በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ ስለተጫረቱት ኩባንያዎች ምን ይታወቃል?

የሞባይል ስልክ ማማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ከአንድ መቶ ሃያ ዓመት በላይ በመንግሥት ስር በሚተዳደረው ኢትዮቴሌኮም ብቸኛ የበላይነት በብቸኝነት ተይዞ ቆይቶ አሁን ተፎካካሪ እንዲገባበት ተፈቅዷል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለት የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ካወጣ ከወራት በኋላ በተለያዩ አገራት ውስጥ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል።

መንግሥት በእጁ የሚገኙትን የተለያዩ ተቋማት ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር ከወሰነ በኋላ ካቀረበው ሁለት የቴሌኮም ዘርፍ ፈቃዶች በተጨማሪ የኢትዮ ቴሌኮምን የተወሰነ ድርሻ ለግልና ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ለመሸጥ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህንን ዘርፍ ለውድድር ክፍት ማድረግ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ የነበሩ ሲሆን፤ በተለይ በስልክና በኢንተርኔት የአገልግሎት ጥራት ላይ የሚያስከትለው ለውጥና የዋጋ ቅናሽ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አውንታዊ እድገትን ያመጣል የሚሉት ይበረክታሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና ፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚሉት፤ በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት ለማስመዝገብ ዘርፉን ክፍት ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ወደ ገበያው ለመግባት ያመለከቱት ኩባንያዎች ትልልቅ መሆናቸውን በመግለጽም "ዘርፉን ለማዘመን የውጭ ዕውቀትና ካፒታል ያስፈልጋል። ኩባንያዎቹ ይህንን ይዘው ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ" ሲሉ አስረድተዋል።

የእነዚህ ተቋሞች ወደ ገበያው መምጣት ምጣኔ ሀብቱ ላይ አወንታዊ ሚና እንዳለው የሚያሰምሩበት አቶ ዘመዴነህ፤ እንደ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት፣ አምራቾችና በሌሎችም ዘርፎች ያሉ ተቋማት በተሻለ ቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሠሩ እንደሚረዳም ያክላሉ።

በውጭ ኩባንያዎች ከሚያዙት ሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች በተጨማሪ ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮቴሌኮምም በሩን ለባለሃብቶች ይከፍታል።

በዚህም በመንግሥት ብቸኛ ባላቤትነት ስር የቇየው ተቋሙ በቅርቡ 40 በመቶን ድርሻ ለውጪ ባለሃብቶች፣ 5 በመቶን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን መንግሥት እንደሚይዘው ይጠበቃል።

የቴሌኮም ዘርፍ ለውድድር ክፍት መሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት በርካሽ ዋጋን ከማስገኘቱ ባሻገር "ለሥራ ፈጠራና ለውድድር በር ይከፍታል" ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

እንደ ቴሌኮም ያሉ የመሠረታዊ አገልግሎት ዘርፎች ክፍት ሲሆኑ ከሥራ ፈጠራ በተጨማሪ ምጣኔ ሀብትን እንደሚያሳድጉ የሚናገሩት አቶ ዘመዴነህ፤ "ኢትዮጵያ ዘርፉን ለገበያ ክፍት ማድረጓ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ ነው" ይላሉ።

ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ መንግሥት ከወሰነ ጥቂት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ያዘጋጃቸውን ሁለት ፈቃዶች ለመስጠት የጨረታ ጥሪ ያቀረበው ኅዳር 18/2013 ዓ.ም ነበረ።

በዚህም 12 ያህል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ የጨረታ ሰነድ ያቀረቡት የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን እና የአራት ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው።

በዚህም መሰረት የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የብሪታኒያው ቮዳፎን፣ የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም እና ኤምቲኤን ግሩፕ፣ የብሪታኒያው ሲዲሲ ግሩፕ እና የጃፓኑ ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት የጨረታ ሰነዳቸውን አስገብተዋል።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሳተፍ በጋራና በተናጠል ፍላጎት ስላሳዩት ኩባንያዎች ምን ይታወቃል? ተቋሞቹ ከዚህ ቀደም በየትኞቹ አገራት ሠርተዋል? በቴሌኮም ዘርፍ ያላቸው እንቅስቃሴስ እንዴት ይገለጻል?

