ኢትዮ ቴሌኮም አስፋፋሁት ያለው 4 ጂ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Stefano Sferrazza / EyeEm
በስልክዎ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ባለዎት የኢንተርኔት ፍጥነት የተለያዩ ምልክቶችን ይመለከታሉ።
E፣ O፣ GPRS፣ 3 ጂ እና 4 ጂጥቂቶቹ ናቸው። 4 ጂ ከእነዚህ መካከል ፈጣን የሚባለው ነው።
4 ጂ ኤል ቲ ኢ በሚልም ሊገለጽ ይችላል 'Long Term Evolution' ወይም በግርድፉ የረጅም ጊዜ ዝግመተ ለውጥ በሚል ሊተረጎም ይችላል።
እጅግ ፈጣን የተባለለት የ'አምስተኛ ትውልድ' ወይም 5 ጂ የሞባይል ኢንተርኔት ጥቅም ላይ ከዋለም ዋል አደር ብሏል።
ቴክኖሎጂው ሁሉም ዘንድ አልደረሰም። ቢደርስም ለዚህ የተዘጋጀ ስልክ ያስፈልጋል።
ለሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነት ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ባይኖሩም የኢንተርኔት አቅራቢዎች አንደኛው ትውልድ ወደሌላኛው በማቅናት ወደ አራተኛው እና አምስተኛው ትውልድ እየዘለቁ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ኢትዮ ቴሌኮም ከ50.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ይገልጻል። ኩባንያው አሉኝ ከሚላቸው ከ50.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች መካከል ከ 48 .9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ከ 23.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው።
የኢንተርኔት አገልግሎትን እአአ በ1997 ይፋ ሲያደርግ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ጀመረ።
በ2007 የ3ጂ አገልግሎት ይፋ አድርጓል።
"የ4 ጂ ኤልቲኢ አገልግሎት ከፍተኛ ፍጥነትና ባንድዊድዝ እንዲሁም አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ እንደመሆኑ ደንበኞቻችን አገልግሎታቸውን ዲጂታይዝ ለማድረግ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ ነው" በሚል ኢትዮ ቴሌኮም 4ጂ/ኤልቲኢ ኢንተርኔትን በ2015 ነበር በአዲስ አበባ ያስጀመረው።
ለዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረው የ 4 ጂ አገልግሎትን"በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች የዳታ ትራፊክ ዕድገትና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የ4 ጂ ኤልቲኢ አገልግሎት የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን በቀጣይ በሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ" ብሏል ኩባንያው በድረገጹ።
አገልግሎቱን በተለያዩ አካባቢዎች በማድረስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ አገልግሎቱን አስጀምሯል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ምሥራቅ 'ሪጅን' በሚገኙት አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ገላን፣ ሞጆ እና አዋሽ መልካሳ አገልግሎቱን ለደንበኞቹ ማድረስ ችሏል፡፡
ቀጣይ ተረኞች ደግሞ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ እና ቻግኒ ሆነዋል፡፡
በደቡብ ደቡብ ምዕራብ 'ሪጅን' ውስጥ በሚገኙ ስድስት ከተሞች ማለትም በወላይታ ሶዶ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕና፣ በወልቂጤ፣ በቡታጅራ እና በጂንካ የአራተኛው ትውልድ የማስፋፊያ ፕሮጀከቱን አጠናቆ አገልግሎቱ ተጀምሯል፡፡
ኩባንያው ለህብረተሰቡ ያቀረበውን የ4 ጂ ኢንተርኔት ለመጠቀም የሚያስፈልገውን የተንቀስቃቃሽ ስልክ ለህብረተሰቡ 'በተመጣጣኝ ዋጋ' እንዲያቀርቡ አስተላልፏል።
"በኩባንያችን የሦስት ዓመት የዕድገት ስትራቴጂ ላይ እንዳመላከትነው በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች የዳታ ትራፊክ እድገትና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የየ4 ጂ ኤልቲኢ አገልግሎት የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ እየሠራ ይገኛል" ብሏል።
በቀጣይ ወራትም በሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎች እያከናወንኩ ሲል በድረገጹ አስነብቧል።
ለመሆኑ እነዚህ ኢትዮቴሌኮም አስፋፋው ያለው 4 ጂ እና ሌሎች የተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት ትውልዶች ምንድናቸው?

