ሰብዓዊ መብት ፡ "የሕግ የበላይነት መሰረቱ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ማክበር ነው" ኢሰመኮ

በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊመብቶች ኮሚሽን የፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድም ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል።
የኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋና ዋስትናው የፍርድ ቤት ውሳኔ መከበር መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክተዋል።
አክለውም አቶ ልደቱን ጨምሮ በፍርድ ቤት ዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ታሳሪዎች "በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊፈቱ ይገባል" ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ቢቢሲ ይህንንና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ ከሆኑት ከአቶ ምስጋናው ሙሉጌታ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ የፍርድ ቤት ውሳኔ ካለመፈጸም ጋር በተያያዘ መግለጫ ለማውጣት አልዘገያችሁም?
አቶ ምስጋናው፡ መዘግየቱን በሚመለከት ከዚህ ቀደምም ስንከታተል ነበር። በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ ይከታተላል። ሁሉንም የክትትላችንን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ማለት አይደለም። ይህንን ችግር [የአቶ ልደቱ ዋስትና መብት አለመከበር] መነሻ ተደርጎ ነው እንጂ፣ የተወሰኑ የተደጋጋሙ ነገሮችም አሉ።
እንደዚህ በስም ታዋቂ ያልሆኑ የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው ነገር ግን በፖሊስ እስር ስላሉ ሰዎች የደረሱን ጥቆማዎች አሉ። ስለዚህ ይህ በአጠቃላይ አሁን የአቶ ልደቱ ታዋቂም ስለሆኑ፣ ብዙ ሰው ጉዳያቸውንም ስለሚከታተል ጥሩ ማሳያ ይሆናል በሚል ነው እንጂ፤ አሁንም እየተከሰተ ያለ ነገር ስለሆነ ዘግይቷል ብዬ አላስብም።
ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለው ግን በእኛ እምነት ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር በዋነኛነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው። የመንግሥት አካላትም እኛ ያወጣነውን መግለጫ መሰረት በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳሉ። የሕግ የበላይነት የሚባለው መሰረቱ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ስለሆነ ነው።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ መግለጫዎችን ታወጣላችሁ። እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ከመንግሥት አካላት ጋር ትነጋገራላችሁ?
አቶ ምስጋናው፡ አዎ እንነጋገራለን። እንዲህ አይነት መግለጫ ማውጣት አንደኛው ፋይዳ የመንግሥት አካላትም ነገሩን እንዲገነዘቡ፣ ሕብረተሰቡም ይህንን እንዲረዳውና ግፊት እንዲያደርግ እድል እፈጥራል ብለን እናስባለን። እንነጋገራለን።
መግለጫዎች ከማውጣታችን በፊት ችግሮች ሲደርሱ፣ ከደረሱ በኋላ ምርመራ አድርገን የማስተካካያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እናደርጋለን። አንዳንዶቹ ይፈታሉ፤ አንዳንዶቹ ጊዜ የሚወስዱ ናቸው ተብሎ ቃል ይገባልናል። እነርሱንም ግን መተግበራቸውን እንከታተላለን።
መግለጫዎቹ በመንግሥት ላይም ሆነ ይህንን ውሳኔ በሚወስኑ አካላት ላይ ጫና ይፈጥራሉ ብለን እናስባለን እና በዚያ መልኩ ነው እየሄድንበት ያለነው። ግን ይህ የሚቆም ነገር ሳይሆን ከአሁን በኋላም የምንቀጥልበት ነው።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈርጀ ብዙ ናቸው። በተለያዩ ስፍራዎች የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይሰማሉ። በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት ጥሰቶች ስፋትና ጥልቀት የእናንተ ሪፖርት ምን ያህል ሁሉንም ይሸፍናል?
