"ፖለቲከኞች የሶማሌን ሕዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ አያስቡትም" የኦብነግ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ መሐመድ

አቶ አህመድ መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB

ከሦስት ዓመታት በፊት ለውጡን ተከትሎ ለሰላማዊ ትግል ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው። ቢቢሲ ስለ ምርጫና ስለ ፓርቲው እንቅስቃሴ ከኦብነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌደራል መንግሥት ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ ጋር ቆይታ አድርጓል።

Short presentational grey line

ስለኦብነግ እምብዛምም ከማይታወቁ ነገሮች እንጀምር። አፈጣጠሩ ከዚያድባሬ ወረራ ጋር የሚያያዝ ታሪክ አለው። በሽግግሩ ጊዜ ተሳትፋችኋል። ከምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር ወጣት ሊግ ነው ኦብነግ የተፈጠረው ይባላል። ክልሉን ለሁለት ዓመት ያህል አስተዳድራኋል። ልክ ነኝ?

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የተመሰረተው (እአአ) ነሐሴ 15 ቀን 1984 ነው። በወቅቱ የነበረው የምዕራብ ሶማሌ ነጻ አውጭ ግንባር (WSLF) በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረችው ሶማሌዎች በሚኖሩበት አገር ከተዳከመ በኋላ የግንባሩ ወጣቶች ዘርፍ የነበሩ አባሎች ተሰባስበው የመሠረቱት ግንባር ነው።

የምዕራብ ሶማሌ ነጻ አውጭ ግንባር በኢትዮጵያ ሶማሌዎች የተቋቋመው ነው። ሆኖም በሶማሊያ መንግሥት ይደገፍ የነበረ ድርጅት ነበር።

ወጣቶቹ ተሰባስበው፣ ተጠያይቀው ትግላችን እየተዳከመ ስለሆነ ምን እናድርግ በማለት የመሠረቱት ድርጅት ነው- ኦብነግ። እነዚህ ወጣቶች ትግላቸው ከሶማሊያ መንግሥት ነጻ አለመሆኑንና ጣልቃ ገብነት እንዳለው ተረድተው የመሠረቱት ነው።

ኦብነግ በሶማሊያም በኢትዮጵያም ክልክል ስለነበርና ተቀባይነት ስላልነበራቸው በድብቅ ለዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት አቶ አብዱረህማን መህዲ ነበሩ ሊቀመንበር። ከዚያም መሐመድ አብዲ መገኒ ለሁለት ወር ያህል ሊቀመንበር ሆነዋል። ከዚያም አቶ ሼህ ኢብራሂም አብደላህ ቋሚ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ድርጅቱን ለረዥም ጊዜ መርተዋል። እርሳቸው አሁን በሕይወት የሉም።

የኦብነግ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሶማሌዎች ኦጋዴን ተብሎ የሚጠራውን አገር ነጻ ማውጣት ነበር።

የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የኦብነግ መሪዎች እና ኃላፊዎች አገር ውስጥ ገብተው በመጎብ ዞን፣ ገርቦ በምትባል ወረዳ ሕዝብ ሰብስበው፤ ብሔራዊ ውይይት አድርገው ሸህ ኢብራሂም አብደላ እንደገና ተመርጠው በሽግግር መንግሥቱ ተሳትፏል።

በመጀመሪያው ምርጫም ተሳትፎ በ84 በመቶ ድምፅ አብላጫ ድምጽ አግኝተው በክልሉ መንግሥት መሥርተዋል። ኢህአዴግ/ሕወሓት ምን ዓይነት የሕዝብ ድጋፍ፣ ዓለማና አቋም እንዳለን ካየ በኋላ ግን ወረረን። በዚህ ምክንያት ለትጥቅ ትግል ጫካ ተገባ፡፡ ፍላጎታችን በዲሞክራሲ መሳተፍ ነበር፤ ተገደን፣ ተገፍተን ጫካ ገባን።

ለምን ያህል ጊዜ ነው ክልሉን?

ለተወሰነ ጊዜ ነበር። አንድ ዓመት ከአሥር ወር ገደማ አስተዳድረናል። አሁን ያለው የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁም እስካሁን ያለው በሶማሊኛ የተጻፈ መርሐ ሥርዓተ ትምህርት [ካሪኩለም] በኦብነግ በተመራው ክልላዊ መንግሥት ነበር የተጀመረው።

መሠረታዊ የሆኑ ሥራዎችን ከጀመርን በኋላ የሕዝብ ድጋፋችን በጣም ከፍተኛ ስለነበር ጦርነት ተከፈተብን። ኃላፊዎችን መግደል ጀመሩ በዚህ ምክንያት ወደ ጫካ ገባን።

ላለፉት 36 ዓመታት የቆየ አንጋፋ ድርጅት ነው። በዋናነት ለራስ ገዝ [self determination] ሲዋጋ የኖረ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ለውጡን ተከትሎ በተደረሰ ስምምነት ወደ አገር ቤት መጥታችኋል። ነገር ግን አሁንም ስማችሁ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ነው። እንዴት ይህን ስም ይዛችሁ ትቀጥላላችሁ? በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ስሜት ይሰጣል?

