ኢሰመኮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ቡድን ማሰማራቱን ገለጸ

አርማ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን ማሰማራቱን አስታወቀ።

ከአርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ በኋላ በተከሰተው የጸጥታ ችግር በሕይወትና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርብ መከታተል መቀጠሉን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥራ ማሰማራቱን እና በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ ስልታዊ ክትትል እያደረኩ እገኛለሁ ብሏል።

ኢሰመኮ የሚያደርገው ምርመራ ውጤት የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓይነት፣ መጠን፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የተጎዱ ሰዎች የሚካሱበትና መልሶ የሚቋቋሙበት እንዲሁም ይህን የመሰለ ጥሰት ድጋሚ ከመከሰት ለመከላከል ስለሚያስችሉ እርምጃዎች ተገቢ ግብዓት እንደሚሆን እምነቱን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ በወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎችም የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ በተከታታይ መመልከቱንም አስታውቋል።

በተለይም እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ እስክንድር ነጋ በመጀመሪያ ላይ ታስረው ይገኙ የነበረበትን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ያለውን እስር ቤት፣ እንዲሁም አሁን የሚገኙበትን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሚገኘው እስር ቤት በተጨማሪም በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን ጊዜያዊ የእስር ቤት ኮሚሽኑ መጎብኘቱን እና ታሳሪዎችንና ኃላፊዎችንም ማነጋገሩን ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ የእነ አቶ እስክንድር ነጋ የእስር አያያዝ ላይ እንዲሻሻል ምክረ ሀሳብ የሰጠባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ መደረጋቸውን፣ እንዲሁም በዋስትና መብት ሊለቀቁ ስለሚገባቸው የተወሰኑ ታሳሪዎች የሰጠው ምክር ሃሳብም በሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተግባራዊ መደረጉን በመልካም እርምጃነት እውቅና እሰጣለሁ ብሏል።

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ ስድስት ታሳሪዎች አሁን የሚገኙበት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ መሆኑን ገልጿል።

ጨምሮም ንጽህናው የተጠበቀ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚያገኝ፣ ታሳሪዎቹ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከቤተሰብ አቅርቦት የሚቀበሉበትና ለመተያየት የሚችሉበት፣ በአጠቃላይ አነጋገር ተቀባይነት ደረጃ ያለው ሲሆን፤ በተወሰነ መልኩ ከወቅቱ የአየር ጸባይና ከሕንጻው ባሕሪ የተነሳ የመቀዝቀዝ ጠባይ ያለው በመሆኑ ቅዝቃዜውን ለመቀነስ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተመልክተናል ብሏል ኮሚሽኑ።

ኮሚሽኑ ጨምሮ እንዳለው፤ ከታሳሪዎች ከቤተሰብ ጋር በተገቢው መጠን ተቀራርቦ ለመተያየት አለመቻላቸው፣ የክፍሎቹ መቀዝቀዝ፣ የፀሐይ መቀበያ ጊዜ ማጠር፣ የመብራት መቋረጥ የመሳሰሉ ቅሬታዎች ደርሰውኛል ብሏል።

ኮሚሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን እና አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታተል አስታውቋል።

በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ከሚገኙ ታሳሪዎች መካከል የኦኤ.ምኤን ጋዜጠኞች አቶ ጉዮ ዋርዮ እና አቶ መሀመድ ሲራጅ፣ የኦፌኮ አባል አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዲሁም ሦስት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችን ኮሚሽኑ መጎብኘቱን አስታውቋል።

አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳልተፈጸመባቸው ተናግረው ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ልንሆን እንችላለን የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል ብሏል።

የውጪ አገር ዜጎቹን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች እስካሁን ከቤተሰብ አባላት ጋር አለመገናኘታቸውን እንደገለጹለት ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ከበርካታ ታሳሪዎች የተነሳለት ቅሬታ፤ እስካሁን ቃላቸውን ለመርማሪ ፖሊስ አለመስጠታቸው እና በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መሆኑ ነው።

ኮሚሽኑ የፍትሕ አካላት ውስን በሆነ አቅም በርካታ ጉዳዮችን በማጣራት የሥራ ጫና ያለባቸው ቢሆንም በተቻለ መጠን የምርመራ ሥራውን እንዲያቀላጥፉ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ታሳሪዎች በሚመለከት ኮሚሽኑ በቅርቡ ለመመልከት በዝግጅት ላይ ያለ ቢሆንም፤ ብዙ ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ በተሟላ ሁኔታ ያለወቁ በመሆኑ ሁሉም ታሳሪዎች ለቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ በስልክ እንዲያስታውቁ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ሰጥቼያለሁ ብሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የታሳሪዎች ጉዳይን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት "አሁን ባለው የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ሁኔታ፤ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ በቅድሚያ ትኩረት ሊያከናውኑ የሚገባቸው ያላቸውን ጉዳዮች ጠቅሷል።

በዚህም መሰረት ሁሉም ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ በማናገር ያሉበትን ቦታ ማሳወቃቸውን ማረጋጥ እና በተፋጠነ ምርመራ በዋስትና መብት ወይም በነጻ ሊፈቱ የሚገባቸውን ታሳሪዎች በመለየት በአፋጣኝ መለቀቃቸውን ማረጋገጥ መሆኑን አመልክቷል።