ምርጫ 2013፡ ብልጽግና፣ ኢዜማ እና እናት ፓርቲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎች አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Vepar5
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሦስት ወራት በኋላ በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ ከሚሳተፉ ፓርቲዎች መካከል ብልጽግና፣ ኢዜማ እና እናት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች ማቅረባቸው ተገለጸ።
በምርጫው ከሚሳተፉት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማቅረብ በኩል ገዢው ፓርቲ ብልጽግና 2432 ዕጩዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚው መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ከዚህ አንጻር ከብልጽግና በመከተል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማስመዝገብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1385 ዕጩዎችን እንዲሁም እናት ፓርቲ ደግሞ 573 ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።
ሦስቱን ፓርቲዎች ጨምሮ በምርጫው ለመወዳደር በፓርቲና በግል ለመወዳደር ከስምንት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ቦርዱ ይህንን ይፋ ያደረገው ለሳምንታት ሲያካሂድ የነበረው የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን በተመለከተና አስካሁን ካለው ሂደት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ [ሐሙስ] መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት በምርጫው ላይ ለመሳተፍ 47 ፓርቲዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከዕጩዎች አንጻርም 8209 ዕጩዎች ለተመራጭነት መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
ነገር ግን የተጠቀሰው የዕጩዎች ቁጥር ያለቀለትና የመጨረሻው ሳይሆን፣ ሊጨምር እንደሚችል የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ በምርጫው ለመሳተፍ የተመዘገቡት ፓርቲዎች ቁጥር ግን ከዚህ በኋላ ከተጠቀሰው እንደማይቀየር ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለ22 ቀናት በተካሄደው የእጩዎች ምዝገባ በምርጫው 125 ግለሰቦች በግል ለመወዳደር በዕጩነት መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
የዕጩዎች ምዝገባ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በአጠቃላይ በ673 የምርጫ ክልሎች ላይ ተካሂዷል።
የኦነግ እና ኦፌኮ ጉዳይ
ባሳለፍነው ሳምንት ኦፌኮ እና ኦነግ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ "ተገፍተናል" በሚል እንደማይሳተፉ ማስታወቃቸው ይታወቃል።
ሐሙስ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕጩዎች የተመዘገቡበትን መዝገብ ይፋ ባደረገበት ጊዜ፣ የእነዚህ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ዕጩዎች ዝርዝር በሰነዱ ላይ አልተካተተም።
እነዚህ ፓርቲዎች ከምርጫ ራሳቸውን ስለማግለላቸው የተጠየቁት ሰብሳቢዋ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ "ወደ ዕጩዎች ምዝገባ ከመሄዳችን በፊት ፓርቲዎች ስለገጠማቸው ችግር በቡድን እና በግለሰብ አግኝተን ለችግራቸው መፍትሄ ለመስጠት ሞክረናል" ብለዋል።
ኦፌኮ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ፣ ካልተሟሉ በስተቀር ምርጫ ውስጥ አልገባም በማለት መውጣቱን ጠቅሰው፤ ምርጫ ቦርድ እንደምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ከቀረቡት ጉዳዮች አንጻር እንደማይሰራ አንዳንዶቹም የሚመለከቱት አይደሉም ብለዋል።
"እውነት ለመናገር አንዳንዶቹ ደግሞ እንዴት መልስ እንደሚያገኙ አናውቅም፤ በቀጥታ ከምርጫ ቦርድ ጋር የሚገናኙ አይደሉም። ስለቢሮዎቻቸው መዘጋት፣ ፓርቲዎቹ የት አካባቢ እንደተዘጋባቸው ቢጠየቁም የት አካባቢ እንደተዘጋባቸው አላቀረቡም" ብለዋል።
ሁሉም ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ የቦርዱ ግዴታና ኃላፊነት ነው ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢዋ፣ ሁለቱ ፓርቲዎች በቦርዱ ከምርጫ አልተገፉም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ፓርቲዎች በምርጫ አለመሳተፋቸው የሚያሳዝን መሆኑን የገለፁት ወ/ት ብርቱካን፣ ነገር ግን በዚህ ምክንያት ችግር ይፈጠራል ብለው የተዘጋጁበት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።
በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የገጠመው ችግር
ቦርዱ በዕጩዎች የምዝገባ ሂደት ጊዜ አጋጠሙኝ ያላቸውን ዋና ዋና ችግሮች በመግለጫው አንስቷል።
ከእነዚህም መካከል የቁሳቁስ ማጓጓዣ የትራንስፖርት ትብብር ማነስ፣ የቁሳቁስ ማዘጋጃ ቦታና ቢሮ ባለመሟላት የተፈጠሩ መዘግየቶችና በሠላምና በፀጥታ በኩል ችግሮች እንደነበሩ ተጠቅሰዋል።
ችግሩንም ለመፍታት ተከታታይ ውይይቶችን የኦፕሬሽን ዘርፍ በማቋቋም ለመፍታት ጥረት መደረጉንም ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።
ቤንሻንጉል ጉሙዝና እና በአራቱ የወለጋ ዞኖች በፀጥታ ስጋት ምክንያት ከተቀሩት የኦሮሚያ አካባቢዎች የዕጩዎች ምዝገባ ዘግይቶ የተካሄደ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች አሁንም የፀጥታ ችግር ስጋት መኖሩን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በቤንሻንጉል መተከል ዞን "ግጭት በነበሩባቸው አካባቢዎች የተለየ ዝግጅት እና እቃዎችን ማጓጓዝ ስላስፈለገ የዕጩዎች ምዝገባው ጊዜ ወስዷል።"
ነገር ግን በአራቱም የወለጋ ዞኖች የዕጩዎች ምዝገባ ዘግይቶ ቢጀመርም በአሁኑ ጊዜ ምዝገባው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ወቅት ዕጩዎች የታሰሩባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ሰብሳቢዋ ገልጸው፤ ለምሳሌ በቤንሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ከተማ እና ሐረሪ ክልል ሁለት የአብን ዕጩዎችና ሦስት አባላቱ ታስረው እንደተፈቱ ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በመስቃን አካባቢ ሁለት የግል ዕጩዎች ታስረው እንደሚገኙና ይህንን ጉዳይ ለክልሉ መንግሥት አሳውቀው እንዲፈቱ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርጫ 2013
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ፤ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው በዚህ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ማለትም ከአገሪቱ ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ድምጽ በመስጠት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በዚህ ምርጫ በመላው አገሪቱ ድምጽ የሚሰጡባቸው ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችና ከ254 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።















