"የሌሎችን ንብረት ከውድመት ለመከላከል በሄድኩበት፤ ሌሎች ደግሞ የእኔን ቤት አትርፈውታል"

የኢትዮጵያ ካርታ

ከሦስት ሳምንታት በፊት የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያን ተከትሎ የአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች የተከሰውን ነገር ድንገተኛ ዱብዳ እንደሆነ ነው አሁን ድረስ የሚሰማቸው።

የሃጫሉ ግድያ ዜና በተሰማ በሰዓታት ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ከተሞችና መንደሮች በጥቃት ፈጻሚዎች መወረራቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ግለሰቦች በዘመናት ጥረት ያቆሟቸው መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ከነሙሉ ንብረታቸው የእሳት እራት ሆነዋል።

ጎራ ለይተው በድንገት ለጥፋት የተሰማሩት ጥቃት ፈጻሚዎች ምንም እንኳን ያደረሱት ጉዳት ያልታሰበና ከባድ ቢሆንም በየአካባቢዎቹ ያሉ ቀና ሰዎች ጥረት ባይታከልበት ኖሮ ከዚህ የባሰ ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ቤት ንብረታቸው ወድሞ በህይወት የተረፉ ሰዎች ለቢቢሲ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ግን እንዲህ ያሉ ቀናና ሰብዓዊነት የተላበሱ አስተዋይ አባቶችና እናቶች ባሉበት ከተማና አካባቢ ያንን ሁሉ ጥፋት የግፍ ግድያ የፈጸሙ ጥቃት ፈጻሚዎች ከወዴት እንደመጡ የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ታዲያ በተለያዩ ስፍራዎች ጥቃቱ የተፈፀመባቸውና ንብረታቸው እንደወደመባቸው የሚናገሩ ሰዎች በህይወት ለመትረፋቸው ምክንያት የሆኗቸው ለዘመናት አብረው በጉርብትና የኖሯቸው ሰዎች ድፍረት የተሞላበት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል።

የጥቃቱ ኢላማ የነበሩ ሰዎችን ከአጥቂዎች በመታደግ በኩል ቢቢሲ ካነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች መካከል ስማቸው በበጎ እየተደጋገመ ከሚነሱት በጎ ሰዎች መካከል የባቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ተስፋዬ ኤዳኦ ሴሮ ይጠቀሳሉ።

አቶ ተስፋዬ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው። የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን የሚተዳደሩት በግል ሥራ ነው። በአካባቢያቸው ባለ ቤተ ክርስቲያን እና ልጆችን በሚደግፍ ፕሮጀክት ላይም ለማኅበረሰባቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማደረግ በነዋሪው ዘንድ ይታወቃሉ።

በከተማዋ ምን ተከሰተ?

"ክስተቱ ከመፈፀሙ በፊት የሰማነው ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን አገር ሰላም ብለን በተኛንበት ሌሊት ላይ ጩኸት ሰማን" ይላሉ አቶ ተስፋዬ፤ ጩኸቱ ከሰፈራቸው ራቅ ብሎ ነበር የሚሰማቸው።

ጩኸቱን ለማጣራት ሲወጡም በአካባቢው የማይታወቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተመለከቱ። ከዚያም ጨለማው እየገፈፈ ሲመጣ ወደ እርሳቸው ሰፈርም በመምጣት የሰው ቤት መደብደብ ጀመሩ። የአካባቢው ሽማግሌዎችና ሌሎች ወጣቶች በጋራ ሆነው "ይህ ለምን ይሆናል?" በማለት "ባለን አቅም ድርጊቱን ለማስቆም መሞከር ጀመርን" በማለት ሁኔታውን ያስታውሱታል።

አቶ ተስፋዬና ጎረቤቶቻቸው ጣልቃ ገብተው ጥቃት ፈጻሚዎቹ "ተዉ" ባይሉ ኖሮ በአካባቢው ከደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በላይ የከፋ ይደርስ እንደነበር ነዋሪዎች ይመሰክራሉ።

