ሃጫሉ ሁንዴሳ፡ የጥቃት ሰለባዎች አሁንም ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ

ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል ሻሸመኔ ከተማ አንዷ ነች

የፎቶው ባለመብት, -

የምስሉ መግለጫ, ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል ሻሸመኔ ከተማ አንዷ ነች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ባደረገው ምርመራ የጥቃት ሰለባዎች የነበሩት ሰዎች አሁንም የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው አመለከተ።

ኮሚሽኑ ለሁለት ሳምንታትም ከ40 በላይ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ያሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ምስክሮችንና የመንግሥት አካላትን በማነጋገር መረጃ በማሰባሰብ አሁን ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ዝርዝር የምርመራው ግኝቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች አቅርቧል።

የነዋሪዎች የጥቃት ስጋት

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ ምርመራ በተደረገባቸው በአብዛኞቹ አካባቢዎች መረጋጋት ያለ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ አጠቃላይ የደኅንነት ስጋት እንዳለና ተጎጂዎቹ አሁንም በተለያዩ ቡድኖች የጥቃት ማስፈራሪያና ዛቻዎች እየደረሳቸው እንደሆነ ለኮሚሽኑ መናገራቸውን ጠቅሷል።

መግለጫው እንደማሳያ በዶዶላ ከተማ የሚገኙ ተጠቂዎች በሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከ60 በላይ ሰዎች ስም ተዘርዝሮ ከተማውን ለቅቀው እንዲወጡ ካልሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የሚገልጽ የማስጠንቀቂያ ወረቀት መሰራጨቱን ከነዋሪዎች መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

እንዲሁም በባቱ (ዝዋይ) ከተማ ተጎጂዎች ከተማውን ለቅቀው እንዲወጡ የሚል ማስፈራሪያ በስልክና በአካል እየደረሳቸው መሆኑን፤ በሻሸመኔ ከተማ ደግሞ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ቤት ለቤት በመሄድ ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር ካላመጣችሁ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን እንዲሁም እንገላችኋለን በማለት ዛቻ እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በተወሰኑ አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት ሳይቀር ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን የጠቀሰው የኮሚሽኑ ሪፖርት በምሳሌነትም የቡራዩ ከተማ በተለይ ከታ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ እንዲሁም የጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ በነዋሪዎች ላይ ያለውን የደኅንነት ስጋት በተመለከተም መንግሥት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አክብሮ የመንቀሳቀስና በሌሎች መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላትም ጥሰት እንዳይከሰት የመከላከልና ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ብሏል።

የችግሩ ሰለባዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ ለሌላ ጥቃት እንዳይዳረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ጠቅሶ፤ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት የነዋሪዎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ፣ አጥፊዎችን እንዲቆጣጠሩና የሕግ አስከባሪ እና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብሩ ጠይቋል።

የተፈናቀሉ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ

ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ አለመረጋጋቱ ተከስቶባቸው በነበሩት አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች "አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው" ለማወቅ እንደቻለ ገልጿል።

ስለዚህም ለተጎጂዎቹ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊና ሌሎች ድጋፎችን ማቅረብ እንዲሁም የተፈናቀሉት ደግሞ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ጊዜ የማይሰጠው በመሆኑ ትኩረት በመስጠት ዕለታዊ ድጋፍና በዘላቂነት የሚቋቋሙበት መፍትሔ መሰጠት እንዳለበት ጠቅሷል።

ከዚህ አንጻርም የመኖሪያ ቤታቸውና ንብረታቸው የወደመባቸው ተጎጂዎች አሁን ድረስ በሰው ቤትና በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ መሆኑንና እነዚህን ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን፣ በተለያዩ ወገኖች የሚሰጣቸው የዕለት ምግብ እርዳታና የህክምና አገልግሎትእንዲሁም በቂ አለመሆኑን ጠቅሷል።

በተወሰኑ አካባቢዎችም በተለይም በአብያተ ክርስትያናትና በሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎችን "ለደኅንነታቸው ማረጋገጫ ባልተሰጠበት ሁኔታ የመንግሥት ኃላፊዎች ወደ ቤታችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አታገኙም" የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ መጫናቸውና ሻሸመኔና አጋርፋ ለአብነት በመጥቀስ ይህ ግፊት ተገቢ አለመሆኑንም አመልክቷል።

ኮሚሽኑ የችግሩ ሰለባዎች ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ መንግሥት አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግና በተለይም ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የክረምት ወቅት በመሆኑ ተጎጂዎች ለተጨማሪ ችግር እንዳይዳረጉ ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ በተጨማሪም ግብረሰናይ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የእስረኞች አያያዝ

ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በጎበኛቸው የእስር ቦታዎች አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች መመልከቱን ገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ ተጠርጣሪዎች በአነስተኛ ቦታ ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ መታሰራቸውን ለወረርሽኝ ያላቸውን ተጋላጭነት እንደሚጨምረው ሪፒርቱ ጠቅሶ፤ የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት አነስተኛ መሆኑ፣ በተወሰኑ ታሳሪዎች ላይ ድብደባና ኢሰብዓዊ አያያዝ ጥሰት መፈጸምና አለመጣራቱ እንዲሁም ተጠያቂነት ያለመኖሩን አመልከልቷል።

በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ሕፃናትና አዋቂዎች አንድ ላይ መታሰራቸውን ኮሚሽኑ እንደችግር ያነሳው ሲሆን የተወሰኑ ታሳሪዎች በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት አለማቅረባቸው እንዲሁም ፍርድ ቤት በዋስትና የለቀቃቸውን እስረኞች በተለያዩ ምክንያቶች በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸውን ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸው ወድሞባቸው እርዳታን ያስፈልጋቸው እንደነበር የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ከሳምንታት በፊት ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በልሉ 523 መኖሪያ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን 499 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፤ በተጨማሪም 195 ሆቴሎች መቃጠላቸውን ሌሎች 32 ሆቴሎች ደግሞ በንብረታቸው ላይ የመሰባበር ጉዳት መድረሱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ከሁከቱ ጋር ተያይዞም በሺህዎች የሚቆተሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።