ምርጫ 2013፡ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ተጠባቂ የሚያደርጉ አምስት ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Mustafa Ferhat Beksen
በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ባለ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ፀረ መንግሥት አመፆች ተቀሰቀሱ።
ይህም ከግዜ ወደ ግዜ እየተጋጋለ ግንባሩ ከውጪም ከውስጥም ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ እና ሊቀመንበሩ እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሆነ።
የሕዝባዊ አመፁን፤ ብሎም በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረውን የመከፋፈል ምዕራፍ ይዘጋል ተብሎ በተጠበቀው ለውጥ፣ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መጋቢት 18/ 2010 የፓርቲው ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፣ በበዓለ ሲመታቸው አስተዳደራቸው ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን ዋና ዋና ተግባራት ያካተተውን ንግግራቸውን አሰሙ። ታዲያ በንግግራቸው ላይ፤ መንግሥት 'ከተፎካካሪ' የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ማሻሻል እንዲሁም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን የተጠቀሰ ጉዳይ ነበር።
በምርጫ ዙሪያ አስተዳደራቸው ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብበራሪያ በሰጡበት ሌላኛው የምክር ቤት ንግግራቸው ላይም ‹‹ላለፉት ሶስት አመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ አካሄዳችን መቀየር አለበት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ናፍቆናል ብሎ ከውጪም ከውስጥም ባደረገው ጥረት ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ የሆነውን እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚቀጥለው ምርጫ እንደ አንድ ዋና መመዘኛ ተወስዷል›› ሲሉም ተደመጡ።
ታዲያ ከዚህ ለውጥ ማግስት የሚካሄደው ምርጫ ምን የተለየ ያደረገዋል?
ብርቱካን ሚደቅሳ
‹‹መንግሥት ለራሱ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በምርጫ፣ ለቦርድ አመራርነት ያስመርጣል የሚውን ክስ ከግምት ውስጥ ያስገባ›› በማለት የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው የሚታወቀውን ብርቱካን ሚደቅሳን እጩ ማድረጋቸውን አስረዱ።
የቀድሞዋ ዳኛ፣ ፖለቲከኛ እና ምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ አልሆነም ሲሉ ከስ የመሰረቱት፤ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ምርጫውን ለማስፈጸም በዝግጅት ላይ መሆናቸው መጪውን ምርጫ በጉጉት እንዲጠበቅ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሹመትን ተከትሎ ነበር ብርቱካን ሚደቅሳ በስደት ከሚኖሩበት ሰሜን አሜሪካ ለኃላፊነት ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው የመጡት።
ቦርዱ ከእርሳቸው በፊት ሶስት ሰብሳቢዎች ኖረውት ያውቃል። ሕገ መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ የመጀመሪያው የቦርዱ ሰብሳቢ የነበሩት ከማል በድሪ ከ1986-1997 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል። ቀጥሎም መርጋ በቃና ከ1999-2009 ዓ.ም እንዲሁም ሳሚያ ዘካሪያ ከ2010-2011 ቦርዱን መርተዋል።
ብርቱካን ከሌሎቹ በምን ይለያሉ?
