ምርጫ 2013፡ ኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ በመጪው ምርጫ አጀንዳ እንዲሆን ጠየቀ

የኢሰማኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Ethiotube

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ 2013 የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የምርጫ አጀንዳ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ ይህንን ያለው ለምርጫ 2013 ሊከበሩና ሊፈጸሙ የሚገባቸው ያላቸውን "ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ" ባስተዋወቀበት ወቅት ነው።

ከዚህ ቀደም የኢሰማኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) "የዚህ ምርጫ ቅስቀሳዎች አካል መሆን አለበት ብለን የምናስበው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው" በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ "በጣም ውስብስብ እና ጥልቅ የሆነ" የሰብዓዊ መብት ቀውስ መኖሩን ገልፀው ነበር።

ኮሚሽኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢመረጡ በሰብዓዊ መብቶች ረገድ ምን ቃል እንደሚገቡ ማድመጥ እንደሚፈልጉም በወቅቱ ተናግረው ነበር።

ግንቦት 28 እና ሰኔ 15 ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላው ኢትዮጵያ ለሚካሄደው ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳዎቻቸውን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ላይም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሠልፎች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊያከብሯቸው፣ ሊፈጽሟችው እና ሊያስፈጽሟቸው ይገባል ያላቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ አደረጓል።

ኮሚሽኑ በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት እነዚህን ስድስት ነጥቦች ሊያፈጽሟቸውና ሊያስፈጽሟቸው ይገባል ሲል ገልጿል።

ባለ ስድስት ነጥቦቹ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳዎች ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች ማሳወቅ፣ ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት እንዲቆሙ፣ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ የሆነ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚሉትን ጠቅሷል።

ጨምሮም ለሰብአዊ መብት መሻሻል የሚያግዙ የሕግና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ቃል ኪዳን መግባት፣ የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዲረጋገጥ እና ከግጭት ቀስቃሽ፣ የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መቆጠብ መሆናቸው ላይ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

ለእነዚህም አጀንዳዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ባለድርሻ አካላት በይፋ ቃል እንዲገቡና እንዲሁም በገቡት ቃል መሰረት እንዲተገብሩ ጥሪውን አቅርቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) "የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በአገራዊ ምርጫው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በኮሚሽኑ የተቀመጡትን የሰብአዊ መብት አጀንዳ ነጥቦች አትኩሮት ሰጥተው እንዲመለከቷቸው፣ ቃል እንዲገቡ በጠየቅናቸው ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃልኪዳን እንዲያሳውቁ እና በአጀንዳው በተቀመጠው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በ2012 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ 2013 ዓ.ም የተሸጋገረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በተለየ ከፍ ያለ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ መንግሥትና ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን የበኩሉን እንደሚወጣ በተደጋጋሚ ቃል መግባቱ ይታወሳል።