ምርጫ 2013 ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሚና ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, NEBE
ሳምንታት የቀሩትን 6ኛውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ ለማስፈጸም አምስቱ የምርጫ ቦርድ አባላት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ቦርዱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትን ብርቱካን ሚደቅሳ (ወ/ሪት)ን ጨምሮ አምስት አባላት አሉት። አቶ ውብሽት አየለ፣ ብዙወርቅ ከተተ (ወ/ሪት)፣ አበራ ደገፉ (ዶ/ር) እና ፍቅሬ ገ/ሕይወት የምርጫ ቦርድ አባላት በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሾማቸው ይታወሳል።
የቦርዱ አባላት ሚናቸው ምንድነው?
አምስት አባላት ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔን በተመለከተ ከፍተኛውን የመወሰን ኃላፊነት የያዘ አካል ነው። በዚህም ቁልፍ ውሳኔን የማሳለፍ ስልጣን አለው።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 መሠረት ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ እና በምርጫ ሕግ መሠረት የሚካሄድን ማንኛውንም ምርጫ እና ሕዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ያስፈጽማል።
የምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ደግሞ በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት ተከስቷል ብለው ሲያምኑ ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የመወሰን ስልጣን አላቸው።
የሥራ አመራር ቦርዱ የምርጫ ቦርድ የመጨረሻው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አካል ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን የምርጫ ውጤቶች ይፋ ከመደረጋቸው በፊት የምርጫ ውጤቶችን ያጸድቃል።
የምርጫ ሕጎችን ማስፈጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቆጣጠር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጎማ ማከፋፈል፣ ለምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ መስጠት እና መቆጣጠር፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን ማሰናዳት እንዲሁም በጀት አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ማዋል የሚሉት ከቦርዱ ስልጣን እና ተግባር መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የቦርዱ አባላት እንዴት ይመረጣሉ?
የቦርድ አባላት የሚመረጡት ዝርዝር ሥነ-ሥርዓቶችን ተከትሎ ነው።
በቅድሚያ ጠቅላይ ሚንስትሩ እጩ የቦርድ አባላትን የሚመለምል ኮሚቴ ያቋቁሟሉ።
የዚህ ኮሚቴ አባላት ደግሞ ከተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍል የሚወጣጡ እና ገለልተኛ የሆኑ ግለሰቦችን ያቀፈ መሆን ይኖርበታል።
ከሐይማኖት ተቋማት፣ ከሳይንስ አካዳሚ፣ ከሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ ከንግድና ማኅበራት፣ ከሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት እና ከአገር ሽማግሌዎች የሚመረጡ ሰዎች የኮሚቴው አባላት ይሆናሉ።
ከዚያም ይህ ኮሚቴ የምርጫ ቦርድ አባል ሊሆኑ የሚችሉ እጩዎችን ጥቆማ ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበራት ይቀበላል።
ኮሚቴው ከተጠቆሙት ሰዎች ውስጥ የቦርድ አባላት ሊሆኑ የሚችሉ እጩዎችን በመለየትና ፍቃደኝነታቸውን በማረጋገጥ የእጩዎቹን ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀርባል።
ጠቅላይ ሚንስትሩም የእጩዎቹ ስም ዝርዝር ከኮሚቴው ከደረሰባቸው በኋላ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በቀረቡት እጩዎች ላይ ምክክር ያደርጋሉ።
ከምክክሩ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ እጩዎቹን ለሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ። ምክር ቤቱም የቀረቡት እጩዎችን በአብላጫ ድምጽ ሲያጸድቅ እጩዎቹ የቦርዱ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሆነው ይሾማሉ።
ብርቱካን ሚደቅሳ- የቦርድ ሰብሳቢ
ብርቱካን ሚደቅሳ (ወ/ት) የቦርዱ ሰብሳቢ ናቸው።
ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ቀደም ሲል የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። ብርቱካን ወደ ስደት ከመሄዳቸው በፊት በተቃዋሚ ፓርቲ በአመራር ቦታ በፖለቲካው ውስጥ ይንቀሳቃሱ እንደነበረ ይታወሳል።
ብዙ የተባለለትን የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎም ከተነሳው ውዝግብ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን የዕድሜ ልክ እስራትም ተፈርዶባቸው ነበር። ከእስር ከወጡ በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ጥናቶችን አድርገዋል።
ከሰባት ዓመታት ስደት በኋላም በ2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ ተሹመዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ይገኛሉ።
አቶ ውብሸት አየለ - የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ
አቶ ውብሸት አየለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቅ ናቸው። በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በዳኝነት አገልግለዋል። ከዳኝነት ሥራቸው ለቀው የራሳቸውን ቢሮ በመክፈት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ሆነው ሠርተዋል።
አቶ ውብሸት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በማማከር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውይይት በማስተባበር እንዲሁም በሌሎች የቦርዱ እንቅስቃሴዎች ላይ በሙያቸው ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተጠቅሷል።
አቶ ውብሸት በሲቪክ ማኅበራት እና ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
አበራ ደገፋ (ዶ/ር) - የቦርድ አባል
አበራ ደገፋ (ዶ/ር ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሶሻል ወርክ እና ሶሻል ዴቨሎፕመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በተጨማሪም፣ በኔዘርላንድስ ከሚገኘው ኢንስቲትዩት ፎር ሶሻል ስተዲስ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና ልማት የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ አላቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው የመምህርነት ሥራቸው ባሻገር በልዩ ልዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች በሙያቸው እንዳገለገሉ የሚነገርላቸው አበራ (ዶ/ር)፤ በዘመን ባንክ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች አስተዳደር ጉባኤ እና በኦሮሚያ የሕግ ጆርናል የቦርድ አባል በመሆን መስራታቸው ይጠቀሳል።
የምርጫ ቦርድ አባል ሆነው ከመሾማቸው በፊት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ እና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ እንዲሁም የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባል ሆነዋል።
ብዙወርቅ ከተተ (ወ/ሪት) - የቦርድ አባል
ብዙርቅ ከተተ(ወ/ሪት) የከፍተኛ ትምህርታቸውን ከኩባ ሐቫና ዩኒቨርሲቲ የውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል በሥነ ቋንቋ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ አግኝተዋል።
ብዙወርቅ (ወ/ሪት) በልዩ ልዩ ተቋማት አገልግለዋል። ከእነርሱም መካከል የቀድሞው የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ አክሽን ኤይድ ኢንተርናሽናል ይገኙበታል።
በግጭት አፈታት እና መከላከል ላይ በሚሠራው የጀርመን አማካሪ ድርጅት ውስጥም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጄክት አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል።
ብዙወርቅ (ወ/ሪት) በመልካም አስተዳደር፣ በአቅም ግንባታ እና ሲቪክ ተሳትፎን በማበረታታት ላይ የሚሠራ፤ 'ዜጋ ለዕድገት' የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራች እና የቦርድ ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል።

የፎቶው ባለመብት, NEBE
አቶ ፍቅሬ ገ/ሕይወት
ከቦርድ አባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁትን ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) በመተካት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጓደለ የአንድ የምርጫ ቦርድ አባል ቦታ ጥቅምት ወር ላይ አቶ ፍቅሬ ገ/ሕይወትን ሹሟል።
አዲሱ የምርጫ ቦርድ አባል አቶ ፍቅሬ /ሕይወት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ያገለገሉ መሆኑን ተገልጿል።















