ምርጫ 2013፡ 18 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪ ተመዝግቦበታል የተባለው ምዝገባ ተራዘመ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ምርጫ ከ18 ሚሊዮን በላይ መራጮች ቢመዘገቡም የመራጮች ምዝገባ ጊዜን ማራዘሙን አስታወቀ።
ቦርዱ በመጪው ግንቦት መጨረሻ ለሚደረገው ምርጫ ሲካሄድ የነበረው የመራጮች ምዝገባ ጊዜ መራዘሙን ያስታወቀው ትናንት ባወጣው መግለጫ ነው። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ ባስቀመጠው ግምት መሰረት 50 ሚሊዮን ሰዎች በመራጭነት ይመዘገባሉ ብሎ ነበር።
አስከ ሐሙስ ሚያዝያ 14/2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚልዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን 41,659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከመጋቢት 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው የመራጮች ምዝገባ አርብ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ነበር።
ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች መስተጓጎል በመግጠሙ ምክንያት ምዝገባው ተጀምሮ ሲካሄድባቸው በነበሩ አካባቢዎች እንደየሁኔታው ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ቦርዱ ወስኗል።
ባለፈው ሳምንት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እንደተናገሩት በተለያዩ ክልሎች ተከፍተው ድምጽ ሰጪዎችን ይመዘግባሉ ተብለው ከታቀዱት 50 ሺህ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ምዝገባ እያካሄዱ የነበሩት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
በተጨማሪም በሶማሌና በአፋር ክልሎች ውስጥ የመራጮች ምዝገባ እጅጉን ዘግይቶ ነው የተጀመረው።
የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ የተመዘገቡት ድምጽ ሰጪዎች ቁጥር የተጠበቀውን ያህል እንዳልነበረ ተገልጾ የነበረ ሲሆን በመጨረሻው ሳምንት ላይ የተመዝጋቢዎች አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ቀን አርብ መጠናቀቁን በማስመለከት ያጋጠሙ ችግሮችን በመመርመር የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም ቦርዱ ወስኗል።
በዚህም መሰረት ምዝገባው ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ አስከ ግንቦት 06/2013 ለሦስት ሳምንታት ተራዝሟል።
በተለያዩ ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ በተስተጓጎለባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ለሁለት ሳምንት በመራዘሙ ምዝገባው ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
በተጨማሪ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እና የጸጥታ ችግር አለባቸው ባለባቸው የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ የመራጮች ምዝገባን ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።
በሆሮ ጉድሩ፤ አሊቦ፣ ኮምቦልቻና ጊዳሚ፤ ምሥራቅ ወለጋ፤ አያናና ገሊላ፤ ምዕራብ ወለጋ፤ ቤጊና ሰኞ ገበያ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ "አሁንም የማይጀመር" መሆኑ ተገልጾ፤ ነገር ግን በሌሎች ወረዳዎች የመራጮች ምዝገባን ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ከሰጎን ወረዳ በስተቀር የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ እንዲሁም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች የተቋረጠው የመራጮች ምዝገባ የሚጀመርበትን ሁኔታ ቦርዱ እንደሚያሳውቅ አመልክቷል።
ምርጫ 2013
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ፤ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው በዚህ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ማለትም ከአገሪቱ ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ድምጽ በመስጠት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በምርጫው ከሚሳተፉት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማቅረብ በኩል ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ቀዳሚ ደረጃን ይዟል። ከብልጽግና በመከተል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ ናቸው።
ሦስቱን ፓርቲዎች ጨምሮ በምርጫው ለመወዳደር በፓርቲና በግል ለመወዳደር ከስምንት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።















