በአዛውንቶች የሚመራው የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ

ማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን ፣ 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የምርጫ ሥርዓትን ስለ ማሻሻል የመከሩበት መድረክ ከዋናው አጀንዳ ባሻገር አንድ ጉዳይ በተለየ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል ፤ መድረኩ በአዛውንት ወንድ ፖለቲከኞች የተሞላ መሆን።
የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ፊታውራሪዎች በተለይም ለአራት ወይም አምስት ዐሥርታት በተቃውሞ የቆዩና በዕድሜ የገፉ መሆናቸው ብዙዎችን ያነጋግር ይዟል። ክስተቱ 'ወጣት ሴቶችና ወጣት ወንዶች በተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎ ቦታቸው የት ነው?' የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ሳይለኩስ አልቀረም።
በሌላ በኩል ሴት በመብራት የሚፈለግበት መድረክ መሆኑን ተከትሎም "ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን" የሚሉ አስተያየቶችም በማኅበራዊ ሚዲያ ተንፀባርቀዋል።
"ሴቶችን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን"
የሥርዓተ ፆታና ሕግ አማካሪ የሆነችው ሕሊና ብርሃኑ "ሴቶቸን የማያሳትፉ ተቃዋሚዎችን እንቃወማለን" ሲሉ ድምፃቸውን ካሰሙት መካከል አንዷ ናት።
'ያለውን ሥርዓት ክፍተትና ጉድለት እሞላለሁ ብሎ የተነሳ ተቃዋሚ ሴቶችንና ወጣቶችን አካታች አለመሆን ተቃርኖ አለው' ትላለች ሕሊና።
"አንድን ሥርዓት የተሻለ አደርጋለሁ ብሎ አካታች አለመሆን፣ ፍትህና መፍትሄ ሳይዙ መምጣት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ነው። አካታች ሳይሆኑ ተቃዋሚ መሆን አይቻልም "ትላለች።
ወጣት ሴቶች በሁለት መልኩ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ስታስረዳ፤ ወጣት ሲባል የሚታሰበው ወንድ ፤ ሴት ሲባልም የሚታሰበው ትልልቅ ሴት መሆኑን በምክንያትነት ታስቀምጣለች።
ስለዚህም ሴቶቸን በተለይም ወጣት ሴቶችን ሳይዙ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር የሚቻል አይደለም።
"አካታች ያልሆነ፣ በቁጥር ብዙኃኑን የማይጨምር ፖለቲካ በብሔር ቢሆን ያስነውር ነበር" የምትለው ሕሊና 'ወጣቱ አገር ተረካቢ ነው ' እንዲሁም 'የሴቶች ተሳትፎና ወደ አመራርነት መምጣት ቀስ በቀስ ይስተካከላል' የሚሉ አስተያየቶችንም በበጎ አትመለከታቸውም።
"ወጣት የነገ መሪ ነው" የሚባለው መደለያ ሆኖ ይሰማታል። "ወጣት የሆንኩት፣ ሰው የሆንኩትና ጉዳይ ያለኝ ዛሬ ነው። ስለዚህ የዛሬ እንጂ የወደፊት አይደለሁም።" ትላለች። በተመሳሳይ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎም መሆን እንደሚገባው ሳይሆን ቀስ ብሎ እንደሚመጣ ነገር መታየቱም ትክክል እንዳልሆነ ትረዳለች።
ሕሊና በከፊል መፍትሄ ሊመነጭ የሚችለው ከምርጫ ቦርድ እንደሆነ ታስባለች። ይህ ሊሆን የሚችለውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምዝገባ በሚመጡበት ጊዜ ነው። ይኸውም ተመዝጋቢ ፓርቲዎች የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን በቁጥር ጭምር እንዲያስቀምጡ መስፈርት ማበጀትን ይጨምራል።
በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ሕግ ሲኖር ደግሞ ፓርቲዎቹ እንዲሁ መቃወም ብቻ ሳይሆን የጠራ የሥርዓተ ፆታና የወጣቶች ፖሊሲ እንዲቀርፁ እንደሚያበረታታቸው እምነት አላት።
"ትግላችን ይቀጥላል"
የአረና ፓርቲ መሥራች የሆኑት የቀድሞ የህወሓት ታጋይ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ እስከ አሁን የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ በጣም የተገደበ መሆን የተቃውሞ መድረኩ ዛሬም በስልሳዎቹ የፖለቲካ ትኩሳት ወጣቶች፤ (በዛሬዎቹ አዛውንቶች) እንዲመራ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
"ምህዳሩ በጣም ገዳቢና ነፃነት የሌለው ነበር። እስከዛሬ በተቃውሞ ያሉት በስልሳዎቹ ወጥተው ደፍረው መናገር የቻሉ ናቸው።ወጣቱ ግን የሴቶች ፣ የወጣት ማኅበርና ወጣት ሊግ እየተባለ ታፍኖ የቆየ ነው።"
ነገሮች ክፍት ሆነው ሰዎች በፈለጉበት መንገድ በነፃት የሚደራጁበት እድል እስካልተፈጠረ ድረስ አሁንም ለዓመታት የዘለቁት ቀደምት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መቀጠላቸው እንደማይቀር ያመለክታሉ።
