ምርጫ 2013 ፡ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተስፋ እና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Mustafa Ferhat Beksen
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ ለግንቦት 28 እና ሰኔ 5 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዛለች። ለዚህም ፓርቲያቸውን ወክለው የሚወዳደሩ የተለያዩ ዕጩዎች ምዝገባም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሃረሪ፣ በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች ከየካቲት 08 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በእነዚህ አካባቢዎች የእጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቀው የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑንም በምርጫ ቦርድ ተገልጿል።
በአፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ ፣ ደቡብ ሕዝቦች እና ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቶች ደግሞ ከየካቲት 15 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወንበት ጊዜ እንደሚሆን ቦርዱ አሳውቋል።
በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከዛሬ ሰኞ የካቲት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አመራሮች አባላቶቻቸውና መሪዎቻቸው መታሰራቸውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ቢሮዎቻቸው መዘጋታቸውን በመግለጽ ይህም በምርጫ ተሳትፏቸው ላይ ጥላ ማጥላቱን ገልፀዋል።
አባላቶቻቸው ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን አክብሮላቸው እንኳ አለመፈታታቸውን በመግለጽም ተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ያሳስበናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ምርጫ ሊሆን ይችላል?
በማክስ ፕላንክ ተቋም የፖስት ዶክቶራል ፌሎ የሆኑት ዶ/ር በሪሁን አዱኛ በሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናቶችን ሰርተዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ኢትዮጵያ ካካሄደቻቸው ካለፉት አምስት ምርጫዎች ልዩ የሚያደርገው አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ መሆኑን በመግለጽ ይጀምራሉ።
በርካቶች ይህንን ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ የዲሞክራሲ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቅራኔዎች ይፈታል ብለው መጠበቃቸው፤ አገራዊ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚለው ላይ የጋራ መግባባት መኖሩም ለየት እንደሚያደርገው ይናገራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ይህ ምርጫ መሠረታዊ ምርጫ መሆኑን መንግሥት ማሰብ ይኖርበታል ሲሉም ይመክራሉ።
ይህ ምርጫ እንደከዚህ ቀደሞቹ ዓይነት ምርጫ ካልሆነ እና መሠረታዊ ምርጫ ከሆነ ደግሞ "ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት አለበት፤ ብቻውን ሊያደርገው የሚችለው ነገር አይደለም" ሲሉ አክለዋል።
የባለፉት አምስት ምርጫዎች ኢህአዴግ በሚባል ፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ የተደረገ ነው በማለት ይሄኛው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ግን በአዲስ ብልጽግና በሚባል ፓርቲ መዋቅር ስር የሚደረግ መሆኑን በራሱ ልዩ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ።
ሌላው ለዶ/ር በሪሁን ይህ ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች በመላው አገሪቱ የሚካሄድ አለመሆኑም ለየት ያደርገዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ ይህንን ምርጫ ስጋትና ተስፋ ይዞ እንዲካሄድ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑንም ይናገራሉ።
የፖለቲካ ለውጥ እና የፖለቲካ ሽግግር ወሬ በሚሰማበት ወቅት የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ደግሞ ይህንን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለየት እንደሚያደርገው ይስታውሳሉ።
ሆኖም ግን ይላሉ ዶ/ር በሪሁን ይህንን ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች የተለየ ነው ወይንም አይደለም የሚለውን የሚወስነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ነው ይላሉ።
ከዘንድሮው ምርጫ ምን ይጠበቃል?
