የኢትዮጵያ ምርጫ 2013፡ የትኞቹ ፓርቲዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ?

በግንቦት ወር መጨረሻና በሰኔ ወር መጀመሪያ ከትግራይ ክልል ውጪ በመላው ኢትዮጵያ ለማካሄድ በታቀደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ቢቢሲ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የኋላ ታሪክ፣ የመሪዎቻቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና አሁናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን መነሻ በማድረግ በፌዴራሉና በክልሎች እንዲሁም በከተማ መስተዳድሮች ምክር ቤቶች ድምጽ የማግኘት እድል ሊኖራቸው እንደሚችል የሚገመቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደሚከተለው ዘርዝሯል።
ፓርቲዎቹ የተዘረዘሩት በእንግሊዘኛ መጠሪያቸው ሆሄያት ቅደም ተከተል መሠረት ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/
አብን ረዥም የፖለቲካ የትግል ታሪክ ባይኖረውም በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ውስጥ ተጽዕኖው ቀላል የሚባል አይደለም።
በብሔር ተኮር የፓለቲካ እንቅስቃሴ የአማራ ብሔርተኝነትን በመወከል የሚንቀሳቀሰው አብን የተመሠረተው በ2010 ዓ.ም ነው።
ንቅናቄው ዋነኛ ዓላማዬ "የአማራ ህዝብን ጥቅምና መብት ማስከበር ነው" የሚል ሲሆን ከምስረታው በኋላ ባሉት ሦስት ዓመታት ጎልቶ መምጣት ችሏል።
ፓርቲው በአማራ ክልል በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ይታመናል። በክልሉ በርካታ ስፍራዎችም ቢሮዎችን ከፍቶ ይንቀሳቀሳል።
ከአምስት ወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከሚቀርቡ ፓርቲዎች መካከል አብን አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በቅርቡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ የነበራቸው የንቅናቄው ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ፤ ለምርጫው ሰፊ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናውን ገልጸዋል። "በሕዝብ ለመዳኘትና ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል" ዝግጁ ስለመሆናቸውም ተናገረዋል።
አብን ከአማራ ክልል ውጪም የአማራ ተወላጆች በብዛት በሚኖሩባቸው በተለያዩ የኢትዮጰያ ክፍሎች ጽህፈት ቤቶችን እያደራጀ ሲሆን ይህም በምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
ባልደራስ በቀድሞው ጉምቱ ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች በዛሬው ፖለቲከኛ አቶ እስክንድር ነገ የሚመራ ፓርቲ ነው።
አቶ እስክንድር በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስና ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ አለው። ባልደራስ "የአዲስ አበባን ጥቅም ለማስከበር" ያስጀመረው እንቅስቃሴ ሲሆን፤ እንቅስቃሴው አድጎ አዲስ አበባን መሠረት በማድረግ ወደ ፓለቲካ ፓርቲነት አድጓል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ መሪው አቶ እስክንድር የታሰርበት ባልደራስ፤ በከተማ አስተዳደሩ ይሰራሉ ያላቸውን 'ሕገ ወጥ' ተግባራት እንደሚታገል ሲገልጽ ቆይቷል።
ባልደራስ በተለያዩ ወቅቶች የሚጠራቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችና ሰልፎች ግልጽ ባልሆኑ ምክንያቶች ሲሰረዙ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
ፓርቲው በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፈጠረው ተጽዕኖ እና አቶ እስክንድር በፖለቲካው ውስጥ ባለው 'የገዘፈ' ስም ምክንያት፤ ባልደራስ በመጪው ምርጫ አዲስ አበባ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
የኢትዮጰያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/
ኢዜማ በምርጫ 97 ተሳትፏቸው የታወቁ እውቅ ፖለቲከኞችን ያቀፈ ነው።
በመላው አገሪቱ ሊባል በሚያስችል መልኩ ከ400 በላይ የምርጫ ወረዳ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቷል። ከብሔር ፖለቲካ በተለየ "ዜግነትን መሰረት ያደረገ" ፖለቲካን እንደሚያራምድ የሚገልጸው ፓርቲው፤ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ቀዳሚ ግቤ ነው ይላል።
ፓርቲው ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ መልኩ፤ በአገሪቱ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የውጪ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ 40 የፖሊሲ ሰነዶችን እንዳዘጋጀም ገልጿል።
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ሕገ ወጥ ነው ያለውን የመሬትና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወረራ በተመለከተ ያወጣው የጥናት ሪፖርት የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በ97ቱ ምርጫ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የፓርቲው መሪ፤ አቶ አንዱአለም አራጌ ደግሞ የፓርቲው ምክት መሪ ናቸው።
ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት ቀደም ብሎ የጎላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የነበረውን ሰማያዊ ፓርቲ ሲመሩ የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋን ሊቀ መንበር ያደረገው ኢዜማ፤ 6 ፓርቲዎች ከስመው የመሰረቱት ነው።
ከእነዚህ ውስጥ ነፍጥ አንግቦ ሲታገል የነበረው አርበኞች ግንቦት 7 ተጠቃሽ ነው። ይህ ድርጅት በውጪና በአገር ውስጥ ቀላል የማይባል ደጋፊዎች እንዳሉት ይገለጻል።
ታዲያ የዚህ ሁሉ ድምር ኢዜማን በምርጫ 2013 ለውጤት ከሚጠበቁ ፓርቲዎች አንዱ አድርጎታል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/
ኦብነግ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ረዥም እድሜ ያስቆጠረ ድርጅት ነው።
ከ37 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ኦብነግ መሰረቱን በሶማሌ ክልል ያደረገ ነው።
