በክብረ ወሰን የተንበሸበሸው የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኖማድላንድ የተሰኘው የድራማ ዘውግ ያለው ሲኒማ ሦስት የአስካር ሽልማቶችን በማግኘት የዘንድሮው አነጋጋሪ ፊልም ሆኗል።
የዘንድሮው ኦስካር 'የመጀመሪያው' እና 'የመጀመሪያዋ' በሚሉ ቅጥያዎች የደመቀና በክብረ-ወሰን የተንበሸበሸ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።
ጥቁር እንግሊዛዊው ዳንኤል ካሉያና ሰር አንተኒ ሆፕኪንስ በትወና ዘርፍ አሸናፊ ለመሆን ችለዋል።
ዳይሬክተሯ ክሎዊ ዣዎ በምርጥ ሴት ዳይሬክተር ዘርፍ የኦስካር ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያዋ እስያዊት ሆናለች።
የ83 ዓመቱ ሰን አንተኒ ሆፕኪንስ ምርጥ ተዋናይ በመባል በዕድሜ ትልቁ ተሸላሚ ሲሆን ዳንኤል ካሉያ ደግሞ በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ ኦስካር ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር ብሪታኒያዊ ሆኗል።
ፍራንሲስ ማክዶርማን 'ኖማድላንድ' ላይ ባሳየችው ትወና ምርጥ ሴት ተዋናይት ተብላ የኦስካር ሽልማት አግኝታለች።
በሴት ረዳት ተዋናይ ዘርፍ ደግሞ ደቡብ ኮሪያዊቷ ዩህ-ጁንግ ናት ሽልማቱን መውሰድ የቻለችው።
የዘንድሮው ኦስካር ሽልማት ሎስ አንጀለስ ውስጥ ባለ አንድ ግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ሰዎች ዘርዘር ብለው ተቀምጠው ነው የተከናወነው።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ ዕጩዎች ደግሞ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አዳራሽ ነው የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱን የተከታተሉት።
በሁለቱም አዳራሾች ውስጥ ያልታየው ሰር አንተኒ ሆፕኪንስ 'ዘ ፋዘር' በተሰኘው ፊልም ነው ሽልማት ያገኘው።
'ሳይለንስ ኦፍ ዘ ላምብስ' በተሰኘው ቀደምት ፊልሙ ከ25 ዓመታት በፊት የኦስካር ሽልማት ያገኘው ሆፕኪንስ አንድ የማስታወስ ችግር ያለበት አባት ሆኖ በተወነበት ፊልሙ ሁለተኛ ኦስካሩን አግኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምርጥ ወንድ ተዋናይ በተሰኘው ዘርፍ ሟቹ ተዋናይ ቻድዊክ ቦስማን ያሸንፋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
የዌልስ ዜግነት ያለው ሆፕኪንስ ማሸነፉ ብዙዎች ያልጠበቁት ነበር። ለዚህም ይሆናል ተዋናዩ በሁለቱም አዳራሾች ያልተገኘው።
ሌላኛው የምሽቱ መነጋገሪያ የነበረው 'ኖማድላንድ' ዳይሬክት የተደረገው ቻይና ተወልዳ፣ እንግሊዝ ተምራ አሜሪካ በምትኖረው ዣዎ ነው።
ዣዎ በታሪክ ኦስካር ያሸነፈች ሁለተኛዋ ሴት ዳይሬክተርና የመጀመሪያዋ ነጭ ያልሆነች ሴት በመሆን ታሪክ ፅፋለች።
በምሽቱ ኖማድላንድ 3 ሽልማቶችን፣ ዘ ፋዘር፣ ጁዳስ ኤንድ ዘ ብላክ መሳያህ፣ ማ ሬይኒ፣ ማንክ፣ ሶል እንዲሁም ሳውንድ ኦፍ ሜታል እያንዳንዳቸው 2 ሽልማቶችን አሸንፈዋል።
የ32 ዓመቱ የለንደን ነዋሪ ዳንኤል ካሉያ ጁዳስ ኤንድ ዘ ብላክ መሳያህ በተሰኘው ፊልም ላይ ባሳየው ብቃት ነው ኦስካር የተቀዳጀው።
ዩህ-ጁንግ ዩን ኦስካር ያገኘች የመጀመሪያዋ ደቡብ ኮሪያዊት ሆናለች።
በወጣትና ተስፋ ያላቸው የሲኒማ ሴቶች ዘርፍ እንግሊዛዊቷ ኤሜራልድ ፌኔል አሸናፉ ሆናለች።
የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከወትሮው በሁለት ወራት ዘግይቶ ነው የተከናወነው። ተዋንያኑ በአዳራሾቹ ዘርዘር ብለው ይቀመጡ እንጂ አብዛኛዎቹ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አላደረጉም ነበር።
