ጥሩ ጥያቄ ነው። በለውጥ ስማችን አይለወጥም። በሕዝብ ፍላጎት ነው ይህ ስም የተሰየመው። አቋም የያዘውም በሕዝብ ፍላጎት ነው። ዝም ብሎ በመሪዎች፣ በሁለት. . . በሦስት. . . በሃምሳ በመቶ ሰዎች የሚወሰን አይደለም።

የመገንጠልም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ የሚወሰነው በሕዝብ ድምፅ ነው። ይህ ሕዝብ ምን ዓይነት ድርጅት እንደሚፈልግና ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ ድርጅቱ የሚወሰነው በሕዝብ ድምፅ ነው። እኛ ከለውጡ ሰዎች ጋራ ስለተግባባን የድርጅቱን ስም፣ አቋምና ዓላማ መለወጥ አንችልም። እንደዚህ ዓይነት ባህርይም የለንም።

በሕዝብ የተቋቋመ ድርጅት፣ ለሕዝብ የተቋቋመ ዓላማ ስለሆነ፤ አንቀይርም። መቀየርም አንችልም። ሕዝብ ተጠይቆ፣ ተሰብስቦ፣ ብሔራዊ ስብሰባ ተካሂዶ ነው ዓላማችን የሚቀየረው።

የኢትዮጵያ መሪዎች ደግሞ ሕዝብን የመሳብ ጠባይ ካላሳዩ ዝም ብሎ በቀላል የሚቀየር ነገር አይደለም።

ታዲያ ኮንፈረንሱን የማታደርጉት ለምንድን ነው? የመቀየር ጊዜው አሁን አይደለም ብላችሁ ስለምታምኑ ነው? ነጻ አውጭ ግንባር ብሎ ራሱን ከማዕከላዊ መንግሥት ለመገንጠል የሚያስብን ድርጅት ስም ይዞ ከሌሎች ፓርቲዎችስ ጋር እንዴት ነው የምትሠሩት?

እኔ ግራ የገባኝ፣ እኔ ግራ የሚገባኝ ይሄ ጥያቄያችሁ ነው። ብዙ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ይሄን ጥያቄ ሲጠይቁኝ ቆይተዋል። የመገንጠል [self determination] ጉዳይ ብዙ ጋዜጠኞች …፤ ምንድነው ችግራችሁ? ከዚህ ነጥብ ማለፍ ያቃታችሁስ ለምንድነው?

እንዴ! የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ራሱ እስከ መገንጠል ይፈቅዳል። ለምን ይሄ ነገር ለጋዜጠኞች ራስ ምታት (stress) ሆነባችሁ? ለምን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይዋጥላችሁ ቻለ? ለምን ይሄ ነገር ጉሮሯችሁ ውስጥ ተቀርቅሮ እንደቀረ እኔ ግራ ገባኝ።

ሕጋዊ የሆነ ነገር ነው፤ ሕዝብ ይሆንልኛል ባለው መሄድ አለበት። ኢትዮጵያ ከሆነችላቸው በኢትዮጵያዊነት መቆየት ይችላሉ፤ ካልሆነችላቸው ደግሞ የራሳቸውን መንግሥት መፍጠር ይችላሉ። ይህ በዓለም ሕግጋትም ያለ ነው።

በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥት ያለ ነው። ለምን ደግማችሁ ደጋግማችሁ የእኛን ድርጅት ይሄን ጥያቄ እንደምትጠይቁ ግራ ይሆንብኛል። ጋዜጠኞች ግን ከዚህ ጥያቄ ማለፍ ለምን አቃታችሁ?

ከዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ዋና ፀሐፊያችሁ አቶ አብዱራህማን መህዲ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ላይ "ሶማሌ በማዕከላዊ መንግሥቱ የተናቀና የተረሳ ክልል ነው። እኛ ኢትዮጵያዊነት አይሰማንም፤ በቅኝ ነው ማዕከላዊ መንግሥቱ የያዘን" ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ቀደም ሲል ያለ ስሜት ነው። ከለውጡ በኋላ ይህ ስሜታችሁ በምን ያህል መጠን ተፈውሷል?

በእርግጥ ይህ የመሪዎች ስሜት ሳይሆን የሕዝብ ስሜት ነው። እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ የእኛ ሕዝብ፣ የሶማሌው ሕዝብ፣ የኦጋዴኑ ሕዝብ የእኔ መንግሥት የሚል ስሜት አሁንም ያለው አይመስለኝም።

ምክንያቱም መንግሥት የራስ የሚሆነው ስለ ራስህ ሲያስብ ነው። ከአጤ ቴዎድሮስ፣ ከአጤ ምንሊክ፣ ከአጤ ኃይለ ሥላሴ፣ ከኮሎኔል መንግሥቱ እና አቶ መለስ ዜናዊ እስከ ዛሬ ድረስ የሶማሌ ሕዝብ ምን ተደረገለት? ምንስ ይደረግ ነበር?

የሶማሌ ሕዝብ በፌደራል መንግሥት ምን ያህል ተሳትፎ ተሰጣቸው? ወይም ምን ያህል ጥቅም አገኙ? እንዴትስ ነው የሚታዩት? ዛሬ እኮ የኢትዮጵያን ብር እና የኢትዮጵያን መንግሥት የማያውቁ ሰዎች በክልላችን ውስጥ አሉ። ይሄ ምን ይነግርሃል?

ለምን? በምንድን ነው የሚገበያዩት ታዲያ?

ለምን? መንግሥት ስላልደረሳቸው ነዋ።

የሶማሌ ሕዝብ ወታደር ተልኮ፣ ወታደር ሲጨፈጭፋቸውና ሲገድላቸው ነው የሚያውቁት።

ይህን ነገር መቀየር ያለብን እኛ ሳንሆን የኢትዮጵያ መንግሥትና መሪዎች ናቸው።

እኔ ልንገርህ ለምሳሌ…በቅርቡ በፌደራል የተዘጋጀ ውይይት ላይ በቢሾፍቱ ተሳትፌ አንድ ሰው ምን ብሎ ጠራኝ መሰለህ።

በውይይት ላይ ነው የምልህ…አንድ ሰው "ወንድሜ ሶማሌው እንደገለፀው" ይለኛል። ተመልከት እንግዲህ!

ምንድነው ችግሩ ታዲያ፣ አልገባኝም?

እኔ በማንነቴ እኮራለሁ ችግር የለብኝም። ግን ለምሳሌ ሌላው ተሳታፊ የኦሮሞው ወንድሜ፣ የሃዲያው፣ የጉራጌው እየተባለ በብሔሩ ተሰይሞ ስሙን ከብሔሩ ጋር አያይዞ አልተነሳም። ወንድሜ ኦሮሞው፣ ወንድሜ ሃዲያው አልተባለም። እኔ ለምን ልዩ ሆንኩ? ይህ ምን ያሳይኻል?