ሳፋሪኮም

ዋና መሥሪያ ቤቱ ናይሮቢ የሚገኘው ሳፋሪኮም የኬንያ የቴሌኮም ድርጅት ሲሆን፤ ኬንያ ውስጥ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢና በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው።

ሳፋሪኮም የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመር፣ የኢንተርኔት፣ የስልክ ግብይት እንዲሁም ሌሎችም አገልግሎቶች ይሰጣል።

እአአ በ1997 ገደማ የተቋቋመው ሳፋሪኮም፤ በተለይም ኤምፔሳ በተባለው የሞባይል ገንዘብ መለዋወጫ አገልግሎቱ በስፋት ይታወቃል።

ሌላው ኤምሽዋሪ የሚባለው አገልግሎት ሳፋሪኮም ከባንክ ጋር በጥምረት የጀመረው ሲሆን፤ ተገልጋዮች በሞባይል ገንዘብ እንዲቆጥቡና እንዲበደሩ ያስችላል።

ሳፋሪኮም በሌሎች አገራት ከሚሠሩ የቴሌኮም ድርጅቶች ጋር በመጣመር አገልግሎቱን ማስፋፋት ጀምሯል። ከእነዚህ መካከል ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድ ይጠቀሳሉ።

የሳፋሪኮም ድረ ገጽ እንደሚያሳየው፤ ከኬንያ የቴሌኮም ገበያ 64.5 በመቶ ድርሻን ይወስዳል። ወደ 35.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችም አሉት።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ቮዳፎን ከሳፋሪኮም 40 በመቶ ድርሻን ገዝቷል።

ሳፋሪኮም ኬንያ ውስጥ ከሚገኙ የቴሌኮም ድርጅቶች ቀድሞ የ3ጂ ኢንተርኔት አስገብቷል። በቅርቡ ደግሞ ዋና ዋና በሚባሉ የኬንያ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት መዘርጋት ጀምሯል።

የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ጥሪ ማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ፤ ሰዎች እንዲደውሉላቸው የሚጠይቅ የጽሁፍ መልዕክት በነጻ እንዲልኩ የሚያስችል አሠራር ዘርግቷል።

የሞባይል ስልክ ማማ

ቮዳኮም

በአፍሪካ ውስጥ ሰፊ የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጡት ኩባንያዎች መካከል ቮዳኮም ይጠቀሳል። የኢንተርኔት፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ እንዲሁም ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ዘርፎችም አሉት።

መነሻውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ቮዳኮም፤ በታንዛንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ እና ኬንያ ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል።

የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታው ከ296 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ የድርጅቱ ድረ ገጽ ይጠቁማል።

ቮዳኮም ቢዝነስ አፍሪካ በሚል በ29 አገራት ንግድ ነክ አገልግሎቶች ይሰጣል። ከቮዳኮም 60.5 በመቶ የሚሆነው የባለቤትንት ድርሻ የብሪታኒያው ቮዳፎን ነው።

የ3ጂ እና 4ጂ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጠው ቮዳኮም፤ በአፍሪካ በግንባር ቀደምነት የቀጥታ 5ጂ ኔትወርክ እንደዘረጋ ይነገርለታል።

ቮዳፎን

የብሪታኒያው ቮዳፎን አገልግሎት የሚሰጠው በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ውስጥ ሲሆን፤ በ21 አገራት ውስጥ ኔትወርክ ዘርግቷል።

አውሮፓ ውስጥ በኔትወርክ ዝርጋታ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ የሚነገርለት ቮዳፎን፤ አፍሪካ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሞባይል ገንዘብ መለዋወጫ አገልግሎትን እንዲጠቀሙ እንዳስቻለ በድረ ገጹ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል።

ቮዳፎን የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ፣ ኢንተርኔትና ሌሎችም ተያያዥ አገልግሎቶች ይሰጣል።

