ምርጫ 2013፡ ኦብነግ እና ኢዜማ በሶማሌ ክልል የምርጫ እንቅስቃሴያችንን እናቆማለን አሉ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB
ኦብነግ እና ኢዜማን ጨምሮ አራት በሶማሌ ክልል ውስጥ በምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ ያላቸው ቅሬታ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በክልሉ የምርጫ እንቅስቃሴ አይኖረንም ብለዋል።
ይህን ጥያቄ ያቀረቡት የኦጋዴን ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ አንዲሁም የሱማሌ ክልል የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
ፓርቲዎቹና ግለሰቦቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ የምርጫ ሕጎች እና ፓርቲዎች የፈረሙት ቃለ መሃላ በሱማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ተጥሰዋል ብለዋል።
የኦብነግ ሊቀመንበር አብድራህማን ሞሐመድ መሃዲ አራቱ አካላት ይህን መግለጫ ያወጡት ትናንት (እሁድ) በጅግጅጋ ከተማ ውይይት ካካሄዱ በኋላ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ሊቀመንበሩ አቶ አብድራህማን የክልሉ አስተዳዳሪዎች የድምጽ ሰጪዎችን ካርድ አግተው ወስደዋል፤ ለፈቀዱት ግለሰቦችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ካርዶች ሰጥተዋል ሲሉ ይከስሳሉ።
ሊቀመንበሩ ይህን ያሳያል ያሉትን በአንድ ግለሰብ በርካታ የድምጽ መስጫ ካርዶችን ይዞ የሚያሳይ ምስልም ለቢቢሲ አጋርተዋል።
የኢዜማ ቃል አባይ ናትናኤል ፈለቀም፤ ፓርቲያቸው በውይይቱ ከተሳተፈ በኋላ የጋራ መግለጫው መውጣቱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አራቱ ፓርቲዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ አስፈጻሚዎች በክልሉ አስተዳዳር ጫና ሥር ወድቀዋል፣ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ሂደት እና የድምጽ ሰጪዎች ካርድ ስርጭት ከምርጫ ቦርድ ይልቅ በክልሉ አስተዳዳሪዎች ቁጥጥር ሥር ወድቋል ሲሉ ከስሰዋል።
ጨምረውም ለሶማሌ ክልል የተመደበው የመራጮች ምዝገባ ካርድ ቁጥር አልታወቀም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች የምርጫ ካርድ ስርጭት እንዲታዘቡ አልተጋበዙም የሚሉ እና ተያያዥ ቅሬታዎችን ቀርበዋል።
እነዚህ አራት አካላት በዚህ ሁኔታ ፍትሃዊ እና ነጻ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ስለዚህም ተዓማኒነት ያላቸው፣ ገለልተኛ የሆኑ እና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉ የምርጫ ቦርድ ምርጫ አስፈጻሚዎች ወደ ክልሉ እስኪመጡ ድረስ፣ እንዲሁም ግልጽ እና ተዓማኒነት ያለው የመራጮች ምዝገባ ሂደት እስኪኖር ድረስ በሶማሌ ክልል ለመሳተፍ የሚያስችለን የምርጫ ስርዓት ባለመኖሩ የምርጫ ተሳትፏችንን ለጊዜው እናቆማለን ሲሉ ገልጸዋል።
የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ሶሊያና ሽመልስ በበኩላቸው በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ ከኦብነግ ፓርቲ ቅሬታ መቀበላቸውን አረጋግጠው፤ በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ ብሔራዊ ቦርድ ዛሬ እንደሚወያይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ከኦብነግ ቅሬታው ደርሶናል። የጋራ መግለጫው ግን አልደረሰንም። የመራጮች ምዝገባ ገና መጀመሩ ነው፣ ሁለት ወይም ሦስት ቀን ቢሆነው ነው። የምርጫ ቁሳቁሶችም ተጓጉዘው እዚያ የደረሱት ባለፈው ሳምንት ነው" በማለት የተነሱ ቅሬታዎችን መርምሮ ምላሽ ለመስጠት በቂ ጊዜ እንዳልነበረ አመልክተዋል።
የኢዜማ ቃል አቀባይ አቶ ናትናኤል ፈለቀም በሶማሌ ክልል የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አና በምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች መካከል ዛሬ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይም በክልሉ ከምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ችግሮች ተቀርፈው የምርጫው ሂደት በአስቸኳይ ይቀጥላል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይና በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ በድምጽ ሰጪነት የሚሳተፉ መራጮች መዝገባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት የተላለፈው ስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ላይ በመራጭነት ለመሳተፍ ባለፉት ሳምንታት የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ምርጫ ቦርድ አስታውቆ ነበር።
የሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ከሌሎች አካባቢዎች ዘግይቶ ከቀናት በፊት መጀመሩን ፓርቲዎች ገልፀዋል።