ብርቱካን በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ቅንጅትን ወክለው ተወዳደረዋል። ምርጫውን ተከትሎም መንግሥት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና አመራሮችን የማሰር እርምጃ ሲወስድ የዚህ ገፈት ቀማሽ ነበሩ።
በፖለቲካ ተሳትፏቸው ዓመታትን በእስር ያሳለፉት ብርቱካን በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከተመራጭነት ይልቅ ምርጫውን የሚያስፈጽመውን ተቋም ይመራሉ።
‹‹ዛሬ የማቀርባቸው እጩ ለመንግሥትም ቢሆን በተሳሳተ መንገድ እጅ የማይሰጡ፣ ለሕግ እና ስርዓት ጽኑ እምነት ያላቸው፣ እምነት ብቻ ሳይሆን፤ ለዚያ ዋጋ ለመክፈልም ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስመሰከሩ ናቸው›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤት ስለ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
አዲሷ ሰብሳቢ ከመጡ ቦርዱ የተቋሙን ሕጋዊ እና ተቋማዊ ቅርፅ በተለያ መልኩ ቀይሯል።
ቦርዱ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ አባላት የነበሩት ሲሆን፤ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ወደ አምስት ዝቅ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ምርጫን የምታስተዳድርባቸው ሶስት ሕጎች ወደ አንድ ተጨምቀው እና የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ሥራ ላይ ውሏል።
ቦርዱ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን በመቀየር አዳዲስ ቁሳቁሶችን ማስተዋወቅ ከጀመረም ሰነባብቷል።
ብርቱካን በ1996 ዳኛ ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ በሚይዙት ጠንካራ አቋም ስማቸው ይነሳል። በስደት በቆዩበት አሜሪካም ተጨማሪ ትምህርት፤ በተለይም ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ ልምዶችን ማግኘታቸው ተደምሮ መጪውን ምርጫ የሚያስፈጽመውን ቦርድ መምራታቸው፣ የምርጫው ተዓማኒነት የራሱ ሚና ይኖረዋል የሚሉ አስተያየቶች ተደጋግመው ተሰምተዋል።
በሕገ-መንግሥት እና ምርጫ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ያደረጉት የሕግ ባለሞያው አደም ካሴ፤ የቦርዱ ሰብሳቢ ጥንካሬ የቦርዱ ጥንካሬ ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ቢስማሙም፤ ከግለሰብም በላይ ሌሎች የቦርዱ አባላት ገለልተኛነት ብሎም የተቋሙ ጥንካሬ ይወስናል ሲሉ ያስረዳሉ።
ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ዳኛ መሆኑ ወሳኝ ቢሆንም ይህ ያለ መንግሥት ትብብር ውጤታማ ምርጫ ለማካሄድ ያስችላል ማለት እንዳልሆነም አደም ይገልፃሉ።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅሞ ከሚያደርስብን በደል አልተከላከለንም ሲሉ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲዎች በቀጣዩ ምርጫ የመሳተፍ አቋም ላይ አንገኝም ሲሉ ቆይተዋል።
ኦፌኮ እና ኦነግ አባላቶቻችን ሲታሰሩ እና ጽህፈት ቤቶቻችን ሲዘጉ ምርጫ ቦርድ በዝምታ አልፎናል ሲሉም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
‹‹ምርጫ ቦርድ እንደተቋም ራሱን በማጠንከር ስራዎች ላይ ተጠምዶ መቆየቱ በተለይም የተወዳዳሪ ቡድኖችን መብቶች መጠበቅ ላይ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ይሄም ለቦርዱ በቀረበው በማስረጃ ላይ የተመሰረተ አቤቱታ ላይ ይመሰረታል›› ሲሉ አደም ለቢቢሲ ገልፀዋል። ለዚህም ቦርዱ በቅርቡ ገዢው ፓርቲ በሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ስም አጥፍቷል ተብሎ ለቀረበለት አቤቱታ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እንደማስረጃነት ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ እና የፖለቲካ ግለቱ ሲጨምር እንዲህ ያሉ ወቀሳዎች ይጨምራሉ፤ ቦርዱም እየተፈተነ ይሄዳል ሲሉ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
"አሸባሪ" ተብለው ተፈርጀው የነበሩ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት መሆኑ
መጪውን አገራዊ ምርጫ ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ሌላኛው፤ ነፍጥ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች በዘንድሮ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ መወዳደራቸው ነው።
በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'አሸባሪ' ተብለው ተፈርጀው የነበሩት፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር እና አርበኞች ግንቦት 7 (ከስሞ ኢዜማ ሆኖ) ወደ አገር ቤት ተመልሰው በምርጫው ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከመሳተፍም ባሻገር የክልሉን ምርጫ አሸንፎ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በመጪው ምርጫ ላይ ለመወዳደር እጩዎቹን እያዘጋጀ ይገኛል።
