በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፉ እስካሁን የተለዩ ተቋማት አለመኖራቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Construction Photography/Avalon
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ የግል ተቋማት እንዲሳተፉ ለማድረግ በተጀመረው ሂደት ውስጥ ፍላጎት ካሳዩ የውጭ ኩባንያዎች መካከል እስካሁን ለቀጣይ ዙር የተመረጡት ታውቀዋል መባሉ ሐሰት መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ባልቻ ሬባ (ኢንጂኒየር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአንድ ጋዜጣ እንደተዘገበው በዘርፉ ለመሳተፍ ከቀረቡት መካከል ተለይተው ለቀጣይ ሂደት አጭር መዘርዝር ወጥቶ የታጩ ኩባንያዎች አሉ የሚለውን "ፍፁም ውሸት ነው" ብለዋል።
የኬንያው 'ቢዝነስ ዴይሊ' ጋዜጣ በዛሬው ዕትሙ ኬንያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት የቴሌኮም ዘርፍ ጉልህ ተሳትፎ ያለው ሳፋሪኮም የተባለው ግዙፍ ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመሳተፍ ባሳየው ፍላጎት ለቀጣይ ሂደት ከተረጡት መካከል መሆኑን የሚገልጽ ዘገባ አውጥቷል።
ነገር ግን ዘገባው ትክክል አለመሆኑን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ባልቻ ሬባ "ሒደቱ ግልፅ እና በውድድር ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው" በማለት ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው ተቋማት የጨረታ ሰነድ መውጣቱንና በዚያም መሠረት ተጫራቾች ሰነድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
ከዚያ በኋላ ግልፅ እንዲሆኑ ጥያቄ ለቀረበባቸው ጉዳዮች "በሙሉ መልስ ተሰጥቶ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው" ብለዋል።
የጨረታ ማስገቢያ ቀኑ በተጫራቾች ጥያቄ መሠረት ቀድሞ ከተቀመጠለት የእ.ኤ.አ መጋቢት 5 ቀን በአንድ ወር ተራዝሞ ሚያዝያ 5 ቀን እንዲሆንም ተደርጓል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ብሩክ ታዬም (ዶ/ር) ይህንኑ ያጠናክራሉ።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ አስራ ሁለት ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫ (ኤክስፕረሽን ኦፍ ኢንተረስት) ማስገባታቸውን የሚያስታውሱት ብሩክ (ዶ/ር) ባለፈው ኅዳር ላይ የጨረታ ሰነድ የገዙ ድርጅቶች መኖራቸውንና ይህም ዋጋን የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ለሕዝብ ግልፅ አልሆነም ብለዋል።
"የጨረታ ሰነድ ሲያስገቡ ነው ማን ነው እየተጫረተ ያለው የሚለውን የምናውቀው" ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ስለዚህም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን ከገለጹ ተቋማት መካከል ለቀጣይ ዙር ሂደት የሚለዩትን ለማወቅ ጊዜው ገና መሆኑን ኃላፊዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
'ቢዝነስ ዴይሊ' በዛሬው ዘገባ ግን ሳፋሪኮም የተባለው የቴሌኮም ኩባንያ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለመስጠት ላቀረበቻቸው ሁለት ፈቃዶች ለቀጣይ ሂደት ከታጩት ስድስት ኩባንያዎች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክቷል።
ከ110 ሚሊየን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያን በብቸኝነት እያገለገለ ያለው መንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮም ሲሆን፤ በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ላይ የምትገኘው አገር የቴሌኮም ዘርፍ ለውጪ ኩባንያዎች አጓጊ በመሆኑ የተለያዩ ተቋማት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች ሁለት ፈቃዶችን ከማዘጋጀቷ በተጨማሪ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የኢትዮቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥም ተዘጋጅታላች።
















