ቻይና ለቡድን 7 አገራት “የጥቂት አገራት ቡድን አለምን አይመራም”

የቡድን ሰባት ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቻይና የጥቂት አባል አገራት ቡድን የአለምን እጣ ፈንታ የሚወስንበት ጊዜ አልፏል በማለት የቡድን ሰባት አባል አገራትን አስጠንቅቃለች።

የቡድን ሰባት አገራት የቻይናን ተፅእኖ ለመቀልበስ በጋራ መቆም አለብን በሚል በእንግሊዝ ባደረጉት ጉባኤ መወሰናቸውን ተከትሎ በለንደን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃለ አቀባይ ይህንን መልዕክት አስተላልፈዋል።

"አለም አቀፍ ውሳኔዎች ጥቂት አባል አገራት ባለው ቡድን የሚወሰኑበት ጊዜ አልፏል። ሁሉም አገራት ትልቅም ሆኑ ትንሽ፣ ደሃም ሆኑ ሃብታም፤ ጠንካራም ሆኑ ደካማ እኩል ናቸው ብለን እናምናለን። የአለም ጉዳዮች ሁሉንም አገራት ባማከለ መልኩ ሊወሰኑ ይገባል" ብለዋል።

የቡድን ሰባት አገራት ቻይና በዝቅተኛና መካከለኛ አገራት የምታደርገውን የመሰረተ-ልማት ግንባታ በተሻለ አማራጭ እንተካለን በሚል እቅድ ነድፈዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ምዕራባውያን አገራት የቻይናን ተፅእኖ ለመቀልበስ በአሁኑ ወቅት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ፅኑ እምነት እንዳላቸው ተንታኞች ይናገራሉ።

በዛሬው ዕለት የቡድን ሰባት አገራት የመዝጊያ መግለጫቸውን የሚያወጡ ሲሆን በዚህም ለአዳጊ አገራት የአየር ፀባይ ቀውስን እንዲታገሉ እንዲሁም ከቻይና ፕሮግራም የተሻለ አማራጭ የሆነውን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ እቅድም ይካተትበታል ተብሏል።

የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ (ቢአርአይ) በበርካታ አገራት ባቡሮችን፣ መንገዶችንንና ወደቦችን ለመገንባት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።ነገር ግን አገራት ከማይወጡበት የብድር አዘቅት በመክተትም ከፍተኛ ትችቶች ይቀርቡበታል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይን ከቻይና ፕሮግራም በከፍተኛ ጥራት ደረጃ አማራጭ ነው ያሉትን በአሜሪካ የተደገፈ የተሻለ አለም መገንባት እቅዳቸውንም አስረድተዋል

።የቢቢሲ የፖለቲካ ዘጋቢ ሮብ ዋትሰን በበኩሉ ፕሬዚዳንት ባይደን ከወረርሽኙ በኋላ ያለውን አለም በዲሞክራሲና በጨቋኞች የሚደረግ የፍትጊያ አለም ነው እንደሚሆንም መጠቆማቸውን ዘግቧል።

በእንግሊዟ ኮርንዌል በነበረው የቡድን ሰባት ጉባኤ የወጣው መግለጫ "በጥራት ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ግልፅነት በተሞላ መልኩ አጋርነትን የሚያሳይ ግንኙነትን" ከነዚህ አገራት ጋር መመስረት እንደሚፈልጉ አትቷል።