ምርጫ 2013 ፡ መጪው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ሊካሄድ ነው

የምርጫ ቦርድ አርማ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB

በዚህ ዓመት የሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ አጠቃላይ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ የትግራይ ክልልን ሳያካትት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ ተደረገ።

በዚህም መሠረት ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 28/2013 ዓ.ም ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር የድምጽ መስጫ ቀን ደግሞ ከሳምንት በኋላ ሰኔ 5/2013 ዓ.ም መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የትግራይ ክልልን የማይጨምር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በክልሉ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምርጫ በሚስማማ መልኩ ሲመቻች ለክልሉ የምርጫ ሰሌዳ እንደሚዘጋጅ ቦርዱ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ውጪ ድምጽ በሚሰጥበት ዕለት በተደራቢነት "የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ" የሚሰጥ መሆኑን ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው ላይ አመልክቷል።

ይህ ሕዝበ ውሳኔ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን በአዲስ መልክ ከማዋቀር ጋር ተያያዞ የሚካሄድ ነው።

ቦርዱ አጠቃላዩ ምርጫ ሂደቱን በተመለከተ ባወጣው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ቀደም ብለው ከሚካሄዱ የምርጫ ዝግጅቶች በተጨማሪ የእጩዎች ምዝገባ በየካቲት ወር ከ8 2013 እስከ 21 2013 ድረስ እንደሚካሄድ ተጠቅሷል።

በምርጫው የሚወዳደሩ እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻቸውን ከየካቲት 08 2013 እስከ 23 2013 ቀን ድረስ የሚያደርጉበት ጊዜ ይሆንና ከዚያ በኋላ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ ቅስቀሳ የማይደረግበት ጊዜ ይሆናል።

ምርጫዎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ከተካሄዱ በኋላ ውጤት በምርጫ ጣቢያና በክልል ደረጃ በተለያዩ ቀናት የሚገልጽ ሲሆን የመጨረሻው ውጤት በብሔራዊ ምረጫ ቦርድ ግንቦት 29 እና ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ይፋ ይደረጋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ እንዲካሄድ የጊዜ ሠሌዳ ወጥቶለት የነበረው ስድስተኛው ዙር አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያ ማካሄድ እንደማይችል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።

ቦርዱ ባዘጋጀው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ምርጫውን ወረርሽኙ በደቀናቸው ስጋቶች ሳቢያ ለማካሄድ እንደሚቸገር አመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሃሳብ መሰረት ምርጫው በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ወስኖ ነበር።

እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደረስም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያና በዓለም ደረጃ የሚኖረው ሁኔታ በአገሪቱና በዓለም የጤና ተቋማት የሚሰጡ መረጃዎች በየጊዜው እየተገመገሙ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ታይተው እንደሚወሰኑ ተገልጾ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ከወራት በኋላ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ምክር ቤቱ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ ሃሳብ መሰረት ቫይረሱን ለመካላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ በ2013 ምርጫው እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።