ይህንን መቀየር ያለብን ደግሞ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መሪዎች ናቸው። ይህ ልዩነት ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ያለ ነው። እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚያዩን። ፖለቲከኞች የሶማሌን ሕዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አያስቡትም።

ይህንን አለ የምትሉትን የተንሸዋረረ አመለካከት ለማቃናት እናንተስ እንደ አንድ ፓርቲ ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል ብዬ ለጥይቅዎ?

ከጥንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያዊ መሆናችን አልቀረም።

በድርጅት ብቻ ሳይሆን በሶማሌ ባለሥልጣናት እንደ ሶማሌ ብሔረሰብ ተወያይተው በመሆኑም ድርሻችን ምን ያህል መሆን እንዳለበት መወያየት አለብን።

ትልቁ ሚና መጫወት የነበረባቸው በሥልጣን ላይ ያሉ የሶማሌ ባለሥልጣናት ነበሩ። ምን እንዳጡ፣ ምን እንደሚያንሳቸው መጠየቅ ነበረባቸው።

እኛ እንደዚህ ብለን ስንጠይቃቸው እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የሚያዩን። በመሆኑም ለዚህ ከፍ ያለ ሚና መጫወት ያለባቸው በሶማሌ ክልል ያሉ ባለሥልጣናት ነበሩ።

እኛ ተወያይተን ምን ማድረግ እንዳለብን ለመወሰን እንደ የቤት ሥራ እናስብበታለን። ድርጅታችንም ያስብበታል። በዚች አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለን ድረስ የድርሻችንን ማግኘት አለብን። የድርሻችንን መጫዎች እና የድርሻችንን መካፈል አለብን የሚል እምነት ነው ያለን።

በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ አፋሩም፣ ሐረሪውም ፣ ሶማሌውም፣ ደቡቡም . . . እኔ ተገፍቻለሁ፤ እኔ እንደ ኢትዮጵያ አልቆጠርም እኔ ሁለተኛ ዜጋ ነኝ እያለ ነው። ይህ የስሜት መጎዳት ሁሉም ሕዝብ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ሁሉም አኩራፊ ከሆነ እንዴት ነው ኢትዮጵያን መጠበቅና ወደፊት ማራመድ የሚቻለው? እኔ ተጎድቻለሁ የሚለው ሕዝብስ ወደ መሀል መምጣትና የድርሻውን መወጣት የለበትም ወይ? ይህ ስሜት የማይሰማውስ ብሔር አለ ወይ ኦሮሞው፣ ወላይታው፣ አማራው፣ ሲዳማው . . .

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው።

በዓለም ላይ እኔ ነኝ ጎጂው፣ እኔ ነኝ በዳዩ፣ እኔ ነኝ አጥፊው የሚል ሰው የለም። ጎጂውም ተጎጂውም እንደዛ ነው የሚቀጥሉት።

ባለፉት ሥርዓቶች ምን ዓይነት ችግሮች ነበሩ ብለን እንደ አንድ አገር ዜጋ ተወያይተን፣ ስህተታችንን ተጠያይቀን፤ እርቅ ተቀብለን፤ ወደፊት ምን ይሻለናል? ማለት አለብን ብዬ አንስቻለሁ።

ነገሩ የአዞ እንባ እንዳይሆን፤ ማን ነው ይህን የሚያመጣው? ሥርዓቶቹ ናቸው። በመለስ ዜናዊ አስተዳደር የህወሓት፣ የትግራይ ጊዜ ይባላል። በደርግም ጊዜ የአማራው ጊዜ ይባላል። እነርሱም ግን ተበድለናል እያሉ ነው።

ስለዚህ ቆሻሻችንን ከመቆፈር አሁን ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ላይ መምጣት ያስፈልጋል። መጀመሪያ ይቅርታ መጠያየቅ፣ ሕዝብን ማስተማር፣ መቻቻልና፥ አንድ ሰው ተበድያለሁ ካለ ይቅርታ ማለት ያስፈልጋል።

አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ሥነ ሥርዓት ተከባብረን እየተጓዝን፤ ጥያቄዎች ካሉ በሕጋዊ መሠረት እንዲፈቱ፣ ማንኛውም የወደፊት ዕጣ በሕጋዊ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ነው የማስበው። እኛም እንደዛ ዓይነት አቋም ነው ያለን።

ይቅርታ መጠያየቅ ላይ ብዙዎች ጥያቄ የላቸውም። ጥያቄው ይቅርታ የሚጠይቀው ማን ነው? የሚጠየቀውስ ማን ነው? አጥፊው ማነው? ተጎጂው ማነው? የሚለው ነው። የደርግ መንግሥት ብለዋል ደርግ የትኛውን ብሔር ነው የሚወክለው? ከዚያ በፊት ያሉ አስተዳደርና መንግሥታትን ስንቆጥር የትኛውን ብሔር ነው የምናነሳው? የመሪውን ብሔር ነው የምናነሳው? የወከሉት ሕዝብስ ራሱ ሲበደል አልነበር ወይ?