እንደከዚህ ቀደሙ የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ብቻ ይዞ እነርሱን ለመፍታት የሚደረግ የምርጫ ውድድር ከሆነ ካለፉት በብዙ ላይለይ ይችላል ሲሉ ይገልጻሉ።
ነገር ግን አሁን አገሪቱ ላይ ያሉትን የማኅበራዊ እና የፖለቲካዊ ችግሮችን በመሰረታዊ መልኩ ለመፍታት የሚደረግ እና በዚያ እሳቤ ለመፍታት የሚካሄድ ምርጫ ከሆነ ደግሞ ካለፉት ምርጫዎች የተለየ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመንግሥትን እርምጃዎች በመተቸት የሚታወቁት አቶ እያስፔድ ተስፋዬ በበኩላቸው ይህ አገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት ሲካሄዱ ከነበሩ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች የተለየ ይሆናል ብለው አያስቡም።
ይህንን ሃሳቡን ሲያብራሩም ኢህአዴግ ከዚህ በፊት በአውራ ፓርቲነት ከመራቸውና ከተሳተፈባቸው አምስት ተከታታይ ምርጫዎች የተለየ የፖለቲካ ባህል በዚህኛው ምርጫ አለማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።
ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ምርጫዎች ከምርጫ በፊት፣ በኋላ እና በምርጫ ወቅት የተለያዩ ጉድለቶች እንደሚስተዋልባቸው የሚጠቅሱት አቶ እያስፔድ፤ ለዚህም ማሳያዎች ፓርቲዎች እንዳይንቀሰቅሱ ማድረግ፣ አባላቶቻቸውን ማሰር፣ ቢሯቸውን መዝጋት መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ቀጣዩ ምርጫ ከዚህ በፊት ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች ሁሉ የተለየ ይሆናል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የገለፁት አቶ እያስፔድ፤ ይህ ግን በሂደት መጥፋቱን ይናገራል።
በወቅቱ ተስፋ አድርገው የነበሩበትንም ምክንያት ሲያስረዱ፣ የፖለቲካ ምሕዳሩ ከዚህ በፊት ከነበረው ጊዜ ሁሉ የተሻለ መስፋቱን እና በእስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች መፈታታቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሰው ያሻቸውን ያለ ተጽዕኖ የሚሰሩበት እድል ተመቻችቶ እንደነበርም አልዘነጉም።
ከምርጫ እና ዲሞክራሲ ጋር ተያይዞ ያሉ ተቋማትን የሚመሩ ሰዎችንም በሚመለከት በሕዝቡም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ከሞላ ጎደል እምነት የሚጣልባቸውን ግለሰቦች ወደ አመራርነት ማምጣት መቻሉን በማንሳት ቀጣዩ ምርጫ ተስፋ አለው ብለው እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ግን እነዚህ ነገሮች እንዳለ ተቀልብሰው ወደ ነበርንበት ተመልሰናል" የሚሉት አቶ እያስፔድ የፖለቲካ ምሕዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን በርካቶች እስር ቤት እንደሚገኙም ይጠቅሳሉ።
ዛሬም ፍርድ ቤት ንፁህ መሆናቸውን ገልጾ የታሰሩ መኖራቸውን በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቶች ላይ መገለፁን የሚያነሱት አቶ እያስፔድ፤ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን አክብሮላቸው ነገር ግን ፖሊስ ከመልቀቅ ይልቅ አሁንም ከተማ እና ፍርድ ቤት እየቀያየረ የተለያየ ክስ የሚመሰርትባቸው መኖራቸውን ይገልጻሉ።
የባልደራስ አባላት እንዲሁም የተለያዩ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የምርጫ ቦርድ ግቢ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ መታገታቸውን ራሱ የምርጫ ቦርድ የገለፀው መሆኑን በማንሳት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የፖለቲካ ምሕዳሩ ጠብቦ "ፍትሃዊና የተለየ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው" ይላሉ።
ጋዜጠኞችን በሚመለከትም ሲናገሩ ሲፒጄ ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር ያላት ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ከቤላሩስ በመቀጠል በፍጥነት ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛዋ አገር በሚል እንደፈረጃት ይጠቅሳሉ።
ዶ/ር በሪሁን በበኩላቸው ፖለቲከኞች እስር ቤት ውስጥ ሆነው የሚካሄድ ምርጫ የቅርብ እና የሩቅ ጊዜ ተጽዕኖ እንዳለው ይናገራሉ።
በቅርብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አለመቻል ሲሆን፣ አርቆ ሲመለከቱት ደግሞ ከምርጫ በኋላ ለሚመጣው የፖለቲካ ሥርዓት አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ፓርቲዎች ይደርስብናል ያሏቸው ችግሮች ከአሁኑ መፍታት አለመቻል በኋላ ላይ ምርጫውን ለማከናወን የሰላም እና የደኅንነት ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉም አክለዋል።
ምርጫውም ካለፈ በኋላ ምርጫውን ያሸነፈው ፓርቲ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ሕጎችን ቢያወጣ፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ቢፈልግ የሚወሰነው ፓርላማ ባሉ ፓርቲዎች እና ሰዎች በመሆኑ፣ ከዚህ ውጪ የሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችን በአጠቃላይ ትርጉም ባለው መልኩ የማያሳትፍ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
የምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት
ዶ/ር በሪሁን በምርጫ ቦርድ አካባቢ የማይካዱ የአስተዳደር እና የሕግ ለውጦች መካሄዳቸውን ይገልጻሉ። የምርጫ ቦርድ አመራሮች ቀጣዩን ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው "እንደ ግለሰብ ግምት አለኝ" የሚሉት ዶ/ር በሪሁን አጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ ግን ያለው ችግር ከእነርሱ በላይ ነው ይላሉ።
ምርጫ ቦርድ በራሱ ብቻ ማስፈፀም የሚችለው ነገር የለም በማለትም መንግሥት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ሁሉም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው ብለዋል።
አሁን ያለው ጉዳዩ ከምርጫ ቦርድ በላይ ነው የሚሉት ዶ/ር በሪሁን፣ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ "ዝም ብሎ በምርጫ ቦርድ ላይ ብቻ የምንንጠለጠል አይሆንም" ይላሉ።
መንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝቡ፣ የፍትህ አካላት ሁሉም በትብብር ካልሰሩ አንዱ ተቋም ብቻ ይህንን ምርጫ በሥነ ሥርዓት ማድረግ ይችላል ማለት ከባድ ነው ሲሉ ያክላሉ።
ዶ/ር በሪሁን ይህንን ሁሉ ከግንዛቤ አስገብተው ምርጫ ቦርድ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ይችላል ለሚለው ጥያቄ "መልሴ አይችሉም ነው" ይላሉ።
አቶ እያስፔድ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊነት ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልፀው የኦነግ እና ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ቢሮዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተዘግተው፣ ፓርቲዎቹ ምርጫ ላይ እንዴት መሳተፍ ይችላሉ በማለት፣ ምርጫ ቦርድ ይህንን የፓርቲዎቹን ችግር እንኳ ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳልታየበት ያስረዳሉ።
እርሳቸው እና ሌሎች ግለሰቦች በጋራ በመሆን ባካሄዱት የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዘመቻ የኦነግና ኦፌኮ ቢሮዎች የት የት ቦታ እንደተዘጉ አቅማቸው በፈቀደ በአካል በመሄድ፣ ሌሎቹን ደግሞ ከፓርቲው መረጃ በመሰብሰብ በፌስቡክና ትዊተር ላይ ማስፈራቸውን ያስታውሳሉ።
ፓርቲዎቹም ቢሆኑ ይህንኑ ጉዳይ ለቦርዱ በደብዳቤ በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን አቶ እያስፔድ አክለዋል።
ምርጫ ቦርድ ግን "ኦነግም ሆነ ኦፌኮ ቢሮዎቻቸው የት የት ቦታ እንደተዘጉባቸው በትክክል ስላላቀረቡላቸው መቸገራቸውን" ሲናገር መስማታቸውን ይጠቅሳሉ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከፓርቲዎች የሚቀርቡለትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን በመቀበል ምላሽና መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚያደርግ በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ ይታወሳል።
ምርጫውን የሚያሸንፍ ፓርቲ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት የሚፈልግ ከሆነ አሁን ከምርጫ በፊት ቁጭ ብሎ "በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ካሉ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ጋር መነጋገር፤ በተለይ መንግሥትን ለሚያስተዳድረው፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በይበልጥ ፓርቲ ለብልጽግና ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።
