ምርጫ 2013 ፡ ኦፌኮ እና ባልደራስ በመጪው ምርጫ የመሳተፋቸው ነገር እንደሚያሳስባቸው ገለጹ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ያሳስበናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሁለቱ ፓርቲዎች ይህንን ያሉት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ዓመት ለሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚሆን ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።
የኦፌኮ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ "ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ የፓርቲያችን አመራሮች መታሰር እና የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ለምርጫ የምናደርገውን ዝግጅት አስቸጋሪ ያደርገዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ የባልደራስ አመራሮች በተራዘመ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ እንዳሉ በመጥቀስ "የምንገባበት ምርጫ እጅግ አሳስቦናል" ብለዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ሶሊያና ሽመልስ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው መካሄድ አለበት ነው ያሉት። ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ስጋት ይሆናል ያሉት ሁለት ነገር ነው። አንዱ የአገሪቱ የጸጥታ ችግር ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ቢሯቸው እንደሚዘጋ እና አባሎቻቸው ችግር እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል" ብለዋል።
ፓርቲዎች ለሚያነሷቸው መሰል ችግሮች መፍትሄ መስጠት የሚችለው የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካል እንጂ ምርጫ ቦርድ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሠሌዳውን አርብ እለት ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተሳተፉት አቶ ዛዲግ አብረሃ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየደረሰብን ነው ያሉት ጫናን በተመለከተ ምላሽ ሰጥተው ነበር።
በዚህም መሰረት የቀረቡ ቅሬታዎች ላይ ማጣራት እንደተደረገና አንዳንዶቹ የተጋነኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ የቀረቡትን አቤቱታዎችን ፓርቲያቸው እንደማያጣጥላቸውና ለማረም አስፈላጊውን ነገሮች ሁሉ እንደማያደርግ እንዲሁም ቀጣዩ ምርጫ ትክክለኛ ፉክክር የሚደረግበት እንዲሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ለሚካሄደው ስድስተኛው ዙር አገራዊና ክልላዊ አጠቃላይ ምርጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ በተደረገው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የድምጽ መስጫው ቀን ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 መሆኑ ገልጿል።
አቶ ጥሩነህ በርካታ አባሎቻቸው መታሰራቸውን፣ የቀሩትም ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን እና በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ ጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋታቸውን በመጥቀስ፤ "በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖረንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን" ብለዋል።
ይህንንም ስጋታቸውን ከዚህ ቀደም መግለጫ በማውጣት ማስታወቃቸውን አስታውሰዋል።
ትናንት ምርጫ ቦርድ ባካሄደው ስብሰባ ላይም ተገኝተው ይህንኑ ስጋታቸውን ማስረዳታቸውን የተናገሩት አቶ ጥሩነህ፤ "ችግሮችን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
"ነገር ግን አንዳንድ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ነገሮች መኖራቸውንም ተገንዝበናል" ብለዋል አቶ ጥሩነህ።
እንደ ኦፌኮ እስካሁን በምርጫው አንሳተፍም የሚል ውሳኔ ላይ ባይደርሱም፤ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በሚያስችል አቅም ላይ አለመሆናቸውን ግን አስረግጠው ተናግረዋል።
ለዚህም የጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋት፣ የአባላቶቻቸው እስር፣ ስደትና ማስፈራሪያ እንዲሁም በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።
"በዚህ ሁኔታስ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ ወይ?" ሲሉም ጠይቀዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥትና ጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር በሆኑት በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲያሰማ ለመጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ማዘናቸውን የገለፁት የፓርቲው ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው፤ "በእነአቶ እስክንድር ነጋ ላይ የተሰጠው ቀጠሮ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች በውድድሩ ውስጥ ሳይገቡ መንግሥት ብቻውን ሮጦ 'አሸናፊ ነኝ' ለማለት የተደረገ ይመስላል" ሲሉ ኮንነዋል።
አቶ ገለታው "ምርጫው በህወሓት ዘመን የተለመደ የምርጫ ዓይነት ሊሆን ነው" በማለትም በእነርሱ በኩል ተስፋ እየታያቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"አባላቶቻችን ወከባ አለባቸው። መንግሥት በየጊዜው ምህዳሩን እያጠበበ ነው፤ ባልሰፋ ምህዳር ውስጥ ታሪካዊ ምርጫ ሊደረግ እንደማይችል እያረጋገጠ ነው" ሲሉም ወቅሰዋል።
ይህ እንደ ፓርቲ ብቻም ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ እንደሚያሳስባቸውም አልሸሸጉም።
አቶ ገለታው "ይህ ምርጫ እንደ በፊቱ ተጭበርብሮ እንራመድ ቢባል የማያራምድ ሕዝብ የተነሳበት ወቅት ስለሆነ፤ ድህረ ምርጫ አገሪቷን ወደ ብጥብጥ እንዳይወስዳት ያሳስባል" ብለዋል።
መንግሥት ሁኔታዎችን በፍጥነት ማስተካከል ካልቻለም ምርጫው ታሪካዊ መሆኑ ቀርቶ፤ አደጋዎችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ፓርቲዎች ችግር ገጥሞናል ባሉት ጉዳይ ላይ ለክልል አስተዳደር፣ ለፖሊስ ኮሚሽን ወይም ሌላ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቦርዱ ያሳውቃል" በማለት የመሥሪያ ቤታቸው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ ካላቸው ለቦርዱ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ተጠይቆ፤ 11 ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለቦርዱ ማሳወቃቸውን የጠቀሱት ሶሊያና፤ ቦርዱም ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ያስፈልጋል ብሎ ለመንግሥት ማሳወቁን ገልጸዋል።
በየክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ችግር በተመለከተ ከገዢው ፓርቲ፣ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ጋር የሦስትዮሽ ውይይት የሚካሄድበት አሠራር መዘርጋቱንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የኦፌኮ እና ባልደራስ ፓርቲዎች አመራር እና አባላት የሆኑት ጀዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እንዲሁም እስክንድር ነጋ፣ አስቴር ስዩምና ስንታሁ ቸኮል በሽብር ወንጀል ተከሰው በእስር እንደሚገኙ ይታወቃል።
ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ከየካቲት 8 ጀምሮ የእጩዎች ምዝገባ እንደሚያከናውኑ እና የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ በትናንትናው ዕለት ገልጿል።
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 21 ድረስ ደግሞ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወን ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የድምጽ መስጫ ቀን በአንድ ሳምንት ዘግይቶ ሰኔ 5/2013 ዓ.ም እንደሚከናወን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠብቅ ማስታወቁ ይታወሳል።













