የታኘከ ማስቲካ ዳግም ነብስ ሲዘራ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ጫማ ከማስቲካ

እንግሊዛዊቷ ዲዛይነር አና ቡሉስ የታኘከ ማስቲካን ድጋሚ ጥቅም ላይ በማዋል አዲስ ፈጠራ ከማምጣቷም ባሻገር መንገዶችን ፅዱ እንዲሆኑ በማገዝ ላይ ነች።

የማስቲካ ገበያ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ከ14 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ቢያወጣም ብዙ ማስቲካ ግን መጨረሻ ግን አካባቢን ማቆሸሽ ነው። ይህ ደግሞ ማስቲካን ከሲጋራ ቀጥሎ ሁለተኛው መንገድ የሚያቆሽሽ ነገር እንዲሆን ያደርገዋል።

የእንግሊዝ መንግሥት በየዓመቱ ለመንገድ ፅዳት ብቻ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣል።

ይህን ያስተዋለችው ዲዛይነር አና ቡሉስ አንድ ሃሳብ መጣላት። እነዚህ የሚጣበቁና አካባቢ የሚያቆሽሹ ነገሮች በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል ቢችሉስ? የሚል።

አና ቡሉስ

የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ነው አና ማስቲካን ድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል ላይ የሚያተኩረው ፕሮጀክቷን ጀመረች። ለፕሮጀክቷ መሳካት የሚያግዟትን እንደ ሲጋራ፣ ስፖንጅና የድንች ጥብስ ማሸጊያ የመሰሳሉ ናሙናዎችን ይዘት ማጥናትም ተያያዘች፤ የትኞቹን ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻልም ማጣራት ቻለች።

''ቆሻሻ ተብለው ከሚጣሉ ነገሮች መካከከል ማስቲካን ለምን ድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ሳስበው በጣሙን ደነቀኝ'' ትላለች አና።

ጥናቱንም ባካሄደችበት ወቅት ማስቲካ ከሰው-ሠራሽ ጎማ የተሠራ በመሆኑ ከፕላስቲክ ጋር የሚያመሳስለው እንደ ፖሊመር ዓይነት ይዘት እንዳለው ተረዳች።

''ፖሊሶቡቲሌን ይባላል'' ትላለች አና ''ለብስኪሌት ጎማ የውስጥ ክፍል የምንጠቀመው ዓይነት ነው''። ልክ እንደ ፕላስቲክ ከድንጋይ ከሰል ወጥቶ ከፔትሮኬሚካል የተጣራ ነው።

ማስቲካ መሰብሰብ

"ሰዎች ያኘኩትን ማስቲካ መሬት ላይ ከሚጥሉት ለእኔ እንዲሰጡኝ እንዴት ማድረግ ይቸላል?" 'ጋምድሮፕ' የተሰኙ ደማቅ ሮዝ ቀለም ያላቸውን የቆሻሻ መጣያዎች በየመንገዱ እንዲታዩ በሆነ መልኩ አስቀመጥኩት ትላለች

ቆሻሻ መጣያዎቹ እራሳቸው ከታኘኩ ማስቲካዎች የተሠሩ ናቸው። በመጣያው አጠገብ የሚለጠፍ መልዕክት ደግሞ ማስቲካዎቹ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርገው እንደሚሠሩ ያሳውቃል።

የማስቲካ መጣያ
የምስሉ መግለጫ, ደማቅ ሮዝ ቆሻሻ መጣያወቹ ከታኘኩ ማስቲካዎች የተሠሩ ናቸው

ማስቲካ የሚያኝኩ ሰዎች ይጠቀሟቸው ይሆን? ዊንቼስተር ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ቆሻሻ መጣያዎች ለመጠቀም ከተስማሙት የመጀሪያዎቹ ናቸው። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚሠሩና የሚኖሩ ወደ 8000 ሰዎችን መጣያዎቹን እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልግ ነበር።

''ተማሪዎቹ ከማስቲካ የተሰሩ መጠጫዎችን እንደተቀበሉ ያሸቷቸው ነበር'' የዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ደህንነት ኃላፊ የሆኑት ሊዝ ሃሪስ ሲናገሩ።

