ለአንድ የውሻ ዘር ብሔራዊ በዓል ያወጀችው አገር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቱክሜኒስታን ትባላለች። የቀድሞ የሶቭየት ኅብረት አካል ነበረች። በመካከለኛዋ እሲያ የምትገኝ በተፈጥሮ ጋዝ የታደለች አገር ናት። ቱክሜኒስታን አሁን አዲስ የብሔራዊ በዓል አውጃለችው። በዓሉ ለአንድ ውሻ ዝርያ ክብር የታወጀ ነው።
በዲሞክራሲ መብቶች አፈናና በሙስና ስሟ ተደጋግሞ ይነሳል።
ቱክሜኒስታን አሁን አዲስ የብሔራዊ በዓል አውጃለችው። በዓሉ ለአንድ ውሻ ዝርያ ክብር የታወጀ ነው።
የውሻ ዝርያው ስም አላባይ ይባላል። የሼፔርድ ውሻ ዓይነት ሲሆን በዚያች አገር ለብዙ ዓመታት ብርቅዬ ዝርያ ተደርጎ የሚወደድ ነው።
ትናንት እሁድ ልዩ የእውቅና በዓል ተደርጎለታል። ሽልማትም ተበርክቶለታል።
ፕሬዝዳንት ጉባንጉሊ በርዲሙካሜዶቭ የዚህን አላባይ ውሻ በብሔራዊ ደረጃ መወደስ አስፈላጊነትን ያንቆለጳጰሱ ሲሆን ውሻው ብሔራዊ ኩራታችን ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቱክሜኒስታን ይህ አላባይ ውሻ ብቻ ሳይሆን አሃል ቴክ ፈረስ ዝርያም የብሔራዊ ኩራት መገለጫ ነው።
ትናንት እሁድ ለአላባይ ውሻ ዝርያ ልዩ ክብረ በዓል ተሰናድቶ ነበር።
የአላባይ ውሾች የቁንጅና ውድድርም ተደርጓል።
የአላባይ ውሾች ቁንጅና ውድድርን ተከትሎ ደግሞ ብልህና ቀልጣፋ ውሾች ውድድርና የእውቅና የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል።
የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በርዴሙካመዶቭ በድንበር አካባቢ በጥበቃ ታማኝና ጀብዱ ለፈጸመ ውሻ የአገሪቱን ትልቅ ሜዳሊያ ሸልመውታል።
ይህን ሜዳሊያ ለርዕሰ ብሔሩ ያቀበሉት ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ወንድ ልጅና የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሰርዳር በርዲሞካመዶቭ ናቸው።
በውቧ የቱክሜኒስታን ዋና ከተማ አሽጋባት የተገነባው የዚህ ውሻ ዝርያ ማራቢያ ማዕከልም በፕሬዝዳንቱ ተመርቋል።
አላባይ ውሾች በቱርከሜኒስታን እጅግ ተወዳጅና በእረኞች ዘንድ የሚዘወተሩ ሲሆኑ በዓለም ውሾች ዝርያም ግዙፎቹ ናቸው። አንድ የአላባይ ውሻ በአማካይ እስከ 80 ኪሎ ይመዝናል።
ባለፈው ዓመት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በርዲሙካመዶቭ 6 ሜትር ቁመት ያለው ከወርቅ የተሠራ የውሻ ሐውልት በዋና ከተማዋ አደባባይ መርቀዋል።
ዋና ከተማዋ አሽጋባት በርካታ የውሻና የፈረስ ሐውልቶች አሏት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አምባገነን ናቸው፣ ተቀናቃኝ የላቸውም የሚባሉት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚስተር በርዴ ሙካመዶቭ የየትኛውንም አገር መሪ ሲጎበኙ የውሻ ወይም የፈረስ ስጦታን ይዘው ነው የሚሄዱት።
በጎርጎሳዊያኑ 2017 ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን አላባይ ውሻን በስጦታ ባበረከቱበት ወቅት ድንክየውን ውሻ በማጅራቱ በኩል አንጠልጥለው በእንዝላልነትና ርህራሄ በጎደለው አኳኋን ለፑቲን ማስረከባቸው እጅግ ሲያስተቻቸው ነበር።
ቅጽበቱም በቪዲዮ በመላው ዓለም ተዛምቶ ሚሊዮኖች ከፍ ዝቅ አድርገዋቸው የዓለም መሳቂያ ሆነው ነበር።
ስጦታውን የተቀበሉት ቪላድሚር ፑቲን ግን አላባይ ድንክ ውሻውን በፍቅር አቅፈው መቀበላቸው በአንጻሩ ውዳሴን አስገኝቶላቸው ነበር።












