ባለሙያዎች በኮቪድ ምክንያት የጠፋን የማሽተት ስሜት ለመመለስ 'የማሽተት ሥልጠና' ውሰዱ አሉ

ወጣት ሴት የናና ቅጠል ስታሸት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮቪድ-19 መያዛቸውን ተከትሎ የማሽተት ስሜታቸውን በፍጥነት መመለስ ያልቻሉ ሰዎች የማሽተት ሥልጠና እንዲወስዱ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ሰጡ።

ባለሙያዎቹ የማሽተት ስሜትን ለመመለስ የስትሮይድስ ህክምና ከመከታተል ይልቅ 'የማሽተት ስልጠና' መውሰዱ የተሻለ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህ የማሽተት ስልጠና ለወራት የተለያዩ ሽታዎችን በማሽተት አእምሮን እንደገና በማሰልጠን የተለያዩ ሽታዎችን እንዲለይ የማድረግ ሂደት ነው።

የዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚለው የማሽተት ስልጠና ዋጋው ርካሽ እና ሂደቱም ቀላል ነው።

ከስቴሮይድስ ሕክምና ጋር ሲነጻጸርም፤ የማሽተት ስልጠናው የጎንዮሽ ጉዳቶች የሉትም።

ከትኩሳት እና ከማያቋርጥ ሳል በተጨማሪ የመሽተት እና የጠዓም ስሜት ማጣት ከኮሮናቫይረስ ዋና ዋና ምልክቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ማሽተት አለመቻል ብዙውን ጊዜ ሕመሙ ካለፈ በኋላ በፍጥነት ይመለሳል። ሆኖም ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ከህመሙ ከስምንት ሳምንት በኋላም የማሽተት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል።

የኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ ኖርዊች የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባው ፕሮፌሰር ካርል ፊልፖት እንደሚሉት ኮርቲኮስትሮይድስ ማሽተትን የመመለስ አቅሙ በጣም ጥቂት ነው።

"የታወቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሉት ከቫይረሱ በኋላ በሚመጣ የማሽተት ስሜት ማጣትን ለማከም መታዘዝ የለባቸውም ብለን እንመክራለን" ብለዋል።

"እንደ ዕድል ሆኖ በኮቪድ-19 የተነሳ ሽታ ማጣት የሚገጥማቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች በፍጥነት የማሽተት ስሜታቸውን መልሰው ያገኛሉ" ብለዋል።

ከስቴሮይድ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል የደም ግፊት እና የስሜት መለዋወጥ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።

ዓለም አቀፍ የአለርጂ እና ሪህኖሎጂ ኦረም መጽሔት ላይ በወጣው ጽሑፍ መሠረት ተመራማሪዎቹ "የማሽተት ሥልጠና"ን በአማራጭነት አቅርበዋል።

ይህም ተለይተው የሚታወቁ እና በቀላሉ የሚለዩ ሽታ ያላቸውን አራት ነገሮችን ማሽተትን ያካትታል። ለምሳሌ ብርቱካን፣ አዝሙድ፣ ነጭ ሽንኩርት እና ቡናን በቀን ሁለት ጊዜ ማሽተት።

ፕሮፌሰር ፊልፖት እንዳሉት ጥናቶች 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ከስድስት ወር በኋላ የማሽተት ስሜታቸውን ሙሉ በሙሉ መልሰው ያገኛሉ።

በዚህ ጊዜ ካልተመለሰ ግን አእምሮ ሽታ እንዲለይ እና የተለያዩ ሽታዎችን እንደገና እንዲያውቅ "የማሸተት ስልጠና" ይረዳል።