በኢንተርኔት አማካይነት የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ነክ መገልገያዎችን በማስተሳሰር የሚታወቀውና ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ የሚባለውን አገልግሎት በተለይም ለንግድ ተቋማት ያቀርባል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1980ዎቹ ወዲህ የተስፋፋው ቮዳፎን የስልክ ጥሪ፣ የጽሁፍ መልዕክትና ኢንተርኔት የሚያቀርብ ሲሆን፤ አውሮፓ ውስጥ የ5ጂ ዝርጋታ ላይ በስፋት ይሠራል።

በአፍሪካ በጋና፣ በሊቢያና በካሜሩን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ በኳታር፣ በባህሬንና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ በእስያ ደግሞ በጃፓን እና በሕንድ የሚሰጠውን አገልግሎት መጥቀስ ይቻላል።

ኤምቲኤን ግሩፕ

ኤምቲኤን ግሩፕ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ የቴሌኮም ተቋም ነው። በተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እንዲሁም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አገልግሎት ይሰጣል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን ደቡብ አፍረካ ጆሀንስበርግ ያደረገው ተቋም ወደ 273 ሚሊዮን የሚጠጉ ተገልጋዮች እንዳሉት በድረ ገጹ ያሰፈረው መግለጫ ይጠቁማል።

በ20 አገሮች የሚሠራው ኤምቲኤን ግሩፕ ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው ከናይጄሪያ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ በ1994 ገደማ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ነበር የተቋቋመው።

የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ እና የሞባይል ገንዘብ ልውውጥ የሚሰጠው ኤምቲኤን ግሩፕ፤ በዋትስአፕ መተግበሪያ ተጠቃሚዎቹ የአየር ሰዓት እና የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት (ዳታ) እንዲያገኙ በማስቻል ስሙ ይነሳል።

ከማስተርካርድ ጋር በመጣመር ለተጠቃሚዎቹ የድረ ገጽ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ከመዘርጋቱ ባሻገር፤ በሞባይል ገንዘብ መለዋወጥ የሚቻልበት መንገድም አለው።

ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን

ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን የጃፓን ተቋም ሲሆን ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ነው።

በብረት ምርት፣ በትራንስፖርትና ምህንድስና፣ በማዕድን፣ በሪልስቴት እና ሌሎችም ዘርፎች ለረዥም ዓመታት ሠርቷል።

ከእነዚህ በተጨማሪ በመገናኛ ብዙሃን እና በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ የሚሰጠው አገልግሎት የኬብል ቴሌቭዥን እና 5ጂ የሞባይል ኢንተርኔትን ያካትታል።

ቲ-ጋያ የሚባል የሞባይል አከፋፋይ ያለው ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን አጠቃላይ አገልግሎቶቹን በ66 አገራት እንደሚሰጥ ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ከተሰማራባቸው ዘርፎች መካከል የመገናኛ ብዙሃን እና ቴሌኮምዩኒኬሽን ቅርንጫፉ 11.9 በመቶ ድርሻ ይይዛል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1919 ኦሳካ ኖርዝ ሀርበር በሚል ስያሜ ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራው ድርጅቱ፤ በምሥራቅ እስያ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና ሌሎችም የዓለም ክፍሎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

ሲዲሲ ግሩፕ

የብሪታንያው ሲዲሲ ግሩፕ እንደ አውሮፓውያኑ በ1948 ከተመሠረተ ወዲህ ላለፉት 70 ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ ሲሠራ ቆይቷል።

በተመሠረተበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዛምቢያ የሲሚንቶ ዘርፍ፣ በቦትስዋና የከብር እርባታ ዘርፍና በሌሎችም የአፍሪካ እና እስያ አገሮች ሠርቷል።

1998 ላይ ሴልቴል በተባለ የአፍሪካ የሞባይል ስልክ ድርጅት ኢንቨስት ማድረጉ ከቴሌኮም ዘርፍ እንቅስቃሴው አንዱ ነው።

በድረ ገጹ ላይ በሚገኘው መረጃ መሠረት፤ በተለያዩ አገሮች በጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ፣ በጤና እና ሌሎችም ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ ይቻላል።

ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የተደረገባቸው አገራት ሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኮትዲቯር ናቸው።