ግንባሩ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ሜዳ የገባው፣ የካቲት 01/2011 ዓ.ም 1740 ታጣቂዎቹን ትጥቅ በማስፈታት በሶማሌ ክልል በሚገኙ የሲቪል እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ለመመለስ ከክልሉ መንግሥት ጋር ተስማምቶ ነበር።
ምንም እንኳን የፓርቲው መሪዎች እርስ በእርስ ብሎም ከክልሉ መንግሥት ጋር የተለያዩ ፖለቲካዊ ያለመግባባቶች ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም አንድም የግንባሩ አባል ወደ ትጥቅ ትግል አለመመለሱን ፓርቲው ለቢቢሲ ገልጿል።
የፓርቲው ሊቀ መንበር አብዲራሂም መሃዲ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የተገባላቸው አብዛኛው ቃል ባይፈፀምም ፓርቲያቸው በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዳልቆረጠ እና በክልሉ ያለውን ሰላም እንደ ስኬት እንደሚቆጥረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
‹‹ሕዝባችን ከዚህ በኋላ ወደ ጦርት እንዲገባ አንፈልግም፣ ለዚህም ነው ልዩነት ወደ ግጭት እንዳያመራ የራሳቸንን ድርሻ እየተወጣን ያለነው። መጪው ምርጫም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ እና የፌደራል መንግሥት ምን እንደሚያደርጉ ባናውቅም የክልሉ መንግሥት ግን ወደ አገር ከገባንበት ቀን ጀምሮ የሚያደርስብን ጫና አሳሳቢ ነው›› ሲሉም አብዲራሂም ገልፀዋል።
መሠረቱን በኦሮሚያ ክልል ያደረገውን እና የጠቅላይ ሚንሰትሩን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ አገር የተመለሰው ኦነግ፤ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ዓላማዬን 'በሠላማዊ ለማሳካት እየተንቀሳቀስኩ እገኛለሁ' ይላል።
ከ400 በላይ የምርጫ ወረዳ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ኢዜማ፣ 6 ፓርቲዎች ከስመው የመሰረቱት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ነፍጥ አንግቦ ሲታገል የነበረው አርበኞች ግንቦት 7 ተጠቃሽ ነው።
ኢዜማ "ዜግነትን መሠረት ያደረገ" ፖለቲካን በማራመድ፤ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ቀዳሚ ግቤ ብሎ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የሕገ-መንግሥት እና ምርጫ ጉዳዮች ባለሙያው አደም ካሴ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አፈና ምክንያት የተቃውሞ ፖለቲካ መሰረቱ በአብዛኛው በውጪ አገራት ነበር ይላሉ። አደም የእነዚህ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መመለስ ከፍተኛ ተስፋ እንዲሁም ጫና እና ጭንቀት ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።
‹‹አንዳንዶቹ እንግልት አለብን፣ ቢሮ ከፍተን መንቀሳቀስ አልቻልንም እያሉ ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ በእስር ላይ ናቸው። በተለይ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉት ፓርቲዎች ከዚህ አንጻር ያኔ ሲመጡ የነበረውን የሚያክል ተስፋ አሁን ባይኖርም፤ ተስፋው ሙሉ በሙሉ ተሟጥጧል የሚል ግምት የለኝም፣ ይህም በቀጣይ ወራት የሚኖረው መሻሻል ላይ ይመሰረታል›› ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
በርካታ ፖለቲከኞች እስር ላይ ሆነው መካሄዱ
በኢትዮጵያ በተለይም ከሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላቶች በእስር ላይ ሆነው ምርጫ ማካሄድ እንግዳ ነገር አይደለም።
በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተለይም በ2002 እና 2007 ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ ሆኖ ይካሄዳል የሚሉት አደም፤ ከሁለቱ ምርጫዎች የማይሻል ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ሲሉ ያነፃፅራሉ። ነገር ግን መለኪያው መሆን ያለበት ሕገ መንግሥታዊ ስርአቱ እና ሕጎች የሚጠይቁት መመዘኛዎች መሟላታቸው ነው፤ ከዚህ አንፃር ዘርፈ ብዙ ጎዶሎች አሉ ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት የኦነግ፣ የኦፌኮ እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአዲስ አበባ ያለውን ዋና ጽህፈት ቤቱን ጨምሮ 103 ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል። በዲስትሪክት ደረጃ 989 አባላቶቼ ታስረው ይገኛሉ ያለው ኦነግ 145 መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም 32 ከፍተኛ አመራሮቼ በእስር ላይ ናቸው ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
የኦፌኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እስር ላይ መሆናቸውን በማስታወስ "አሁን በምርጫ አንሳተፍም አንልም። ይሁን እንጂ ምርጫ መሳተፍ የማያስችል ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው" ይላሉ።
በተመሳሳይ ግንቦት 28 ለሚካሄደው ምርጫ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ "የምንሄደው ምርጫ ውስጥ እንገባም የሚል እምነት የለንም። ነገር ግን እንደ አገር የምንገባበት ምርጫ አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ያሳስበናል" ሲሉ ለቢቢሲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተናግረዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የቀድሞ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ ፓርቲው የታሰረበት አባል ወይም አመራር ባይኖርም፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወደ 20 የሚቆጠሩ ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ፓርቲያቸው እጩዎቹን ያስመዘግባል፤ ነገር ግን ቅስቀሳን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን እንዴት ያካሂዳል የሚለው ያሳስበናል ብለዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደበኛ ስብሰባ እንኳን እንደልባቸው ለማካሄድ የማይፈቀድላቸው ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚጠቅሱት አደም፤ ገዢው ፓርቲ ግን የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የወጡ ደንቦችን እንኳን የማያከብሩ ሰልፎችን ሲያካሂድ መመልከት በራሱ አሁንም ለገዢው ፓርቲ የሚያደላ ስርአት እንዳለ ያሳያል ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹መንግሥት አሁንም የፖለቲካ ችግሮችን እንደ ፀጥታ ችግር አድርጎ የማየት አባዜው ስላለ በተለይም ምርጫው እየቀረበ ሲሄድ እና ሙቀቱም ከፍ እያለ ሲመጣ በተቃዋሚዎች ላይ ጫና ሊጨምር ይችላል›› ሲሉ ባለሞያው ያስረዳሉ። በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ውድድር የማይፈቀድበት ምርጫ ሊሆን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
ህወሃትን የማያሳትፈው ምርጫ
ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪ በነበረባቸው ያለፉት አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች የተለያዩ ወቀሳዎችን ሲያስተናግድ ቆይቶ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በተመለከተ ግን ከማዕከላዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የተገለለው ፓርቲው ወቀሳዎችን ሲያቀርብ ነበር። በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ምርጫ እንዲራዘም ሲወሰንም ህወሃት በክልሉ ምርጫ ማካሄዱ ብሎም ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ፓርቲው ከጥቂት ወራት በኋላ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ የተሰረዘ ሲሆን፣ የፓርቲው አመራሮች በክልሉ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተወሰኑት ህይወታቸው አልፏል፣ ሌሎቹ በትጥቅ ትግል በበረሃ የሚገኙ ሲሆን የተወሰኑት በሕግ ጥላ ስር ይገኛሉ።
እናም ህወሃት ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ጀምሮ እንደ ፓርቲ ተሰርዞ የሚካሄድ የመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ ይሆናል። በክልሉ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ዘግይቶ እንደሚደረግ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። አደም እደሚያስረዱት ህወሃት በትግራይ ክልል ብቻ የሚወዳደር ፓርቲ እንደመሆኑ የፓርቲው ያለመኖር በቀጥታ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም በሂደት የሚታዩ ውጤቶች ግን መኖራቸው አይቀሬ ነው ይላሉ።
እንደ አደም ገለፃ ፓርቲው እንደ አንድ ነባር ፓርቲ ያካበተው የራሱ ልምድ፣ አቅም እና ሃብቶች የነበሩት መሆኑ እና አሁን ያ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የራሱ ጉድለት ይኖረዋል። በህወሃት የሚደገፉ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ ያንን ያለማግኘታቸው የፓርቲው መጥፋት ከክልሉ ያለፈ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ያስረዳሉ።
ምርጫው ኢትዮጵያ ለገባችባቸው ችግሮች መፍትሄ ያመጣ ይሆን?