በተጨማሪ የፖለቲካው ሴቶችን አሳታፊ አለመሆን የአባታዊ ሥርዓት ውጤት እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ አረጋሽ ሴቶች በመደራጀት ለራሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥቅም ተደራጅተው ይህን እውነታ መቀየር እንዳለባቸው ያምናሉ።
ለእርሳቸው በብዙ የትግል ድምር ውጤት ዛሬ ላይ መደረሱ አንድ ነገር ነው ። የሕገ መንግሥቱ መፅደቅ ደግሞ እንደ ትልቅ ስኬት ይመለከቱታል።
"ግን ይህ ሕግ ስላልተተገበረ ዛሬም ስለ ዲሞክራሲ ችግር፣ ስለ ሰብአዊ መብት ጥሰት እየሰማን ነው። ታገልን፣ የተቻለንን አደረግን፤ ግን ሂደት ነውና ምን ማድረግ ይቻላል። ለውጥ እንዲመጣ ትግላችን ይቀጥላል" ይላሉ ወ/ሮ አረጋሽ።
"ቆሞ የቀረ ተቃውሞ"
የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ በፓርቲ ደረጃ በአስተዳደር ወደ ላይ እየወጡ ያሉ ሰዎች ሲታይ ኢህአዴግ የተሻለ አቋም ላይ ነው የሚል እምነት አለው።
በተቃራኒው "በ60ዎቹና 70ዎቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተቆጣጠሩት የተቃውሞ ፖለቲካ ቆሞ ቀርቷል" ይላል።
የተቃውሞ ፖለቲካው ለምን በአንጋፋዎች ተሞላ? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መሪዎቹ ለተለየ ሐሳብ ክፍት አለመሆናቸውን ያነሳልና፣ ወጣቱ ደግሞ በነበረው 'ዘልማዳዊ ፖለቲካ' ውስጥ ጊዜውን ከሚያጠፋ ለራሱ ሮጦ የፈለገበት መድረስ የሚፈልግ በመሆኑ እንደሆነ ይገልፃል።
ከነዚህ በተጨማሪም ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆኑም ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ያምናል። እርስበርስ መጠላለፍና በወጣቶች አቅም ላይ ጥርጣሬን ማሳደር በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው።
"...የሚሞክረውም በሴራና በዘልማድ በሚሠራ ሥራ ተጠልፎ ይወጣል። የእኔም ቆይታ በዚህ ውስጥ ነበር። 'እናንተ ደግሞ ትናንት መጥታችሁ ፖለቲካ ልታስተምሩን ነው?' ይባላል"
ይህ በእንዲህ እያለ በርካቶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አብዛኞቹ አባሎቻቸው ወጣቶች እንደሆኑና በአደረጃጀትም የወጣት ቡድን እንዳላቸው ይገልፃሉ።ይህ ከሆነ ወጣቶች ለምን ጎልተው አይታዩም?
ዮናታን እንደሚለው ምንም እንኳ መዋቅሮቹ ቢኖሩም በዚህ 'በጣም በታፈነ ' የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ልምድ ለሌለው ወጣት ሰብሮ መውጣት ትልቅ አቅም የሚጠይቅ ነው። "የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ደግሞ ከራሳቸው ውጭ ማንም ጎልቶ እንዲወጣ የሚፈቅዱ አይደሉም።"
"ወጣቶችም አዛውንቶችም ያስፈልጋሉ"
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ድርጅታቸው በመዋቅር የተደራጀ የወጣት ሊግ እንዳለውና የወጣት ክንፉ ትግሉን በበላይነት የሚመራ እንደሆነም ይገልጻሉ፤ በግምት ሰማንያ በመቶ የሚሆነው አባላቸውም ወጣት እንደሆነ በማስገንዘብ።
ወጣቱን እንዴት ወደ አመራር እናውጣ? የሚለው ላይ ካልሆነ በስተቀር ትግሉን የተሸከመውና የዛሬውን ለውጥ ያመጣው ወጣቱ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ።
"ከሥር የወጣነው፣ ከውጭ የገባው እንዲሁም ምኒሊክ ቤተመንግሥት የገባነውም በወጣቱ ትግል እንጂ በሌላ እኮ አይደለም" ሲሉ ይህንኑ እምናታቸውን በማስረጃ ያጠናክራሉ።
በተቃውሞ ፖለቲካው አመራር ደረጃ ለምን የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎና አመራር አልታየም ለሚለው ጥያቄ ታዲይ ዶ/ር መረራ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ይልቅ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ጥያቄውን የሚመልሰውም የአገሪቱ ፖለቲካ ነውም ይላሉ።
"የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ከቀውስ ወደ ቀውስ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ መንግሥት ወጣቱን ሲያሳድድ፣ ሲገርፍና ሲገድል ነበር። ስለዚህም ወጣቱ ወይ እስር ቤት ወይ ስደት ላይ ነበር።
"ወጣቶችም አዛውንቶችም ያስፈልጋሉ" የሚሉት ዶ/ር መረራ በፓርቲያቸው በወጣቶችና በአዛውንቶች መካከል ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለና አንጋፋዎቹ ወጣቶቹ ላይ መንገድ እንዳልዘጉም ያስረዳሉ።
ጠቃሚውና ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ወጣቱም አዛውንቱም የራሱን የቤት ሥራ ቢሠራና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚታገሉ ሰዎች ትግሉን ቢገፉ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ።