አቶ ምስጋናው፡ በሚፈለገው መጠን ሁሉም ቦታ ላንደርስ እንችላለን። ሰብዓዊ መብቶች እንደምታውቀው ለሁሉም ነው ተግባራዊ የሚሆኑት። አይበላለጡም፤ የማይነጣጠሉ ናቸው። አንድ ሰብዓዊ መብት ከአንድ መብት አያንስም። አንድ አካባቢ የሚደርስ ነገር ከአንድ ቦታ አይበልጥም። ይህ በመርህ ደረጃ በደንብ መሰመር ያለበት ነው።
ኮሚሽኑ ሪፎርም ላይ ነው፤ የአቅም ውሱንነት አለበት። ስለዚህ ሁሉም ቦታ ለመድረስ ላይችል ይችላል። ግን በተቻለ መጠን ዋና ዋና የሚባሉትን ለመመርመር ለመከታተል እየሞከርን ነው። ለምሳሌ በወላይታ ምርመራ አድርገናል። በቅርቡም ኦሮሚያ ውስጥ የተከሰቱ ጥሰቶችን ለመመርመር ባለሙያዎች ልከን ምርመራ አድርገናል።
የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲደረጉ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አካላትን እየወተወትን እንገኛለን። እና ከችግሩ ስፋት አንጻር በአቅም ውሱንነት ምክንያት ያላየናቸው ይሆናሉ እንጂ የቁርጠኝነት ችግር የለም። በቅርቡም የሚወጡ ሪፖርቶች ይኖራሉ።በዚህም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱና ወደፊት እንዳይደገሙ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው።
እንደሚሉኝ በእናንተ በኩል ተነሳሽነቱ ካለ ዋነኛ ችግሮቻችሁ ምንድን ናቸው?
አቶ ምስጋናው፡ አንደኛው የአቅም ነው። ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ አገር ናት። የሰብአዊ መብት ጉዳዮች እዚህም እዚያም በተደጋጋሚ ይነሳሉ። በተለይ ከግጭት ጋር የተያያዘ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰፊ ናቸው። ስለዚህ ኮሚሽኑ የባለሙያዎች ብዛትና የሀብት ክፍተቶች አሉ።
ሁለተኛ በተቻለ መጠን ሰፊ የሆነ ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ እየተሞከረ ነው። ነገር ግን በተለይ አሁን ያለንበት ሁኔታ ነገሮች በጣም በፍጥነት እየተከሰቱና ሰፊ ቦታ እየሸፈኑ ነው። እንደዚያም ሆኖ በእኛ እምነት ዋና ዋና የሚባሉትን በደንብ እየተከታተልን ነው።
የምንከታተለውን በሙሉ ለሕዝብ ይፋ ላናደርግ እንችላለን። ግን ባለን አቅም ያለምንም ማበላለጥ ጉዳዮቹን ለመከታተል ጥረት እያደረግን ነው። አቅማችን ደግሞ ሲጠነክር በሚታይ መልኩ ተደራሽነታችንን እናሰፋለን ብለን እናምናለን።
ከየትኛው የመንግሥት አካል ጋር ነው በደንብ በቅርበት እየሰራችሁ ያላችሁት?
አቶ ምስጋናው፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ተቋም ነው። ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር እንደ አስፈላጊነቱ ግንኙነት እናደርጋለን። ለምሳሌ ለፓርላማው ነው ተጠሪነታችን በዋነኝነት። የእኛም ሥራ እንደ ቁጥጥር ሥራ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። እና እኛ እንደ አግባብነቱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የምናገኛቸውን ግኝቶች እናነሳለን። መፍትሄ እንዲሰጣቸው እናደርጋለን። እና በዚያ ረገድ ነው መታየት ያለበት።
በዋነኛነት የሰብዓዊ መብት ማክበር ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ስለዚህ ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውን እንከታተላለን። እንዲወጡ እንወተውታለን። ጥሰቶችም ሲገኙ ያው ምርመራ አድርገን በተቻለ መጠን ተጠያቂነት እንዲኖር እና ወደፊት እንዳይደገም የማድረግ ነገር ነው ያለን።















