል" ይላሉ።
አሰራሩ ለጋዜጠኞች፣ ለጸሀፊዎችም ጠቃሚ መሆኑ ባያጠያይቅም የሰው ልጅን እውቀት የሚተካም እንደሌለ አስረግጧል።