ስጋቶች እና ተስፋዎች
ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ የምታካሄደው በተለያዩ የደኅንነት እና የፀጥታ ስጋቶች ውስጥ ሆና ነው። የሕዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ፣ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ቢኖሩም አገሪቱ ያለችባቸውን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት "ቢዘገይም ምርጫ ማካሄድ አማራጭ የሌለው ነገር ነው" ዶ/ር በሪሁን ይላሉ።
መንግሥት የሕዝቡን ይሁንታ ማግኘት እንዲችል የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች እና ሕጎች ተቀባይነትና ተፈጻሚነት እንዲያገኙ ምርጫ ማድረጉ አማራጭ የለውም ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ከዶ/ር በሪሁን ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ያላቸው አቶ እያስፔድ ይህንን ቀጣይ አገራዊ ምርጫ እስር ቤት ካሉ የፖለቲካ አመራሮች ጋር እውነተኛ የሆነ ድርድር ሳያካሄዱ ማከናወን ከዚህ ቀደም "አገሪቱ የሄደችበትን መንገድ መድገም" ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ።
አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ማሸነፉን ያስታወሱት አቶ እያስፔድ፣ አሁን የተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዳይንቀሳቀሱ እድሎችን መዝጋት ወደሌላ አማራጭ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ውይይትና ድርድር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ እያስፔድ የመራጮች ምዝገባ እየተጠናቀቀ መሆኑ ግን ይህንን ተስፋቸውን እያመነመነው መሆኑን ተናግረዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚሉት አቶ እያስፔድ፣ ሕዝቦች በተለያየ ምክንያት ተወካዮቻቸው ባልተሳተፉበት እና በሌሉበት ምክር ቤት ለሚወጡ ሕጎች ተገዢ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ከባድ መሆኑን ከዚህ ቀደም የተደረጉ ተቃውሞዎችን በማስረጃነት በመጥቀስ ይናገራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ምርጫ ማለት አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመት ማን ያስተዳድራት በሚል የሚከናወን መሆኑን በማንሳት አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ፣ የሕግ እና ሌሎች በርካታ ልዩነቶች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለየት እንደሚል ተናግረዋል።
አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲም ሆነ የሚመረጠው ፓርቲ አገሪቱ ያለችበትን ችግሮች ሁሉ ብቻውን የሚፈታቸው አይደሉም የሚሉት ዶ/ር በሪሁን፣ ከምርጫውም በፊት ሆነ በኋላ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ስለምርጫውና ከምርጫው በኋላ ምን ማድረግ እንችላለን፣ የቆዩ መሠረታዊ ጥያቄዎችንና ልዩነቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ማሰብ፣ አገሪቱ የምትፈልገውን መሠረታዊ ለውጥ ታሳቢ ያደረገ ውይይት ያስፈልጋል ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእንነጋገር ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልፀው አሁንም ግን ጊዜ መኖሩን ይናገራሉ። ለዚህም ረዥም ርቀት መሄድ ያለበት መንግሥት መሆኑን ይናገራሉ።
ምርጫው በተለያዩ ልዩነት መንፈሶች ውስጥ የሚካሄድ መሆኑንም በማንሳት፣ ውይይቶች እና ንግግሮች ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ መደረግ እንዳለባቸው ያሰረዳሉ።
አለበለዚያ ግን ከሰኔው ምርጫ በኋላ መንግሥት ችግሮችን ካልፈታ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከምርጫ በኋላ ቀውስ ላለመከተሉ ማረጋገጫ የለም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።














