በርካቶች ስፔናውያን ለካታላን ተገንጣዮች የሚሰጥ ምህረትን በመቃወም አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስር ላይ ለሚገኙት የካታላን ተገንጣዮች ለማድረግ የታሰበውን አከራካሪ የይቅርታ ዕቅድ በመቃወም በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ የተቃውሞ ሰልፎችን አካሄዱ።
የስፔን የቀኝ ክንፍ ፓርቲ አመራሮች እአአ በ2017 ያልተሳካውን የነጻነት ሙከራ የመሩ 12 ተገንጣዮች ምህረትን በመቃወም ሰልፉን ተቀላቅለዋል።
በሶሻሊስት ፓርቲ የሚመራው የስፔን መንግሥት ዕቅዱን የፖለቲካ ድጋፉን ለማጎልበት ተጠቅሞበታል ሲሉ ሰልፈኞቹ ይከሳሉ።
መንግሥት በበኩሉ በምህረቱ በካታሎኒያ ላይ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማርገብ ይረዳል ብሏል።
የከፊል ራስ ገዟ ክልል ካታሎኒያ የእአአ 2017 የነፃነት እንቅስቃሴ ስፔንን በ40 ዓመታት ውስጥ ትልቁ ወደ ተባለው የፖለቲካ ቀውስ ከቷታል።
ዘጠኝ የካታላን ተገንጣይ መሪዎች በሕገወጥ የነፃነት ሪፈረንደም ውስጥ ከነበራቸው ሚና ጋር ተያይዞ ጥፋተኛ ተብለዋል። ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙም በቁጥጥር ስር አልዋሉም።
እንደሰልፈኞቹ ከሆነ ይቅርታው ለብሔራዊ አንድነት አደጋ ነው። በማዕከላዊ ማድሪድ ኮሎን አደባባይ ሲሰበሰቡ ብዙዎች ቀይ እና ቢጫ ብሔራዊ ባንዲራዎችን ያውለበለቡ ነበር።
ካርሎስ ባንዴቻ የተባሉ ሰልፈኛ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ይህንን ማስቆም አለብ። ምክንያቱም ይቅር ለማለት ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ተገንጣዮቹ ግን ያን አያሳዩም።"
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እርምጃውን ካታሎኖችን እና ስፔናውያንን ይበልጥ ያቀራርባል በሚል ውሳኔውን ተከላክለዋል።
ሳንቼዝ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ "የስፔን ማኅበረሰብ ካለፈው መጥፎ ታሪክ ወደ ተሻለ የወደፊት ኑሮ መሸጋገር ይኖርበታል" ብለዋል።
የስፔኑ 'ኤል ሙንዶ' ጋዜጣ ባደረገው አንድ ጥናት መሠረት 61 በመቶ የሚሆኑት ስፔናውያን በይቅርታው አይስማሙም፣ 29.5 በመቶዎቹ ደግሞ ደግፈውታል።
የስፔን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካርመን ካልቮ ይቅርታው "ቅርብ" መሆኑን ጠቁመዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር አስገዳጅ ባልሆነው ሪፖርት ለካታላን ተገንጣይ መሪዎች መንግሥት ሊሰጥ የሚችለውን ይቅርታ እንደሚቃወም ገልጿል።