እውነት ብለሃል። በተወሰነ መልኩ ካነሳኸው ነጥብ ጋር እስማማለሁ። ምክንያቱም በሥልጣን ላይ የነበረ ሰው ወይም ሰዎች ናቸው ሥርዓቱን ያጠፉት ይባላል። እውነት ነው የአማራ ሕዝብ ተሰብስቦ የሶማሌን ሕዝብ እንበድል አላለም። የትግራይም ሕዝብ እንደዚያው ተነስቶ የሶማሌ ሕዝብ ወይም ሌላውን እንበድል ብሎ አልተነሳም።

ግን በመለስ ዜናዊ ጊዜ አራት ድርጅቶች ነበሩ። በኢህአዴግ ሥር የተሰበሰቡ ድርጅቶች። ነገረ ግን ብዙ ጊዜ ሰው ሲናገር በህወሓት የተመራው መንግሥት ነው የሚለው? በህወሓት እነማን ነበሩ ሲባል ትግራዮች ነበሩ እንላለን።

በደርግ ጊዜም እነማን ነበሩ ሲባል የአማራው ነበሩ ይባላል።

ያው በተወሰነ ደረጃ ካንተ ጋር እስማማለሁ ምክንያቱም ሥርዓቱ ነበር አጥፊው። በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ከሥርዓቱ በስተጀርባ የትኛው ብሔር ነበረ?

አፍሪካዊያን እኮ ብሔርተኞች ነን ሁላችንም። ይህንን መካድ አንችልም። ኬንያ ብትሄድ ተመሳሳይ ነገር ነው ያለው። ኬንያ ብታነሳ የኪኩዩ መንግሥት ነው የምትለው። እዚህም እንደዛ ዓይነት ነገር አለ። እና መካድ የለብንም፡፡ ይህን መቀበል አለብን ብዬ አስባለሁ።

ከአራት ዓመታት በፊት ሊቀመንበራች አቶ አብዱራህማን መኽዲ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በመቶ ዓመት ውስጥ ኦጋዴን ውስጥ አንድ ሃይስኩልና አንድ ሆስፒታል ነው ያለን። ሴቶቻችን ሊወልዱ ሲሉ ወይም ሲታመሙ ሞቃዲሹ ነበር የሚሄዱት" ብለዋል። በአንጻሩ ሶማሌ በተለይም ሰፊ ድጋፍ ባላችሁ ኦጋዴን በጋዝ ሃብት ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና ትልቅ ሃብት ያለው አካባቢ ነው። አሁን ሕዝባችሁ በልማት እየተጠቀመ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? በዚያ አካባቢ ባለው እንቅስቃሴ ተስፋ ይታያችኋል?

ተስፋ አለን። እንደ እንድ ሙስሊም በቁርዓን ላይ (ላ ታቅናጡ ቢራሕማቲላህ) "በፈጣሪ ፀጋና ሲሳይ ተስፋ አትቁረጡ" የሚል አንቀጽ አለ።

ሁልጊዜም ተስፋ አለን። ምንም እንኳ ብንተችም አሁን ያለው የሶማሌ አስተዳደር በመጠኑ እያደረገ ነው። ጥሩ ነው። ትምህርት ቤቶች በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም በመጠኑ እየተሠሩ ነው፤ ከዚህ በላይ መሆን ነበረበት ማለታችን ባይቀርም ማለቴ ነው።

ይህ ማለት ግን እንዳትሳሳት። አሁንም በእሳት ብርሃን (በኩራዝ ብርሃን) የሚወልዱ የሶማሌ እናቶች አሉ። ከ60 በመቶ በላይ የሶማሌ ሴቶች አሁንም እንደዚያው እየወለዱ ነው ያሉት። ጥራታቸው ዝቅተኛ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች አሉ። ጥራታቸው በጣም ዝቅተኛ ቢሆኑም ሆስፒታሎችም ክሊኒኮችም በመጠኑ አሉ። እየተሠሩም ነው።

ወደፊትም እንዲሠራ፣ እኛም ካሸነፍን ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው ይህንን ነው። ሌላም ቢያሸንፍ መሠረታዊ የሆኑት እነዚህ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት እናምናለን።

የጋዝ ሃብቱ ላይ የምታነሱት የተለየ ጥያቄ አለ?

አንድ የሶማሌ ተረት አለ። "Dhariba ninkii u dhow baa dhuunigiisa leh" ጭብጡ ምንድነው? "ምግብ ሲበስል ለቀረበው ሰው ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት" የሚል አባባል ነው።

የሶማሌው ሕዝብ ከጋዝና ነዳጅ ንብረቱ እንደዚህ ሩቅ መሆን የለበትም። የተሰጠው ድርሻም በቂ አይደለም ብለን እናምናለን። ከዚያ በላይ ነው ማግኘት ያለባቸው ብለን እናምናለን።

በፌደራል መንግሥት ያላቸው ድርሻም በቂ አይደለም እንላለን። የፌደራል ሃብትም የሚደርሳቸው ከዚያ በላይ ማግኘት አለባቸው ብለን እናምናለን።

አቶ አብዱራሕማን እንዳሉት ሕዝባችን ድሮም በጫካ ያለ ሐኪምና መድኃኒት ሲሞት እንደነበረው አሁንም እየሞተ ነው ያለው። ይህ ግን በእኛም ይሁን በሌላ እንደዚህ ሆኖ መቀጠል የለበትም ብለን እናምናለን።

እናንተ ጫካ በነበራችሁበት ዘመን የሶማሌ ሕዝብ በቀድሞ የሶማሌ አስተዳዳሪ አቶ አብዲ ኢሌ ቁም ስቅሉን ሲያይ እንደነበረው እናንተም ፍዳውን ስታበሉት ነበር። አሁን አቶ ሙስጠፌ ከመጡ ወዲህ ግን ክልሉ ከሌሎች ክልሎች አንጻር ብዙም ኮሽታ የሌለበት፣ ሰላም ያለበት እንደሆነ ነው የምናየው፤ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌም በዚህ የሚሞካሹ ናቸው። እናንተ እንዴት ነው የምትገመግሙት?

