በኢራቅ የካቢኔ አባላት በፌስቡክ ማስታወቂያ ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብዱል ማህዲ በበይነ መረብ ከተወዳደሩ 15 ሺ ሰዎች መካከል የካቢኔያቸው አባል የሚሆኑ አምስት ሰዎችን መረጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ወር ነበር በበይነ መረብ የሚካሄደውን የቅጥር ሥነ ሥርዓት ለሕዝቡ ይፋ ያደረጉት።
የካቢኔ አባል መሆን የሚፈልጉ የሃገሬው ተወላጆች ሲቪያቸውንና ብቃታቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ ማስረጃዎችን አያይዘው እንዲልኩም ተጠይቀው ነበር። እስካሁን ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጡት አምስት የካቢኔ አባላት ስማቸው አልተገለጸም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አዲል አብዱል ማህዲ አዲስ መንግሥት በአጭር ጊዜ እንዲያቋቁሙ ጥቅምት ላይ የተጠየቁት ወራትን የፈጀ ያልተቋጨ ፖለቲካዊ ምርጫ ያስከተለውን ውጥንቅጥንና የፓርቲ ፍጥጫን ተከትሎ ነበር።
ይህ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ውስጥ ያልተለመደ የቅጥር መንገድ መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ማህዲ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተዋወቀ ሲሆን፤ ከሚያስፈልጉት 14 የካቢኔ አባላት መካከል አምስቱ በዚህ መንገድ ተመርጠዋል።
ተወዳዳሪዎች ማመልከቻቸውን ሲያስገቡ የየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆናቸውን እንዲናገሩና የትኛውን የሚኒስትር መሥሪያ ቤት መምራት እንደሚፈልጉ እንዲጠቅሱ ተጠይቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያከናወኗቸውን ሥራዎች መጥቀስ ፣ ውጤታማ መሪ ምን መሆን እንዳለበት እንዲሁም በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ያለውን ችግር እንዴት እንደሚፈቱ መልሳቸውን ማስቀመጥ አለባቸው።