ከ1986 እሰከ 2010 ዓ. ም በትጥቅ ትግል የቆየው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፤ ከ1983-87 የነበረው የሽግግር መንግሥት አካል ነበር።
በ1984 በተከናወነው የአካባቢ ምርጫ 87 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ በማሸነፍ የሶማሌ ክልልን ለሁለት ዓመታት አስተዳድሯል።
ሆኖም በኦብነግና ማዕከላዊ መንግሥቱ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ግንባሩ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገባ አድርጎታል። በዚህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'አሸባሪ' ተብሎ ተፈርጆ ነበር።
በ2010 የጠቅላይ ሚኒሰትር ዐብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከተሎ ከሽብር መዝገብ ተሰርዞ በሕጋዊ ፓርቲነት ተመዝግቧል።
የሶማሌ ክልል ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማዬ ነው የሚለው ፓርቲው፤ በቀጣዩ ምርጫ በሶማሌ ክልል ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የፓርቲው አመራሮች በ2011 ወደ አገር ቤት በገቡበት ወቅት የተደረገላቸው 'ሞቅ' ያለ አቀባበል ግንባሩ አሁንም ያለውን ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ምርጫ ያለውንም ተስፋ የሚያመላክት ይመስላል።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ /ኦፌኮ/
በኢትዮጵያ ፖለቲካ የረዥም ዘመን ተሳትፎ ያላቸው መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የሚመሩት ኦፌኮ፤ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ተሳታፊ ነበር።
ሊቀ መንበሩ መረራ (ፕሮፌሰር) በፌዴራሉ የፓርላማ አባል ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት በፓርላማ ውስጥ በሚሰጧቸው አስተያየቶች በበርካቶች ዘንድ ይታወሳሉ። በተደጋጋሚ የታሰሩ ሲሆን ለመጫረሻ ጊዜ ከእስር ሲፈቱ በርካታ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አሁን እስር ቤት የሚገኙት ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ በቀለ ገርባ የዳበረ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው ናቸው።
በኦሮሚያ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቶ ጀዋር መሐመድ ፓርቲውን መቀላቀሉ የኦፌኮን ተጽዕኖ ከፍ እንዳደረገው ይታመናል።
መረራ (ፕሮፌሰር)፣ አቶ በቀለ እና አቶ ጀዋር ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በኦሮሚያ የተለያዩ አከባቢዎች በተጓዙበት ወቅት የተደረገላቸው አቀባል ኦፌኮ በምርጫ 2013 ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀርብ ያመላከተ ነበር።
በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ልምድ ያካበቱ ጉምቱ ፖለቲከኞችን መያዙ [ምንም እንኳን በእስር ላይ የሚገኙ ቢኖሩም] ኦፌኮን በቀጣዩ ምርጫ ለውጤት የሚጠበቅ ፓርቲ አድርጎታል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/
ከተመሠረቱ ብዙ ዓመታት ካስቆጠሩት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ ኦነግ ነው።
በበርካታ የኦሮሚያ አከባቢዎች የነጻነት አርማ ተደርጎ የሚቆጠረው ኦነግ በ1965 ዓ. ም ነበር የተመሠረተው።
ግንባሩ የ1983ቱ የሽግግር መንግሥት አካል የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ግን አማጺ ቡድን ሆኖ ጫካ ገባ። እናም ለዓመታት በትጥቅ ትግል ቆይቶ ከ3 ዓመታት በፊት የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሷል።
ከበርካታ ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር የተዘጋጀው ፓርቲው፤ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ነው።
ፓርቲው በውስጣዊ ችግሮቹ እና በፓርቲ አመራሮች እስር ታጅቦ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለውን የገዘፈ ስምና የትጥቅ ትግል ታሪክ ይዞ ምርጫው እየተጠባበቀ ነው።
ፓርቲው በመንግሥት ይደርስብኛል በሚለው ጫናና በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ በምርጫ ተሳትፎው ላይ ተጽዕኖ ካላደረገበት በስተቀር በኦሮሚያ ክልል ብርቱ ተፎካካሪ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።
ብልጽግና ፓርቲ
ብልጽግና፤ ያለፉትን 5 አገራዊ ምርጫዎች 'አሸንፊያለሁ' ያለውና አገሪቱን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲያስተዳድር የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ውጤት ነው።
ብልጽግና ከኢሕአዴግ መክሰም በኋላ አንዳንድ ለውጦችን እንዳደረገ ቢነገርም፤ ህወሓት ብቻ የተቀነሰበት የቀድሞው ኢሕአዴግ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከህወሓት ውጪ ግንባሩን ከ 'አጋሮቹ' ጋር በመዋሃድ ብልጽግና የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ፈጥረዋል።
የቀድሞውን ኢሕአዴግ ሀብት እና ንብረቶች ጠቅልሏል። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብን ሽሮ መደመር በተሰኘ የፓርቲው ፕሬዝዳንትና በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እሳቤ ተክቷል።
ፓርቲው በመላው ሀገሪቱ አለኝ ከሚለው በሚሊዮን የሚቆጠር አባላት እንዲሆም ረጅም አመታት ያሰቆጠር ጠንካራ መዋቅር በቀጣዩ ምርጫ ተጠባቂ እንዲሆን አርጎታል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ (ዶ/ር) አምጥተውታል የሚባለው ለውጥና በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ያላቸው ድጋፍ እንዲሁም ፓርቲው በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ተጽዕኖ ፈጣሪ አመራሮችን መያዙ በምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲገመት አድርጎታል።

ከላይ የተጠቀሱት አንዳንድ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች በቀጣዩ ምርጫ ላይሳተፉ እንደሚችሉ እየገለጹ ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው ፍክክር ምርጫ 2013 ከባለፉት በተሻለ ዓይን የሚጣልበት እንዲሆን አድርጎታል።