አቶ ሙስጠፌ ከመጣ ሰላም መጣ ከማለት እናንተ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ከፈረማችሁ በኋላ ሰላም መጣ ብትሉ ይመረጣል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም አቶ ሙስጠፌ እኛ አዲስ አበባ እያለን፤ እኛ የሰላም አቅጣጫ ከመንግሥት ጋር ከተስማማን በኋላ ነው የተሾሙት።

ሰላም በአቶ ሙስጠፌ አሊያም በብልጽግና ፓርቲ ሳይሆን፤ በእኛና በኢህአዴግ ነው የተፈፀመው። ሰላም በኦብነግ ነው የመጣው፤ ሰላም በእኛ ውሳኔ ነው የመጣው ብለን እናምናለን።

ምክንያቱም ከመንግሥት ጋር ስንፋለም ነበር። እኛ እስከተፋለምን ድረስ 'እነሱን ሕዝብ ይደግፋቸዋል' በሚል ሕዝብ ሲጨፈጭፉ ከእኛም ጋር ሲዋጉ ነበር። አቶ ሙስጠፌ በመሀል ገብቶ ነው እንጂ በእርሱ ሰላም አልመጣም። በእኛ ነው ሰላም የመጣው።

አሁንም በእኛ ካልሆነ በሰላም አይቆይም ነበር። ምክንያቱም ድርጊታቸው፣ ጸባያቸው፣ አነጋገራቸው እና ሁሉ ነገራቸው ወደ ሰላማዊ የሚወስደን አይደለም ብዬ አምናለሁ። ሰላም በእኛ ነው የመጣው፤ በእኛ ነው የተመሠረተው። አሁንም በእኛ ነው ያለው።

ነገር ግን ሰላም ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ጥሩ ነው። የሕዝባችን ውሳኔ ነው። ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ዜጋ ሆነው በያሉበት ቦታ እየተገደሉ ነው። ሶማሌው የሰላምንም የጦርነትንም ዋጋ ስለሚያውቅ፤ እኛ ስለወሰንን ነው ዛሬ ሰላም የሆነው። ዛሬ የሰላም ቀን ነው።

የፈለግነውን በሰላም እንፈልግ ከሌሎች ጋር በሰላም እንወያይ፣ በሰላም እንሂድ ብለን የኦብነግ ውሳኔ ስለሆነ ነው በዚያ እየሄድን ያለው። አሁንም እንቀጥላለን። ሰላም ለሕዝባችን ለአፍሪካ ቀንድም እንዲወርድ አላህን እንጠይቃለን።

እናንተ ጫካ በነበራችሁ ጊዜ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ፤ አንዳንድ የፈጸማችኋቸው ጥቃቶች አሉ። ግንቦት 2007 እአአ 65 ኢትዮጵያያዊ የጉልበት ሠራተኞች እና ዘጠኝ ቻይናዊያን በማዕድን ቁፋሮ ላይ ሳሉ አቦሌ ላይ ጥቃት አድርሳችሁ ገድላችኋቸዋል። ንጹሃን ሞተዋል። ጅግጅጋም ላይ እንደዚሁ የሰዎች ሕይወት አልፏል። ይህም በናንተ የሆነ ነው። አሁን ለሰላም ትግል ከመጣችሁ በኋላ ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ አይመስላችሁም?

ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ ብዙ ሳር ይወድማል ይባላል።

የትኛውም አገር ጦርነት ሲከሰት የሰላማዊ ሰው ሕይወት ያልፋል። ያለ ነገር ነው። እኛ ዓላማችን ሰላማዊ ሰዎችን እናጥቃ ብለን አልነበረም።

ቻይናውያን በማን ጥቃት ነው የሞቱት? ማንን ጠይቀው ነው የኦጋዴን ግዛት የገቡት?

ከመግባታቸው በፊትና ከገቡም በኋላ አስጠንቅቀናቸው ሰላም አለመሆኑን እየነገርናቸው 'እምቢ' ብለው ስለገቡ እኛ የመንግሥት ሠራዊትን ዒላማ ስናደርግ ቻይናውያኑ ስለሞቱ መንግሥት ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት። አምጪው ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት።

ግን ገዳዮቹ እናንተ ናችሁ እኮ? የተገደሉት በእናንንተ አይደለም እንዴ?

በሁለቱም በኩል ጥይት ተተኩሷል። በማን ጥይት እንደሞቱ አይታወቅም። በማን ጥይት እንደተገደሉ ማን ይናገራል? በእኛ ብቻ የሚላከክ አይደለም። የእኛ እጅ የለበትም ብለን አንክድም። ነገር ግን ማን ነው ያመጣቸው?

ሁለተኛ ደግሞ በማን ኃላፊነት ነው የመጡት? በእኛ ኃላፊነት አልመጡም። እኛ እንደውም ማስጠንቀቂያ ሰጥተን ነበር 'እምቢ' አሉ። በመሆኑም እኛ ይቅርታ የምንጠይቅበት ሰበብ የለም። በእኛ ፍቃድና ኃላፊነት አልመጡም፡፡ ጽፈንላቸው ይቅርባችሁ ብለን ነው እምቢ ያሉት። አገራችንና ሃብታችንን ሊወስዱ ነበር የገቡት።

ስለቻይናውያኑን ይህን ካሉ ኢትዮጵያያን የጉልበት ሠራተኞች ደም ፈሶ ይቅርታ ለመጠየቅ ለምን ጉልበት ያንሳችኋል?

በዚህ ጦርነት ስንት ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል? በዚህ ጦርነት ኃላፊው ማን ነበር? እኛ በሰላም ሕዝባችንን እየመራን በነበረበት ሰዓት አመጹን ቀስቅሶ ሕዝብ የጨረሰ ማን ነው? ጦርነቱን ያነሳሳ አካል ነው ለሁሉም ይቅርታ መጠየቅ ያለበት።

ከእኛ ጦር ለሞቱት፣ ከመንግሥት ጦር ለሞቱት፣ ለንፁሃን ዜጎች ሁሉ ኃላፊነቱን መወሰድ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው። ምክንያቱም በሰላም እንዲያወያየንና ችግራችን በሰላም እንዲፈታ ያልሄድንበት የለም። ኢትዮጵያውያንን ከዚህም ከዚያም የሚያዋጉት ኃላፊነት የሚወስዱት አነሱ ናቸው ብለን እናምናለን።

ፓርቲያችሁ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ለብቻው ተገናኝቶ ያውቃል? ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኛችሁት መቼ ነበር? ምን ተወያያችሁ?

