በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ እየተፎካከሩ ያሉ ኩባንያዎች ታወቁ

የቴሌኮሙኑኬሽን ማማ

የፎቶው ባለመብት, Construction Photography/Avalon

በኢትዮጵያ በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ለመሳተፍ ስድስት የውጭ አገራት ኩባንያዎች በጥምረትና በተናጠል ለመሥራት ፍላጎታቸውን መግለጻቸው ተነገረ።

በመንግሥት በሚተዳደረው ኢትዮቴሌኮም በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ የውጭ ድርጅቶች እንዲሳተፉበት ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ በተለያዩ አገራት ውስጥ በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት በጨረታው ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ ከኢትዮቴሌኮም በተጨማሪ ለሁለት የዘርፉ ተቋማት ፈቃድ ለመስጠት እንደምትፈልግ ካሳወቀች በኋላ በአፍሪካና በሌሎች አህጉራት ውስጥ የሚሠሩ ድርጅቶች በወጣው ጨረታ ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህም መሰረት የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የብሪታኒያው ቮዳፎን፣ ከደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም እና ኤምቲኤን ግሩፕ፣ የብሪታኒያው ሲዲሲ ግሩፕ እና የጃፓኑ ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት የጨረታ ሰነዳቸውን አስገብተዋል።

በዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን በጨረታው ካሳወቁ ኩባንያዎች መካል የተወሰኑት በጥምረት ለመስራት የሚፈልጉ ሲሆን ሁሉም በተለያዩ አገራት ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ የዳበረ ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።

በተደጋጋሚ ሲራዘም የቆየው የጨረታው ሂደት ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 18/2013 ዓ.ም ተጠናቆ ሁለቱን የቴሌኮም ፈቃዶች ለማግኘት ሰነዶቻቸውን ያስገቡት ኩባንያዎችን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በዚህ ጨረታ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የጨረታ ጥሪ ያቀረበው ኅዳር 18/2013 ዓ.ም ነበረ።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም በቀጣይነት ሁለቱን ፈቃዶች የሚያገኙትን ኩባንያዎች በተመለከተ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በቀረቡት የጨረታ ሰነዶች ላይ በሚያካሂዳቸው የተለያዩ ግምገማዎች መሠረት ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያን በብቸኝነት እያገለገለ ያለው መንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮም ሲሆን፤ በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ላይ የምትገኘው አገር የቴሌኮም ዘርፍ ለውጪ ኩባንያዎች አጓጊ በመሆኑ የተለያዩ ተቋማት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች ሁለት ፈቃዶችን ከማዘጋጀቷ በተጨማሪ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የኢትዮቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥም ተዘጋጅታላች።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎትን በብቸኝነት እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮቴሌኮም ሲሆን በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ተቋማት ክፍት እንደምታደርግ ያስታወቀችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ነው።