የሆርሙዝ ወሽመጥ በተኩስ አቁም ስምምነት "መከፈቱን" ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለንግድ መርከቦች "ሙሉ ለሙሉ ክፍት" መደረጉን ካሳወቀች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ።
እስከ አርብ ጠዋት ድረስ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 98 ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ከኢራን መግለጫ በኋላ 88 ዶላር ገብቷል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን በስተደቡብ የሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ሲሆን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ይጓጓዝበታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን እርምጃ በመልካም የተቀበሉት ቢሆንም የማሪታይም ቡድኖች ግን ትክክለኛነቱን እስካሁን እያረጋገጡ ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ "የሆርሙዝ ወሽመጥ ለሁሉም የንግድ መርከቦች ለተቀሩት የተኩስ አቁም ቀናት ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑ ታውጇል" ብለዋል።
የዓለም ገበያ በዚህ መግለጫ ላይ ተመስርቶ ውሏል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የተቀናጀ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ ከየካቲት መጨረሻ አንስቶ በቴህራን ዝግ ሆኖ ቆይቷል።
የነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ እና በዓለም ገበያ የሚቀርበው የነዳጅ እና ጋዝ መጠን በጣም የቀነሰ ሲሆን ይህም ዋጋው እንዲያሻቅብ አድርጓል።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ "ሙሉ ለሙሉ ክፍት" ነው ስትል ፕሬዝዳንት ትራምፕ አድናቆት ቢገልፁም፤ ዓለም አቀፉ የመርከብ ተቆጣጣሪ ድርጅት ግን አሁንም በጥንቃቄ መስራት እንዳለበት ስጋቱን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለመክፈት ኢራን ከያዘችው ቁርጠኝነት ጀርባ ያለውን ዝርዝር መረዳት ይፈልጋል። የመርከቦች መረጃ ጥቂት እንቅስቃሰሴ ብቻ ነው የሚያሳው።
የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ "ከሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት ጋር በተያያዘ የተላለፈውን መግለጫ ሁሉም የንግድ የመርከቦች በነፃ መንቀሳቀስ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ለማረጋገጥ እየሞከርን ነው" ብለዋል።
የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አሽከርካሪዎች ላይ የቤንዚል እና ናፍጣ ዋጋ እንዲጨምር ከማድረጉ በተጨማሪ የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ላይ የፈጠረው ስጋት አየር መንገዶች በረራ እንዲያቆሙ ሊያደርግ ይችላል የሚል ፍርሃት ደቅኗል።
ቁልፍ መተላለፊያ የሆነው ወሽመጡ በአርሶ አደሮች ጥቅም ላይ የሚውለው የማዳበርያ መተላለፊያን ያስተጓጎለም ሲሆን፤ በዚህም በጦርነቱ ምክንያት የምግብ ዋጋ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተነግሯል።
የዓለም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ቁልፍ የማዳበሪያ ኬሚካል በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፍ እና ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
ይሁን እንጂ ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ከሰዓታት በፊት ጦርነቱ ከጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም የቤንዚል እና ናፍጣ ዋጋ መቀነሱን ተከታታይ ቡድኖች ጠቁመዋል።
በነዳጅ ማደያዎች ከሐሙስ ጀምሮ ታንከርን ሙሉ ለማደረግ ባለፈው የካቲት ከነበረው ይልቅ ዋጋ ቀንሷል ብለዋል።
የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት በኢራን የተወሰደው እርምጃ እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።