ይህን ቀን ነው ብዬ ልነግርህ አልችልም። ግን ከስድስት ወር በፊት አንዴ በቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከአቶ አብዱራህማን ጋር ነበር የተወያዩት፤ እስከማውቀው ድረስ።

ስለ አገራዊ ሁኔታ፣ ስለመጪው ምርጫ፣ ስለሠላም፣ ስለ ዲሞክራሲ እና ስለተለያዩ ጉዳዮች ነበር ያነሱት። በጥሩ ሁኔታ ነበር የተወያዩት። ይህን ያህል ነው የማውቀው።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት ወር ላይ ይካሄዳል። እናንተም ትሳተፋላችሁ። በቅርቡ ጥቃት እየፈፀመብ ነው።አባላ ታስረውኛል። ዶሎ፣ ቸረረ፣ ሸበሌና ቆራሄ ዞኖች ሰብዓዊ ጥሰት አለ። እየተንገላቱብኝ ነው ብላችኋል። አሁንም ችግር አለ ማለት ነው? ይህ ችግርስ ከምርጫ እንድትወጡ ሊያደርጋችሁ ይችላል?

በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ እፈልጋለሁ። ዛሬ ከሚደርሱን መረጃዎችና ከምናያቸው ነገሮች በምርጫው እንደምንሳተፍ ሙሉ ቃል መስጠት አልችልም። ጫፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል። ነገሮች እየተደማመሩ ነው።

ለምሳሌ አሁን ላይ የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ነው። የመራጮች ምዝገባ ጊዜው ተራዝሟል። በቴክኒካል ችግር ሊሆን ይችላል። ሆነ ተብሎም ሊሆን ይችላል። ዛሬ ከሚደርሱን መረጃዎች ነገሮች እየተባባሱ ነው። ለምሳሌ ለመራጮች የሚሰጠው ካርድ ለሶማሌ ክልል ምን ያህል ካርድ እንደሚላክ የምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎቹ ማሳወቅ አለበት።

ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ የሚላከውን ካርድ ተወዳዳሪዎች ማወቅ አለባቸው። በምርጫው ምዝገባ ጊዜም ፓርቲዎቹ ወይም ተወዳዳሪዎቹ ታዛቢ ወይም ወኪል መስጠት አለባቸው፤ ነገር ግን ዝም ብለው በተለያዩ ቦታዎች ሳጥኖችን አራገፉ። ሳጥኑ ደግሞ ክፍት ነው። እስካሁን ለእኛ የተሰጠን ካርድ ቁጥር የለም። እና የተያያዘ ነገር እየመጣ ነው።

ብዙ ምልክቶች እየታዩ ነው። በሚቀጥሉት ቀናት ድርጅቱ ተሰብስቦ ይወያይበታል። ሠራተኞቹም መጀመሪያ ሲቀጠሩ ከዘመድ፣ ከመንግሥት ሠራተኛ ሲሆኑ መቶ በመቶ በሶማሌ ክልል ሠራተኞች የብልጽግና ተከፋይ ናቸው። 99 በመቶ የመንግሥት ተከፋይ ናቸው። በመሆኑም በቀላሉ ለመንግሥት ሊገዙ ይችላሉ።

በመሆኑም ምንም በሌለን መረጃ መቀጠል የምንችል አይመስለኝም። ሆን ተብሎ የተደረገ ነገርም ይመስላል። በተጨማሪም ብልጽግና በመንግሥት ሃብትና ንብረት እየተጠቀመ ነው ያለው። ሥልጣኑንም እየተጠቀመ ነው።

ተወዳዳሪ ልናስመዘግብ አልቻልንም። እዚህ አዲስ አበባ ነው እያስመዘገብናቸው ያለው። ይህንን ስናመለክት እናስተካክላለን ሲሉን ነበር። ምንም የተስተካከለ ነገር የለም። የእኛ ተወዳዳሪዎች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው። በመንግሥት መኪና ዘመቻ እያደረጉ ነው። ለምን ስንላቸው ደግሞ ታርጋ መፍታት ጀምረዋል።

ስለዚህ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በምርጫው የምንሳተፍ አይመስለኝም።

ምን ያህል ዕጩዎችን የት አስመዝግባችኋል?

በሶማሌ ክልልም በሌላ የሶማሌ ማኅበረሰብ ባለባቸው አጎራባች ክልሎች እና አዲስ አበባ ለመወዳደር አስበን ነበር።

ግን በተሳሳተ በዕጩዎቻችን የተሳሳተ አረዳድ እና ቴክኒካል ችግር ምክንያት አዲስ አበባ መመዝገብ አልቻሉም። ድሬዳዋ እንዳናስመዘግብ ደግሞ በብልፅግና ተከልክለናል።

ተከልክለናል ሲሉ ምንድን ነው ማስረጃዎት?

የእኛ ዕጩዎች እንዳይመዘገቡ ተከልክለዋል። በምርጫ ቢሮ ኃላፊዎች አትመዘገቡም ተብለዋል። በገርባ ኢሴ፣ በፊቲ፣ ሃደጋላ ያሉ ዕጩዎችም እንደዚሁ ተብለው አስፈርመዋቸው ከሦስት ቀን እስራት በኋላ ተባረዋል።

በሞያሌ፣ በካሱርቱ፣ በዞላአጦ ምርጫ ኮሚሽን ተገናኝተን ለምን አታስመዘግቡም ሲሉ፤ ኦብነግን እንዳናስመዘገብ በመንግሥት ታዘናል የሚል ምላሽ የሰጡ ነበሩ። ብዙ የተከለከልንባቸው ቦታዎች አሉ። እስካሁን 237 የክልል እና 15 ድሬዳዋ ላይ ከዚህ ላይ አምስቱ ዛቻና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው ወጥተዋል።

ከምርጫ ቦርድ ጋር በክልል ሆነ በፌደራል ደረጃ ይህን ያህል ለማስተጋባት ምን ያህል ርቀት ሄዳችኋል?

