የቡድን ሰባት አገራት የቻይናን አለምአቀፋዊ ተፅዕኖ የሚገዳደር እቅድ አቀረቡ

የቡድን ሰባት አገራት

የፎቶው ባለመብት, Leon Neal/PA Media

የቡድን ሰባት (ጂ 7) አመራሮች ቻይና በመካከለኛና ዝቅተኛ አገራት የምታደርገውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ሊገዳደር የሚችል እቅድ አቅርበዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይን ከቻይና ፕሮግራም በከፍተኛ ጥራት ደረጃ አማራጭ ነው ያሉትን በአሜሪካ የተደገፈ የተሻለ አለም መገንባት እቅዳቸውንም አስረድተዋል።

በአለም ላይ ያለውን የቻይና ተፅእኖን ለመቀልበስ በሚል የቡድን ሰባት አገራት የራሳቸው አማራጭ ያሉትን ሃሳብ አቅርበዋል።

የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ (ቢአርአይ) በበርካታ አገራት ባቡሮችን፣ መንገዶችንንና ወደቦችን ለመገንባት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።

ነገር ግን አገራት ከማይወጡበት የብድር አዘቅት በመክተትም ከፍተኛ ትችቶች ይቀርቡበታል።

በእንግሊዟ ኮርንዌል በነበረው የቡድን ሰባት ጉባኤ የወጣው መግለጫ "በጥራት ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ግልፅነት በተሞላ መልኩ አጋርነትን የሚያሳይ ግንኙነትን" ከነዚህ አገራት ጋር መመስረት እንደሚፈልጉ አትቷል።

ነገር ግን ቡድን ሰባት ያቀረቡት ይህ እቅድ ፈንዱ ከየት እንደሚመጣ አልተነገረም። የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርኬል ለዚህ ጅማሮ ገንዘብ ከየትም ሆነ እንዴት እንደሚመደብ ለመወሰን ጊዜው ገና ነው ብለዋል።

አሜሪካ ለአመታት ያህል ቻይና በአገራቱ ላይ የምታካሂደው "የብድር ዲፕሎማሲ" ነው በማለት በከፍተኛ ሁኔታ ታወግዛታለች።

ቡድን ሰባት የተባሉት የአለም ሃብታምና በዲሞክራሲ የዳበሩ አገራት የቻይናን ተፅእኖ ከመቀልበስ በተጨማሪ አለም የሚያጋጥማትን የወደፊቱ ወረርሽኝ ለመከላከልም አዲስ እቅድ ነድፈዋል።

አገራቱ ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የሚያስፈልገው ፈቃድ ከመቶ ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መስጠት የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ መክረዋል።

ይህ እቅድ ከጉባኤው ይፋዊ መግለጫ ጋር እሁድ ይወጣል ተብሏል።

በካብሪስ ቤይ ሪዞርት የሚደረገውን የሶስት ቀን ጉባኤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።