ዝቅተኛ የሴት እንደራሴዎች ቁጥር ያላቸው አገሮች እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለምን ዐይንና ጆሮ ይዞ የቆየው የአሜሪካ ምርጫ በርከት ያሉ ሴቶችን ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ ማምጣቱ በአያሌው ተወስቷል። በአሜሪካ የሰሞኑ የ'ሚድተርም' ምርጫ ክብረ ወሰን በተባለ ቁጥር ሴቶች የሴኔት ወንበር ማሸነፋቸውን ሰምተናል።
የምርጫው ውጤት መቶ በመቶ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ እንኳ 98 ሴቶች የታችኛው ምክር ቤት በእንደራሴነት መግባታቸው ተዘግቧል።
በተለይ በአሜሪካ ሚዲያ እንዲህ በስፋት ከበሮ የሚደለቅለት ይህ የሴቶች ተሳትፎ የእኩልነት ተምሳሌት ተደርጋ ለምትታየው አሜሪካ እንዴት አስደናቂ ሆነ? ለመሆኑ በሁለቱ የአሜሪካ ምክር ቤቶች ውስጥ የሚገኘው የሴቶች ቁጥር የዓለም ምሳሌ ሊሆን ይችላል?
ጥናቶች ተቃራኒው ይመሰክራሉ። በዓለም ላይ አሜሪካንን የሚያስንቁ በርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ ቁጥር ያላቸው ሴት እንደራሴዎች አሏቸው።
ለምሳሌ በአሜሪካ በታችኛው ምክር ቤት የሴቶች ቁጥር ከጠቅላላው እንደራሴ 23 እጅ አካባቢ ነው። ይህ ለብዙ አገራት አስቂኝ ቁጥር ነው።
የኢንተር ፓርላመንታሪ ክበብ በጥቅምት 2011 ባወጣው አንድ ጥናት አሜሪካ ሴቶችን በፓርላማ እንደራሴነት በማስመረጥ ከዓለም 'ውራ ናት' ይላል። ከ193 አገራት መካከል ስትወዳደር ያላት ደረጃም 104ኛ ነው።
የ'ሚድተርም ምርጫን ተከትሎ ከፍተኛ እድገት አሳየ የተባለውን ጨምረን እንኳ ብናሰላው አሜሪካ ከዓለም 70ኛ ደረጃን ነው የሚያሰጣት። እንዲያውም በዚህ ረገድ እነ ዩጋንዳ፣ ዚምባብዌና ኢራቅ የተሻሉ ናቸው።
አሰቃቂ የእርስ በርስ ፍጅት ታሪክ ያላት ሩዋንዳ በከፍተኛ የሴት እንደራሴዎች ቁጥር ዓለምን ትመራለች።
የታችኛው ምክር ቤት 61.3፣ በሴኔት ደግሞ 38.5 በመቶ ሴት ተመራጮች ናቸው የያዙት። ኢትዮጵያ የሴት ውክልና ልቆ ከሚታዩባት ሀገሮች መካከል አንዷ ስትሆን 32 % የሴት እንደራሴዎች አሏት።
የአሜሪካ የረዥም ጊዜ የርእዮተ ዓለም ባላንጣ ኩባ ደግሞ 53.2 በመቶ የምክር ቤቷ እንደራሴዎች ሴቶች ናቸው። ቦሊቪያ፣ ሜክሲኮ፣ ግሬናዳ፣ ናሚቢያና ስዊድን ከ3-7 ያለውን የደረጃ ሰንጠረዥ ይዘውታል።
ከአፍሪካ ዝቅተኛ የሴት እንደራሴ ቁጥር ያላት አገር ናይጄሪያ ስትሆን ከጠቅላላ ተመራጮች 5.6 በመቶ ብቻ ምክር ቤት መግባት ችለዋል።
ከአለም በመጨረሻ ደረጃ የተቀመጠችው የመን ስትሆን 1.8% እንደራሴዎቿ ሴቶች እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል።