የምርጫ ቦርድ አቅማቸው እስከሚፈቅድ ችግሩን ለመፍታት ሞክረው ነበር። መፍታት ያልቻሉትን ደግሞ አዲስ አበባ መጥተን እንድናስመዘገብ አድርገዋል። ለዚህም እናመሰግናቸዋለን።

ይህንን ችግር እንዲፈታ ወ/ሪት ብርቱካን ከክልል መንግሥት ጋር እናገናኛችኋለን ጂግጅጋ እመጣለሁ ብላን ነበር እስካሁን እየጠበቅናት ነው። ችግሩ ይፈታል ብለን እናምናለን። አሁንም ከምርጫ እንቀራለን ማለት አይደለም። ችግሩ ከተፈታ ምርጫ እንካፈላለን፤ ካልተፈታ ግን ውጤቱ መጥፎ ነው።

ምርጫ ትሳተፋላችሁ ብለን ተስፋ እናድርግና እናንተ በክልላችሁ አብላጫ ድምፅ የማግኘት ዕድላችሁ ምን ያህል ነው? የሕዝብ ድጋፋችሁን ስትገመግሙት? ከፍተኛ ድጋፍ ያላችሁ በኦጋዴን ጎሳ ነው። የምትወክሉትም ኦጋዴን ጎሳን ብቻ ነው ይሏችኋል። ከኦጋዴን ጎሳ ውጭ ያሉትንስ ትወክላላችሁ? ይቀበሏችኋል?

[ሳቅ] እኛ እንደ ጎሳ አይደለንም። እንደዚያ ዓይነት ቃላት የሚናገሩ አስተሳሰባቸው ጠባብ ነው ብለን ነው የምናምነው።

እኛ የታገልነው፤ አሁንም የምንታገልለት ለሶማሌው ሕዝብ ነው። በሞያሌ፣ ነገሌ፣ ፊልቱ፣ በጎዱ ኡኩር፣ በጂግጅጋ፣ በድሬዳዋ ባለው የሶማሌ ሕዝበ ተወዳድረናል፤ ደግሞም እንወዳደራለን። ከፍተኛ የማሸነፍ ተስፋ ነው ያለን፤ ነገሩ የምርም በሕዝብ ድምፅ የሚወሰን ከሆነ። እንደዚያ ግን አይመስልም። ለምን በለኝ።

ነገሩ በሕዝብ ድምጽ የሚወሰን ከሆነ ለምንድነው ዕጩ እንዳናመዘግብ የሚከለክሉን። ነገሩ በሕዝብ ድምጽ የሚወሰን ከሆነ ለምንድነው አባሎቻችን የሚታሰሩት?

እኛ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለን ፓርቲ ነን ብለን እናምናለን። አንድ ሰውም አላሰርንም፤ አንድም ሰውም አላባረርንም በሕዝብ ምርጫ ስለምናምን።

ስለዚህ ምርጫው ካልተጭበረበረ 89 በመቶ በላይ ድምፅ እናገኛለን ብለን እናስባለን። ከተጭበረበረ ግን መቶ በመቶ አሸንፈናል ሲል ነበር አቶ መለስ፤ አሁንም እንደዚያ ሊሉን ይችላሉ።

እንደው በምርጫው ብትሸነፉ የምርጫውን ውጤት ተቀብሎ ወደፊት ደግሞ ለተሻለ ውጤት ለመሄድ ያላችሁ ዝግጁነት ምን ያህል ነው?

መቶ በመቶ ዝግጁ ነን!

ምክንያቱም እኛ ከጫካ ትግል መጥተን እንደ ጋዜጠኛ ምን ያህል ሕዝብ አቀባባል እንዳደረገልን ብታይ ጥሩ ነበር፤ አሁንም በቀብሪደሃር፣ በዋርዴር፣ በነገሌ ያለው እንቅስቃሴ ብታይ ጥሩ ነበር።

ሕዝባችን እንደሚመርጠን እናምናለን። እንደ ፓርቲ ከተሸነፍንም እንቀበላለን። ከአሸናፊው ጋር አብረን እንሠራለን። ለሕዝብ ልማት ትግላችንን እንቀጥላለን። ለመጪው ምርጫ እንዘጋጃለን።

ይህ የሚሆነው ግን ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ሲካሄድ ብቻ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን "አሸንፈናል ኑ ፈርሙልን" ቢሉ ግን "አጭበርብራችኋል እንጂ አላሸነፋችሁም" ነው የምንላቸው።

ዘ ጋርዲያን በሶማሌ ክልል ጋዝ በማውጣት ላይ የተሰማሩ እንደ ፖሊ እና ሲጂኤል ያሉ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ሳቢያ የተፈጠረ አካባቢያዊ ብክለትን ተከትሎ በርካቶች እየሞቱ እንደሆነ ዘግቧል። እአአ በ2014 እስከ 2ሺህ 400 ሰዎች ሞተዋል ብሏል። ይህንን የሚመለከተው የፌደራል መንግሥትን ቢሆንም ስለዚህ ጉዳይ ፓርቲያችሁ ያውቃል? ፌደራል መንግሥቱ ትኩረት እንዲሰጥ ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ አለ?

