ከጄፍ ቤዞስ ጋር ለሚደረገው የጠፈር በረራ አንድ ግለሰብ በ28 ሚሊዮን ዶላር ጨረታውን አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ ወደ ጠፈር በሚያደርጉት ጉዞ ለመብረር አንድ ግለሰብ 28 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል የጉዞውን ጨረታ ማሸነፋቸው ተሰምቷል።
በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ በነበረው የቢሊየነሩ ብሉ ኦሪጅን ኩባንያ አማካኝነት በተደረገው ጨረታ ነው የጠፈር በረራው አሸናፊ መሆናቸው የታወቁት።
የግለሰቡ ማንነት እስካሁን ባይታወቅም በሚቀጥሉት ሳምንታት ይፋ እንደሚሆን ተነግሯል።
ጨረታው ከ140 በላይ አገራት ዜጎች የተሳፉበት ነው ተብሏል።
በሐምሌ አጋማሽ ሊደረግ በተካሄደው በዚህ የጠፈር በረራ ላይ የጄፍ ቤዞስ ወንድም ማርክና ስማቸው ያልተጠቀሰ የጠፈር ቱሪስት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
ለሁለት ወራት ያህል ክፍት የነበረው ጨረታ የነበረው የገንዘብ መጠን ከ5 ሚሊዮን ዶላር በታች የነበረ ቢሆንም ጨረታው በበይነ መረብ ክፍት በሆነበት ወቅት አምስት እጥፍ መጨመሩም ተገልጿል።
ከጨረታው የተገኘው ገንዘብም ለብሉ ኦሪጅን ኩባንያ ይውላል ተብሏል።
ጄፍ ቤዞስ በአለማችን ካሉ ቁንጮ ሃብታሞች አንደኛው ሲሆኑ በፎርብስ መፅሄት መሰረት አንጡራ ሃብታቸው 186.2 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
"በሃምሌ አጋማሽ ከወንድሜና የልብ ጓደኛዬ ከምለው ማርክ ጋር አስደናቂ የሚባለውን የጠፈር ጉዞ እናደርጋለን" በማለትም በዚህ ሳምንት በኢንስታግራም ገፃቸው ጄፍ ስለ ጉዞው አስመልክተው ፅፈዋል።
የጀፍ ቤዞስ ወንድም ማርክ በበኩሉ በረራውን "ልዩ እዽል" ብሎታል።
እንደ ብሉ ኦሪጅን ድረ-ገፅ ከሆነ ኩባንያው መንገደኞችን ከመሬት 100 ኪሎሜትር በላይ በመውሰድ የመሬት ስበት የሌለበት ቦታን እንዲቃኙ ያደርገጋቸዋል።
ከዚያም ወደ መሬት በፓራሹት እንዲመለሱ ይደረጋል። አጠቃላይ ይህ ጉዞ አስር ደቂቃዎችንም ይወስዳል ተብሏል።