በጥቃቱ ዕለት ጎረቤታቸው የሆነና ሆቴሉ የተቃጠለበት አንድ ግለሰብ ሆቴሉ በእሳት እንድወድም መደረጉንና እንዲደርሱለት ሲጠራቸው ፈጥነው የደረሱት አቶ ተስፋዬ፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ መኖሪያ ቤቱን ለማውደም በመሄዳቸው 'አይ ቤት ሂድና ልጆቼን ከቤት አድንልኝ' ተብለው እንደተላኩ ይናገራሉ።

ስለሁኔታ እውነታነት የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ "ልጆቹንና ቤተሰቡን ወደ እኛ ቤት ወስደን ካስገባን በኋላ፤ መኪናውን በማውጣት፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመተጋገዝ ቤቱ ደጅ ላይ ለሰዓት ያህል ቆመን ተከላክለን አትርፈንላቸዋል" ሲሉ ይህንን ለወገንና ለጎረቤት በጥቃት ጊዜ የመድረስ ተግባራቸውን ለሌሎችም በመፈጸም አረጋግጠዋል።

እንደ አባት እንደ አካባቢ ሽማግሌ ከጎረቤቶቸቻው ጋር ቆመው ድርጊቱን ለማስቆም የጣሩት አቶ ተስፋዬ "ማፍረስ፣ ማቃጠል አትችሉም። ቤት ማቃጠል ነውር ነው፣ መዝረፍ ነውር ነው፤ ይህ ባህላችን አይደለም" እያሉ ፊት ለፊት በመጋፈጥና በሰዎች በር ላይ በመቆም እንደተከላከሉ ያስረዳሉ።

አቶ ተስፋዬ ጥቃት ፈጻሚ ወጣቶቹ ከመጮህ እና 'ዞር በሉ እናጥፋ!' ከማለት ውጪ፤ ለምን ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ ትርጉም ያለው ነገር ሲናገሩ አለመስማታቸውን ይናገራሉ።

በዚህም ነዋሪው ጣልቃ ሲገባና ድርጊቱን ሲያወግዝ ያሰቡትን መፈጸም እንደማይችሉ ሲያውቁ "በወቅቱም ሰዎች ሲተባበሩና መከላከሉ ሲጠናከር አልፈው ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ" ብለዋል።

እነዚህ ጥቃት አድራሾች የማይታወቁና ቁጥራቸው በርካታ መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋዬ፤ አንዱ ለአንዱ እንኳን እንዳይደርስ ተከፋፍለው በተመሳሳይ ሰዓትና ሁሉም ቦታ መሰማራታቸውን ይገልፃሉ።

አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት በጥቃቱ የተለያዩ ብሔሮች ላይ ጉዳት መድረሱን በመጥቀስ፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ እንዲሁ በዘፈቀደ ዝም ብለው መደዳውን ደህና ቤት ሲያዩ ጥቃት ለማድረስ ከመሮጥ በዘለለ፤ በከተማቸው ውስጥ እየመረጡ ነው ጥቃት ያደረሱት የሚል እምነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ።

"ሁሉም ወጣት አንድ አይደለም፤ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚተባበሩ ወጣቶች አሉ" የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ እርሳቸው የሌላውን ቤት ከጥቃት ለመከላከል በወጡበት ሰዓት፤ የእርሳቸውን ቤት ከቃጠሎ ያተረፉት ሌሎች ጎረቤቶቻቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ተስፋዬ ከዚህ በፊት በግለሰብ ደረጃ ከሚፈጠሩ ግጭቶች ውጪ እንደዚህ ዓይነት ወረራ በዘመናቸው አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

"እኛ ይህ ለምን እንደሆነ አናውቅም፤ ፈጣሪ ይወቅ፤ ከየትና እንዴት እንደመጣ አናውቅም፤ እንደ ቤተክርስቲያን ሰው ፈጣሪ ይወቅ፤ የመጣውን እግዚአብሄር ይመልስ ነው የምንለው" ይላሉ።

