ዋትስአፕ አዲሱን የአጠቃቀም መመሪያ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል

የእጅ ስልክ በእጁ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዋትስአፕ ተግባሪያዊ ሊያደርግ ያሰበው የአጠቃቀም ደንብ እና ግዴታ ቀነ ገደብ መቃረቡን ተከትሎ ለተጠቃሚዎቹ የሚልከው የማስታወሻ መልዕክት ድግግሞሽ ክፍ ብሏል።

ዋትስአፕ ከነገ ጀምሮ በአጠቃቀም ውሎችና ሁኔታዎች ላይ ማሻሻያ ያደርጋል። ተጠቃሚዎች ከነገ በፊት ዋትስአፕ ያስተዋወቃቸውን አዳዲስ ደንቦች መቀብል ይኖርባቸዋል።

አዲሱን የአጠቃቀም ደንብ እና ግዴታ የማይቀቡ ደንበኞች በርካታ የዋትስአፕ አግልገሎቶን ማግኘት አይችሉም።

ይህንንም ተከትሎ ዋትስአፕ መመሪያውን ወዳልተቀበሉ ተጠቃሚዎቸቹ 'ተከታታይ' የማስታወሻ መልዕክቶችን እየላከ ይገኛል።

የሚደረገው ለውጥ በቀዳሚነት 'ቢዝነሶች' ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ የሚያተኩር ይሆናል።

ማሻሻያው የመልዕክት መተግበሪያው ዋትስአፕ ከእህት ኩባንያው ፌስቡክ ጋር መረጃን መጋራት እንደሚጨምር ባለፈው ጥር ላይ ተገለጾ ቅሬታን ፈጠሮ ነበር። ሆኖም አዲሱ ውል ላይ ይህ ማሻሻያ እንደማይከተትበት ታውቋል።

አዲሱን የዋትስአፕ ደንብ የማይቀበሉ ደንበኞች አካውንታቸው ባይዘጋም እንደ ቀድሞ የጹሁፍ መልዕክት መለዋወጥ አሊያም በድምጽ ወይም በቪዲዮ መደዋወል አይችሉም።

አስተማማኝ ደህንነት እንዳለው የሚነገርለት ዋትስአፕ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የግንኙነት መስመር ሚስጥራዊነቱን የሚጠብቅ ስርዓት አለው። ይህም ከላኪውና ከተቀባዩ በስተቀር የተላከው መልዕክት በማንኛውም ሰው እጅ እንዳይገባ ያደርገዋል።

ዋትሳፕ ቀደም ብሎ ባሰራጨው መልዕክት የሚከተሉት ጨመሮ መረጃዎች ለፌስቡክ ኩባንያ መጋራታቸውን አስታውቋል፡

  • ስልክ ቁጥርና ሌሎች ዋትስአፕ ለመክፈት የሚያግዙ እንደ ስም ያሉ መረጃዎች
  • የተጠቃሚዎችን የእጅ ስልክ አይነት። ይህም የሞባይሉን አይነትና አምራቹን ይጨምራል
  • የእጅ ስልኩን መገኛ ቁጥር [IP address] ይህም ተጠቃሚው የሚገኝበትን ቦታ ይጠቁማል
  • በዋትስአፕ በኩል የሚፈጸም ክፍያና የገንዘብ ዝውውር

ሆኖም ይህ የዋትስአፕ አዲስ የአጠቃቀም ደንብ እና መመሪያ የግል መረጃ አጠባበቅ ሕግ [privacy laws] ባሉባቸው አውሮፓ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተግባራዊ አይሆንም።