ድርጅታችን ይህንን ያውቃል። ችግር እንዳለ እናውቃለን።

እኔ ከቆራሂ ዞን ነኝ። ዞኔ ስለሆነ ነገሩን በጥልቀት አውቃለሁ። ዶዶይን፣ ሽላቦ እና ሌሎች ቦታዎች ሄጃለሁ። ሰው በማይታወቅ በሽታ እየሞተ ነው።

ሆዳቸው አብጦ በአፍንጫቸው ደም ፈሶ ይሞታሉ። ሐኪም ቤት ሲሄዱም 'ምንም ያገኘነው ነገር የለም ነው' የሚሉት ሐኪሞቹ። እንስሳትም እየሞቱ ነው።

የፌደራል መንግሥት መፍትሔ ማድረግ አለበት። ኩባንያዎቹ ምን ዓይነት እንቅስቀሴ እያደረጉ እንደሆነ ማወቅ አለበት። ምን ተበላሽቶ እንደሄደ ማወቅ አለበት።

በዓለም ነዳጅ ይወጣል፣ ናፍጣ ይወጣል፣ ቤንዚል ይወጣል። ነገር ግን አካባቢን እንዳይበከል የሚያስችሉ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች አሟልቷል ወይ የሚለውን ፌደራል መንግሥት የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት።

በተጨማሪም የሶማሌ ክልል መንግሥት ኃላፊነት መወጣት አለበት ብለን እናምናለን።

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተናል፤ ግን ምንም ግብረ መልስ አላገኘንም። አሁንም እንጽፋለን። ሕዝብ ምንም ማድረግ አይችልም። አንድ ግመል እየጠበቀ ያለ እረኛ ግመሉ ስትሞት ቤተሰቡ ሲሞት ምን ማድረግ ይችላል?

ይህ ኃላፊነት የፌደራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት ነው። አሁንም ጥያቄያችንን እንቀጥላል።

በቀድሞው አስተዳደር አብዲ ኢሌ ብዙ ጥፋቶች ተፈፅመዋል ከእናንተ ጋር በተያያዘ። የአቶ አብዲ ኢሌን የፍርድ ሂደት ተከታትላችሁ ታውቃለችሁ? ለደረሰባችሁ ጥቃት፣ በደልና ሕዝባችሁ ላይ ለደረሰ ጥፋት ራሳችሁን ችላችሁ ክስ የመመስረት ሐሳብስ አላችሁ?

እኛ በአብዲ ኢሌም ሆነ ከእሱ በፊት በነበሩት፣ ከእርሱ ጋር የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሮችና የኢህአዴግ መሪዎች በአፍሪካም በዓለም ፍርድ ቤትም ከሰናል። በሶማሌም በሌሎችም ሕዝቦች ላይ ባደረሱት በደል ተጠያቂ እንዲሆኑ ከሰናል። አሁንም እንከታተላለን።

ነገር ግን ከሚያሳዝኑን እና ከሚያናድዱን ነገሮች አብዱ ኢሌ እና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በፍርድ ቤት የሚጠየቁት በሶማሌ ሕዝብ ላይ ባደረሱት በደል እና ግፍ ሳይሆን እአአ በነሐሴ 4 በጂግጅጋ የሶማሌ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ባደረሱት በደል እና በቤተክርስቲያን መቃጠል ብቻ ነው።

ይህ ትክክል አይደለም ማለቴ ሳይሆን ከዚያ በፊት ሲያደርግ በነበረውም ጭምር ሊጠየቅ ይገባል። አሁንም የታሰሩትና ያሉት የህወሓት አመራሮች በሶማሌ ሕዝብ ላይ ባደረሱት ግፍና በደል መጠየቅ አለባቸው ብለን እናምናለን። እንከታተላለን። ፍትሕ እስከምናገኝ ድረስ አይደክመንም፤ አይሰለቸንም።

የመጨረሻው ጥያቄ የሚሆነው፣ አሁኗን ኢትዮጵያን ድርጅታችሁ እንዴት ነው የሚገመግማት? አገሪቷ ለመፍረስ ቋፍ ላይ ነው ያላችው ከሚለው ጀምሮ አገሪቷ የተሻለ የአንድነት ተስፋ የሚጣልበት ጊዜ ነው የሚሉም አሉ። በብዙ ክልሎች የሚሰማው ዜና ደግሞ የሚረብሽ ነው። እናንተ ደግሞ ድምጻችሁም አይሰማም። ሌላ ቦታ በሚታዩት ነገሮች አይመለከተንም ብላችሁ ነው? በአገር ጉዳይ ለምን ዳር ያዛችሁ?

ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለችው። በዚህ ወቅት ገዥው ፓርቲ የሚጫወተው ሚና እጅግ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ። እናምናለን። የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ደግሞ እንዲሁ ከፍተኛ ሚና አለው።

ይህች አገር እኛ እንደሚመስለን ለምርጫ ከመሮጥ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋታል ብለን እናምናለን።

ለምን? ትላልቅ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ አይሳተፉም ማለት ይቻላል። ለምን?

አሁን አዲስ አበባ ነው ያለሁት። ለምርጫው ጥቂት ጊዜ ነው የሚቀረው። ግን ይህን አታይም። ዛሬ እንደከዚህ ቀደሙ የምርጫ ፖስተሮችና ምልክቶች አይታዩም።

ሕዝብ ደንታ አይሰጥም ለምርጫ ማለት ነው። ለምን? ብለን መጠየቅ አለብን።

በሶማሌና በአፋር ጦርነት አለ። በአማራና በኦሮሞ ሽኩቻ አለ።

በትግራይም ያለው ይኸው ነው። ይህ ሁሉ ነገር እያለ፤ ብሔራዊ ውይይት ተደርጎ ሳንስማማ ወደ ምርጫ መሮጣችን ወደ ከፋ ሁኔታ ይወስደናል ብለን እናምናለን።

በሁሉም ነገር ባንስማማ በአንድ ነገር ቢያንስ በምርጫ ሂደትና ተሳታፊነት እንኳን ብንስማማ ይመረጣል ብዬ አምናለሁ።

እኔ በግሌ አገሪቷ በከፋ፣ በከፋ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው ብዬ አምናለሁ።

ስለ ነገ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እርግጠኛ አይደሉም?

አይደለሁም። እኔንጃ ወደየት እየሄድን እንደሆነ?