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፍቶ በመተከል ዞን ላይ ተተግብሯል። ኢትዮጵያ እና ሱዳንም አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ በሚል ግጭት ውስጥ ገብተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ የፖለቲካ ልዩነቶች ተካረው እንዲሁም ልሂቃኑ በሚመሩት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ መገኘቷን ብዙዎች ደጋግመው ያነሳሉ። በአገር ውስጥ በተነሱ ግጭቶች አያሌ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት እና እስከ አሁንም ድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ። ብሔርን፣ ሃይማኖትን ብሎም ሌሎች ማንነቶችን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መስማትም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
የአብን የቀድሞ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ መጪው ምርጫ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ማውጣቱ ወይም መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ለአዲስ ቀውስ ይጋብዛል ብለው ይሰጋሉ። ፓርቲያቸው ከምርጫ በፊት አገራዊ ንግግር ያስፈልግ ነበር ብሎ ቢጎተጉትም ተቀባይነት አላገኘም ሲሉ ያስረዳሉ። ምርጫውን ተከትለው የሚኖሩ ውጤቶች ወደ ሌላ ቀውስ ሊያስገቡ ይችላሉ ብለው ቢያምኑም፣ ምርጫው መደረጉ ስላልቀረ ግን ጠንክረው ለመወዳደር ተዘጋጅተዋል።
በደሳለኝ ሃሳብ የሚስማሙት አደም ምርጫ እንኳን እንዲህ በተለያዩ ቀውሶች ውስጥ በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥም ብዙ ግዜ ውጥረት ይፈጥራል ይላሉ። የምርጫ ውጤት ለአምስት አመት ስለሚዘልቅ የተሸነፈው ቡድን ገዢው ፓርቲም ይሁን ተፎካካሪዎቹ በቀላሉ በፀጋ አይቀበሉትም።
‹‹ መሰረታዊ የፖለቲካ ልዩነቶች እያሉ ያለንግግር በሚደረግ ምርጫ ብቻ ካለው ችግር መውጣት አይቻልም። ተቃዋሚዎች የሕዝብ ቅቡልነት እንዳላቸው እና የሚወክሉት እና የሚደግፋቸው የሕዝብ ክፍል እንዳለ አምኖ ለንግግር መቀመጥ ያስፈልጋል›› የሚሉት አደም ‹‹ያለ ንግግር ምርጫን ማካሄድ እንደ ህመም ማስታገሻ ለተወሰነ ግዜ ቅቡልነት ያመጣ ይሆን እንጂ ዘላቂ ውጤት አያመጣም›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ 2007 ምርጫ መማር ያለባትም ይህንኑ እንደሆነ የገለፁት የሕግ ባለሞያው ከምርጫው በኋላ ለጥቂት ወራት ሰላም ቢሆንም ችግሮቹ ከመሰረታቸው ካልተፈቱ ለውጥ አይመጣም ይላሉ። ይህም በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት የፖለሲ ሳይሆን በመሰረቱ በአገረ መንግስቱ ላይ ገና መስማማት ሳይደርስ የተመረጠው ፓርቲ ቅቡልት አለኝ ብሎ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጦችን፣ ካስፈለገም ሕገ መንግስቱን እቀይራለሁ የሚል ከሆነ ወደ ባሰ ቀውስ ሊከት ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ።
ነገር ግን መንግስት ከምርጫው በኋላ በሚመረጡ እና ቅቡል በሚሆኑ ፓርቲዎች አማካኝነት ንግግሩ ይካሄደል ያለውን የሚተገብር ከሆነ ምርጫው ምን አልባት አገሪቷ ካጋጠሟች ችግሮች የሚያወጡ መፍትሄዎችን ሊያመጣ ይችላል ሲሉም ተስፋቸውን ያስቀምጣሉ።













