ከጥንት ሮማውያን እስከ ትዊተር የደረሰው የ# ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዘመነኛው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ''ሃሽታግ'' (#) የምንለው ምልክት በስፓኒሽ ቋንቋ ብዙ ስሞች አሉት። ፓድ፣ ኑሜራል፣ ኩዋድሪሎ፣ ግሪላ እና ጋቶ ደግሞ ጥቂቶች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውም ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር በተገናኘ ሲሆን፤ በተለይ ''ትዊተር'' የተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ የተለያዩ ሃሳቦችና እንቅስቃሴዎች የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማድረግ ይጠቀምበታል።
ምንም እንኳን የ# ምልክትን እ.አ.አ በ2007 ላይ ትዊተር መጠቀም ቢጀምርም፤ የምልክቱ አመጣጥ ግን ወደ ጥንታዊ ሮማ ይጓዛል።
በጊዜውም ጥንታዊ ሮማውያን የአንድን ነገር ክብደት ለመግለጽ ይህንን ምልክት ይጠቀሙ ነበር።
እ.አ.አ በ1950ዎቹ በአሜሪካ የሚገኘው ''ቤል ላብስ'' የተሰኘው የሳይንሳዊ ምርምር ተቋም የሚሽከረከሩ የስልክ መደወያዎችን በማስቀረት የምንደውልበትን ቁጥር በስልኩ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ አለ።
በ1968 ደግሞ ከመደወያ ቁጥሮቹ ጎን ለጎንም የተለያዩ ጥቅሞች ያሏቸው ምልክቶችን አብሮ አስተዋወቀ። ይህ # ምልክትም ከእነዚህ መካከል ነበር።
ምልክቱ ምን ያህል ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ለማጣራት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት አብዛኛዎቹ የስልክ ተጠቃሚዎች ይህን # ምልክት መጠቀም እንደሚያስደስታቸውና ለመጠቀም ቀላል እንደሆነም ገልጸዋል።
በወቅቱም ''ኦክቶትሮፕ'' የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ መልኩ የተጀመረው የምልክቱ አጠቃቀም ወደ ዘመናዊው አለም ሲመጣ ቀስ በቀስ ብዙ ትርጉሞችን መያዝ የጀመረ ሲሆን፤ እንዲያውም የኮምፒውተር መተግበሪያዎች ላይ ሚስጥራዊ መልክቶችን እስከመወከል ደረሰ።
በአሜሪካና በእንግሊዝ በብዛት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ይህ ምልክት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በመላው ዓለም ታዋቂነትን ማትረፍ ከጀመረ አስራ አንድ ዓመታትን አስቆጥሯል።
እ.አ.አ በወርሃ ነሃሴ 2007 ነበር የቀድሞው የጉግል እና የኡበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሪስ ሜሲና ምልክቱን በመጠቀም በተለይ ደግሞ ትዊተር ላይ የተለያዩ የመወያያ ሃሳቦችን ወደፊት ለማምጣት ጥቅም ላይ እንዲውል ሃሳቡን ያቀረበው።
ትዊተር 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ሜሲና ለቢቢሲ እንደተናገረው ምልክቱ ወደ ጥቅም ከመምጣቱ በፊት ሰዎች ሃሳቦቻቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተበታተነና ለተጠቃሚዎች አስቸጋሪ ነበር።
ይህ # ምልክት ወደ ጥቅም ከመጣ ወዲህ ግን ተጠቃሚዎች ምልክቱን ካስቀመጡ በኋላ የሚፈልጉትን ርዕስ በመጻፍ ሌሎች ሰዎች ስለጉዳዩ ያጋሩትን ሃሳብ ማግኘት ይችላሉ። ይህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ የራሳቸውንም ሃሳብ ለሌሎች እንዲያጋሩ ይረዳቸዋል።