በከተማው የሚሸጡ ማስቲካዎች በሙሉ ከፖሊመር የሚሠሩ ስለሆነ ዳግም አዳዲስ ዕቃዎችን ለመሥራት መጠቀም ይቻላ ነበር።

ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሥራ ላይ ማዋል በጀመረ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ በቅጥር ጊቢው ውስጥ የሚጣሉ ማስቲካዎች ቁጥር መቀነስ ያዘ።

የማስቲካ መጠጫዎች
የምስሉ መግለጫ, አንድ መጠጫ ለመሥራት እስከ 42 ታኘኩ ማስቲካዎችን ይፈጃል

ሂትሮው የአይሮፕላን ማረፊያም ለሦስት ወራት ሙከራ ቆሻሻ መጣያዎቹን አስገባ፤ አልፎም ለፅዳት የሚወጣውን ገንዘብ በ6000 ፓውንድ ቀነሰ። ግሬት ሬልዌይ ስቴሽን የተሰኘውም ባቡር ጣቢያ 25 ቆሻሻ መጣያዎች አስገብቶ ብዙ መሻሻየያዎችን አመጣ።

እነዚህ ቆሻሻ መጣያዎች በመኖራቸው ቆሻሻን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻል እንኳ ሰዎች ማስቲካን መንገድ ላይ የመጣል ልምዳቸውን እንዲቀንሱ በእጅጉ አግዟል።

ማስቲካ ቅርጽ መስጠት

ለአና ሌላው ከባድ ፈተና የሆነባት የታኘኩ ማስቲካዎችን በድጋሚ ሥራ ላይ ለማዋል ፈቃደኛ የነበረ ፋብሪካን ማግኘት ነበር። ምክንያቱም ሃሳቡ በጣም አዲስ ነበር።

በስተመጨረሻም አንድ ፋብሪካን አሳምና ሥራው ተጀመረ። ቆሻሻ መጣያዎቿን ተቀብሎ የማይፈለጉትን ቆሻሻዎች ማለትም ወረቀትና ሌሎች ፕላስቲኮችን ይለይና ማስቲካውን ለከሌላ ፕላስቲክ ጋር በማቀላቀል ይፈጭላታል።

የማስቲካ ፋብሪካ
የምስሉ መግለጫ, ማስቲካው እንዲሞቅ ይደረግና ወደ ቅርጽ ማውጪያው ይገባል

በዚህ ፋብሪካ ውስጥ የታኘከው ማስቲካ በቅርጽ ማውጪያ ውስጥ ይከተታል። መጀመሪያ ይሞቅና ከዚያ እንደ ፈሳሽ እንዲወጣና በቅርጽ ማውጪያዎቹ ውስጥ ይደረግና እስኪቀዘቅዝ ይጠበቃል።

''ከዚህ ቀደም ከምንጠቀምባቸው ከፖሊፕሮፔን ይዘቶች ምንም ልዩነት የለውም'' ይላሉ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ብሬት ኒክሰን።

የእንግሊዝ ፓርላማ የማስቲካ አምራቾች ለቆሻሻው መፍትሔ የማያመጡ ከሆነ ግብር እንዲከፍሉ ሊያስገድዳቸው ነበር። ነገር ግን ሪግሊ የተሰኘው የማስቲካ አምራች ለአና ሥራ የገንዘብ ድጋፍ ለገሰ። ፋብሪካዎችም ተረፈ ምርቶቻቸውን ለአና ይለግሱ ያዙ።

የማስቲካ ቦቴ ጫማ
የምስሉ መግለጫ, በሰው-ሠራሽ ጎማ የሚሠራው ማስቲካ በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ ይውላል

ከአና ብልሃት በተጨማሪ ማስቲካ አካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ብክለት ለመቀነስ ሌሎች መፍትሔዎችም ይፈለጉ ጀመር።

ተመራማሪዎች ሰው-ሠራሽ፣ የሚበስበስና በቀላሉ የሚፀዳ ማስቲካ ለመሥራት መላ ማፈላገጉን ተያያዙት።

አሁን ላይ ገበያ ውስጥ ያሉ ማስቲካዎች ባብዛኛው ከሰው-ሠራሽና ከማይበሰብስ ንጥረ-ነገር የተሰሠሩ ናቸው።