የፎቶው ባለመብት, EthioTelecom
1ጂ
1ጂ ወይም የመጀመሪያው ትውልድ የሞባይል ዳታ እአአ በ 1991 ተዋወቀ፡፡
1 ጂ አናሎግ የሆነ የመረጃ መለዋወጫ ዘዴ ነው፡
በ 1 ጂ ጥሪዎችን ማስተላል ብቻ ነው የሚቻለው።
2ጂ
2 ጂ የጽሑፍ መልዕክቶችን አስተዋውቋል።
በኤስኤምኤስ በመባል የሚታወቀው 2 ጂ የጽሑፍ መልዕክቶችን ለመላክ አስችሏል፡፡
2 ጂ በተጨማሪም ኤምኤምኤስ (መልቲሚዲያ ሜሴጂንግ ሰርቪስ) የተባለ የምስል መልዕክቶች ማስተላለፊያም አስተዋውቋል፡፡
በሞባይል ስልኮች ላይ ጂኤስኤም፣ ጂፒአርኤስ ፣ ኢዲጂኢ የሚባሉ አገልግሎቶች አሉት።
3ጂ
የቪዲዮ ጥሪ እአአ በ 2001 ይፋ ሆነ።
3ጂ እና የ2 ሜጋባይትስ በሰከንድ (ወይም በሰከንድ 0.25 ሜጋ ባይት) መረጃው መለዋወጥ የሚያስችል አገልግሎት የመጀመሪያዎቹ ስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለገበያ ሲቀርቡ ተዋወቀ፡፡
እጅግ ፈጣን ባይሆንም ገመድ አልባ የኢንተርኔት በማቅረብ የመጀመሪያው ሲሆን የቪዲዮ ጥሪ እንዲኖር አስችሏል፡፡
ለማስረዳት ያህልም 4.26 ጊጋ ባይት መረጃ ለማውረድ ከአምስት ሰዓት በላይ ይጠይቃል።
4ጂ
2010 ደግሞ 4 ጂን ይዞ ብቅ አለ።
በሚሰጠው ፈጣን ግንኙነትም የሞባይል ጌሞችን እስከወዲያኛው ቀይሯል፡፡
አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው በጣም ፈጣኑ 4 ጂ የሞባይል ኔትዎርክ በአማካይ በሰከንድ 45 ሜጋ ባይት ይሰጣል። ኢንዱስትሪው በሰከንድ አንድ ጊጋ ባይት የመድረስ ህልም አለው።
በ 3 ጂ ተመሳሳይ ፊልም ለማውረድ ከአምስት ሰዓታት በላይ ይወስድ የነበረው ጊዜ 4 ጂ ላይ ከ 8 ደቂቃ በታች እንዲሆን አስችሏል ተብሎ ይገመታል።
5ጂ ምን ማለት ነው?
የቀጣዩ ትውልድ የሞባይል በይነመረብ ግንኙነት ሲሆን በጣም ፈጣን ዳታ የማውረድ እና የመጫን አገልግሎትን ይሰጣል።
የሬዲዮ ሰፔክትረም በመጠቀም እጅግ በጣም ብዙ መሣሪያዎችን በአንድ ጊዜ የሞባይል ኢንተርኔቱን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ፡፡
አሁን በስማርት ስልኮቻችን የምንሠራቸውን ማንኛውንም ነገር በፍጥነት እና በተሻለ ለማከናወን ያስችለናል።
ድሮኖች፣ መኪኖች እና የሞባይል ጌሞች በዚህ ፈጣን ኢንተርኔት በመጠቀም የተሻለ ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡
የሞባይል ቪዲዮዎች በቅጽበት እና ከመቆራረጥ ነፃ በሆነ መልኩ ይቀርባሉ ፡፡ የቪዲዮ ጥሪዎች ይበልጥ ንጹህ እና መንቀጥቀጥ ሳይኖራቸው ለደንበኞች ይደርሳሉ። ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በሚጠለቁ ቁሳቁሶች አማካኝነት ድንገተኛ ሁኔታ ሲከሰት ወዲያውኑ ሐኪሞችን በማሳወቅ ጤንነትዎን በወቅቱ ሊቆጣጠሩት ይችላሉ ፡፡
5 ጂ ከ 10 እስከ 20 እጥፍ የሆነ ፍጥነት ማሳካት ይችላል ይላል የቺፕ አምራቹ ኩዋልኮም፡፡ በዚህ ፍጥነት በአንድ ደቂቃ ባለከፍተኛ ጥራት ፊልም ማውረድ ያስችሉዎታል።
ኢትዮቴሌኮም 5 ጂን ለደንበኞቹ ለማድረስ የያዘው ዕቅድ እንዳለ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
