የአካባቢው ማኅበረሰብም እንደ ኢትዮጵያዊነቱ፤ በሠርግም በለቅሶም፤ ክፉውንም ደጉንም አብሮ ማሳለፍ እንጂ በብሔር መነጣጠል አለመኖሩን በማውሳት በከተማቸው ውስጥ ያጋጠመው ጥቃትና ውድመት መነሻው ምን እንደሆነ ለመረዳት ተቸግረዋል።

"በማኅበረሰባችን ውስጥ የአብሮነት ስሜት እንጂ መነጣጠል በባህላችንም የለም፤ ይህ አዲስ ክስተት ነው፤ የምናውቀው ነገር የለም" ሲሉ የጥቃት ፈፃሚዎቹ ድርጊት የአንድ ወገን መገለጫ አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ሁሉንም የጎዳ ጥቃት

የባቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ተስፋዬ፤ በደረሰው ውድመት የንብረት ባለቤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የከተማው ነዋሪዎችና አልፎ ሂያጅ መንገደኞችም ጭምር ነው የተጎዱት ይላሉ።

"የተጎዱት ሰዎች ወንድሞቻችን ናቸው፤ ከእነርሱ ጋር ብዙ መስተጋብር አለን። የእነርሱ አዕምሮ ሲጎዳ፤ እኔም ነኝ የተጎዳሁት" ብለዋል።

የወደሙት ሱቆች፣ ሆቴሎችና ሌሎች ተቋማት አገልግሎት ባለመስጠታቸው ተገልጋዩ መቸገሩንም በመግለጽ፤ እነዚህ ድርጅቶች ግብር ከፋይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ተስፋየ፤ "በውድመቱ ከተማዋ፤ ከፍ ሲልም አገር ተጎድቷል፤ በዚህም አዝነናል" ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

"ባህላችንን መልሰን ማደስ አለብን"

አቶ ተስፋየ እንደ አገር ሽማግሌነታቸው በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ያለውን መሰል ድርጊት ለማስቆም ይበጃል የሚሉት ሃሳብ አላቸው። ይህም "ባህላችንን መልሰን ማደስ አለብን፤ ባህልን የሚጥሰውን አዲሱን ትውልድ ባህላችንን ማስተማር አለብን" ይላሉ።

ጨምረውም ተቻችሎ፣ ተከባብሮና ተደጋግፎ የመኖር ባህልን እየጣሰ የሚሄደውን ትውልድ በቤተ እምነትና በባህል መግራት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

የቤተ እምነት መሪዎች ወጣቶቹን በእምነታቸው እንዲጓዙ ማድረግና ማረም እንዳለባቸው የሚጠቅሱት አቶ ተስፋዬ " ሽማግሌዎች መምከር አለብን፣ በእምነት ቤት ያሉ ሰዎች ደግሞ ማስተማር፣ የባህል ሰዎችም ባህሉንም እንዲያውቁ ማድረግ፣ አባ ገዳዎችም ኅብረተሰቡ አንድ እንደሆነና በአንድነት መራመድ እንዲችል ማስተማር አለባቸው" ብለዋል።

"ሰው ፈጣሪን ካልፈራ፤ በራሱ መንገድ ይሄዳል፤ በመሆኑም ልጆች ፈጣሪን እንዲፈሩ ማስተማር ያስፈልጋል፤ ሰው መንግሥትን የሚሰማው እምነት ሲኖረው ነው" ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በከተማቸው የተከሰተው ነገር በተመለከተ አንድ ነገር ለማድረግ እየጣሩ ነው።

በዚህም ከተፈጠረው ጥቃትና ውድመት በመማር ዳግም እንዳይከሰት ጊዜ ሳይወስዱ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ከተለያዩ ቤተ እምነቶች ጋር በጋራ እየተወያዩ እንደሆነና በዚህ መልኩ ትውልዱን ለመቅረፅ መሰራት የሚገባቸውን ለማከናወን እየሞከሩ እንደሆነ ገልፀዋል።